ከፍተኛ ሊግ | አርባምንጭ ከተማ ስምንት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

ከፕሪምየር ሊጉ የወረደው አርባምንጭ ከተማ የአዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲቋጭ የነባሮችን ውልም አድሷል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ያለፈውን ዓመት ሲሳተፍ ቆይቶ በሰበሰባቸው ነጥቦች መነሻነት ወደ ከፍተኛ ሊጉ ለመውረድ የተገደደው አርባምንጭ ከተማ በቶሎ ወደ ነበረበት ለመመለስ በከፍተኛ ሊጉ ለሚኖረው ጉዞው አስቀድሞ አሰልጣኝ በረከት ደሙን ከጊዜያዊ ወደ ዋና አሰልጣኝነት በመሾም አስከትሎም ሦስት በክለቡ የነበሩ ተጫዋቾችን ውል በማራዘም ልምምድ የጀመረው ክለቡ አሁን ደግሞ ስምንት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የሁለት ነባር ተጫዋቾችን ውል ማራዘሙን ከክለቡ የደረሰን መረጃ አመላክቷል።

ሰለሞን ሀብቴ የክለቡ አዲሱ ፈራሚ ሆኗል። ረዘም ያሉ ዓመታትን በደደቢት ካሳለፈ በኋላ በመቀጠል በወላይታ ድቻ ፣ ፋሲል ከነማ እና ያለፉትን ሁለት ዓመታት በሲዳማ ቡና ካሳለፈው በኋላ በግራ መስመር ተከላካይ እና አጥቂነት እንዲሁም በአማካይ ቦታ ላይ መጫወት የሚችለው ተጫዋቹ ወደ አርባምንጭ አምርቷል።

የመስመር ተከላካዩ ሳሙኤል አስፈሪም ሌላኛው የአርባምንጭ ፈራሚ ነው። በዱራሜ ከተማ ፣ አረካ ከተማ እና የካ ክፍለ ከተማ ፣ አዲስ አበባ ከተማ እና የተጠናቀቀውን ዓመት በወልቂጤ አሳልፎ ቀጣይ መዳረሻው አርባምንጭ ሆኗል።

ቡድኑ በድሬዳዋ ከተማ ወላይታ ድቻ ፣ አዲስ አበባ ከተማ ፣ በቀድሞው አጠራሩ ኢትዮጵያ ውሀ ስራዎች ፣ ገላን ከተማ ፣ በኢትዮጵያ መድን እና የተጠናቀቀውን ዓመት ደግሞ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያሳለፈውን የመሐል ተከላካይ ፀጋ አለማየሁን ፣ የቀድሞው የጋሞ ጨንቻ ፣ አርባምንጭን በመልቀቅ በወላይታ ድቻ ቆይታ የነበረውን የመስመር አጥቂው ፍቃዱ መኮንን ፣ በደቡብ ፖሊስ ፣ ደሴ ከተማ ፣ ነቀምት ከተማ ፣ ሀምበሪቾ ፣ የካ እና አምና በሀላባ ከተማ የነበረው የቀድሞው የክለቡ አጥቂ አላዛር ዝናቡን ጨምሮ ፣ ተመስገን መንገሻ አጥቂ ከኦሜድላ ፣ ብሩክ ባይሳ የመሐል ተከላካይ ቡሌ ከነቀምት እና ደሳለኝ አሎ አማካይ ከጋሞ ጨንቻ ክለቡን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ናቸው።

ክለቡ ከአዳዲስ ፈራሚዎቹ በተጨማሪ የበላይ ገዛኸኝ እና አሸናፊ ተገኝን ኮንትራት ስለ ማደሱም ታውቋል።