መቻል ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

የሊጉ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ለማድረግ የቀናት ጊዜ የቀራቸው መቻሎች የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር ማጠናቀቃቸው ታውቋል።

በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚመሩት መቻሎች በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ውድድር ያደረጉትን ተሳትፎ አሸናፊ ካጠናቀቁ በኋላ በያዝነው ሳምንት መጨረሻ የሊጉ ቀዳሚ ጨዋታቸውን ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ከማድረጋቸው አስቀድሞ የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቀዋል።

ክለቡን የተቀላቀለው አጥቂው ያሬድ ከበደ ሲሆን የእግርኳስ ህይወቱን በአክሱም ከተማ ጀምሮ ወደ መቐለ 70 እንደርታ በማምራት በክለቡ ለአራት ዓመታት ቆይታ የነበረው ይህ ተጫዋች በአማካይ፣ በመስመር እና በአጥቂነት መጫወት ይችላል። ምዓም አናብስት የሊጉን ዋንጫ ሲያነሱ ቁልፍ ተጫዋቾች የነበረው ያሬድ ከመቐለ የዓመታት ቆይታው በኋላ በ2013 የውድድር ዓመት በሲዳማ ቡና የተጫወተ ሲሆን አሁን ደግሞ ከዓመታት በኋላ ለአንድ ዓመት ለመቻል ለመጫወት ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚመልሰውን ዝውውር ፈፅሟል።

ሌላኛው ፈራሚ አጥቂው ሙሀባ አደም ሆኗል።
በሲዳማ ታዳጊ ቡድን የእግርኳስ መነሻውን ያደረገው ወጣቱ አጥቂ በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና በ2010 በሴካፋ ዋንጫ ለፍፃሜ በደረሰው ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሙሉ ጨዋታ በተከላካይነት ተጫውቷል። በመቀጠል በሲዳማ ተስፋ ቡድን ከተጫወተ በኋላ ባሳለፍነው ዓመት በአንደኛ ሊግ ለተሳተፈው በወንዶ ገነት ቡድን ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ሲያጠናቅቅ ዘንድሮ በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ጥሪ ከመቻሎች ጋር አብሮ ልምምድ ሲሰራ ቆይቷል። በተለይ በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ላይ ለቡድኑ ጎል በማስቆጠር ባሳየው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ለሦስት ዓመት ለመቻል ለመጫወት ፊርማውን አኑሯል።