የፕሪምየር ሊጉ የነገ ተጋጣሚ ክለቦችን ዝግጅት የተመለከተ ፅሑፍ በሚከተለው መልኩ አሰናድተናል

የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሁለት ጨዋታዎች ነገም ይቀጥላል። እኛም በዚህ ፅሑፋችን ጨዋታቸውን ስለሚያከናውኑት ሻሸመኔ ከተማ ፣ ወላይታ ድቻ ፣ ሀምበሪቾ እና ድሬዳዋ ከተማን የተመለከቱ ጥልቅ ጥንቅሮችን አቅርበንላችኋል።

የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያሳለፍነው ዕሁድ መስከረም 20 በተደረጉ ሁለት መርሀግብሮች በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የኒቨርሲቲ ስታዲየም ላይ መጀመሩ ይታወሳል። አህጉራዊ ውድድሮች የነበሩባቸውን ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህርዳር ከተማ ከውድድር እስኪመለሱ በሚል ለሦስት ቀናት በዕረፍት የቆየው የሊጉ ውድድር በነገው ዕለት ተመልሶ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጉበታል። እኛም በዛሬው ጥልቅ የዳሰሳ ፅሑፋችን በነገው ዕለት ጨዋታቸውን የሚያከናውኑ አራት ክለቦች ስለነበራቸው ዝግጅት እና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ በተከታዩ ፅሑፋችን አቅርበናል።

ሻሸመኔ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

– የሊጉ እንግዳ ቡድን ሻሸመኔ ከተማ በ2000 ከተሳተፈበት የሚድሮክ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር በኋላ ማለትም ከ15 ዓመታቶች መልስ የመጀመሪያ ጨዋታውን በነገው ዕለት በፕሪምየር ሊጉ እየተሳተፈ አስረኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘውን ወላይታ ድቻን ከቀትር መልስ 09፡00 ሲል የሚያስተናግድበትን  የመጀመሪያ ሳምንት ሦስተኛ የሊጉ ጨዋታን እንመለከታለን። የተጠናቀቀውን ዓመት በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ ስር ከተደለደሉ ክለቦች መካከል አንዱ የነበረው ሻሸመኔ ከተማ በምድቡ የመጀመሪያውን ዙር ውድድር ወጥ ባልሆነ የውጤት ጎዳና ውስጥ ቢያሳልፍም በሁለተኛው ዙር የሀዋሳ ቆይታው ግን  በደጋፊዎቹ እየታገዘ በሰበሰባቸው ነጥቦች ምድቡን በበላይነት ማጠናቀቁን ተከትሎ በአሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ መሪነት ከ15 ዓመታት በኋላ ወደ ትልቁ የሀገሪቱ የሊግ ዕርከን ማደጉ ይታወሳል። የሊግ ተሳትፎውንም ለማድረግ በክረምቱ አስቀድሞ የአሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙን ኮንትራት በማራዘም የተጫዋቾችን ዝውውር ደግሞ በማስከተል ማከናወን የጀመረ ሲሆን በክለቡ ያሉ ወሳኝ ተጫዋቾችንም ኮንትራት በማደስ ወደ ገበያው ገብቷል። ክለቡ ከፕሪምየር ሊጉ አቤል ማሞ ፣ ኢዮብ ገብረማርያም ፣ ቻላቸው መንበሩ ፣ ሔኖክ ድልቢ ፣ አብስራ ሙሉጌታ ፣ ተመስገን ተስፋዬ ፣ ያሬድ ዳዊት እና ሀብታሙ ንጉሴን ሲያስፈርም ከከፍተኛ ሊጉ ደግሞ ሙሉቀን ታሪኩ ፣ ታምራት ስላስ ፣ አሸብር ውሮ እና አባቱ ጃርሶን ቀላቅሏል። ከሀገር ውጪ ደግሞ ዩጋንዳዊያኑን ግብ ጠባቂውን ሳይዲ ኬኒ እና አጥቂውን አላን ካይዋኔን እንዲሁም ከናይጄሪያ አማካዩ ሚካኤል ኔልሰንን የስብስቡ አካል አድርጓል። በቡድኑ ቆይታ የነበራቸውን ረዳት አሰልጣኞች ውላቸውን አድሶ ስብስቡን በተሟላ መልኩ በመያዝ ከነሐሴ 14 ጀምሮ በቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ከተማ በሚገኘው ኳሊቲ ሆቴል የቅድመ ውድድሩን ሲሠራ የነበረው ሻሸመኔ እንደ አዲስ ብቅ ያለበትን የሊግ ጉዞውን በነገው ዕለት ይጀምራል። በዝግጅት ምዕራፍ ወቅት ጥቂት የወዳጅነት ጨዋታዎችን በማድረግ ቀጥሎም በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር የገባው ክለቡ በምድብ ጨዋታዎች ወቅት ደካማ ቆይታን ያደረገ ቢሆንም በየጨዋታው የሚያሳየውን መልካም እንቅስቃሴ ባሉት ቀሪ ጊዜያት አጠናክሮ ከመጣ እና አሰልጣኙ ለመጫወት የሚያስቡትን የመስመር አጨዋወት እንቅስቃሴን ወጥ በሆነ መልኩ የሚያሳዩ ከሆነ በሊጉ ጥሩ ተፎካካሪ እንደሚሆን ይገመታል፣ ነገር ግን ቡድኑ ለሊጉ አዲስ ከመሆኑ አኳያ ባለፉት ዓመታት አዳጊ ክለቦች ላይ የሚታዩ ድክመቶች አብረውት የሚገኙ ከሆነ ግን የቡድኑ ረጅም ርቀት የመጓዙ ሂደት አዳጋች መሆኑ የማይቀር እንደሆነ መገመት አያዳግትም።


– በሊጉ ላይ ከዓመት ዓመት ጠጣር በሆነ አቀራረብ ለተጋጣሚዎች ፈተና ሲሆኑ ከምንመለከታቸው ክለቦች መካከል ወላይታ ድቻ አንዱ ስለ መሆኑ በድፍረት መናገር ይቻላል። በአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም አማካኝነት ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲመራ የነበረው ቡድኑ በአሰልጣኙ በተመራባቸው በእነኚህ ዓመታት ሁለት መልክን መያዝ ቢችልም በሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ግን የሚታማ አልነበረም። በ2014 ከነበረው አቋሙ በተወሰነ ሳስቶ ያለፈውን ዓመት ለማሳለፍ የተገደደው ቡድኑ በያዛቸው ወጣት ተጫዋቾች እየታገዘ በሰበሰባቸው 37 ነጥቦች ላለመውረድ ሲታገል ከርሞ በደረጃ ሰንጠረዡ 12ኛ ላይ ተቀምጦ ማጠናቀቅ ችሏል። ካሸነፋቸው እና ከተሸነፋቸው ጨዋታዎች የአቻ ውጤቶቹ የሚያመዝነው ቡድኑ የአሰልጣኝ ፀጋዬን ውል መጠናቀቅ ተከትሎ በክረምቱ  በሀድያ ሆሳዕና ጥሩ የውድድር ጊዜን ያሳለፉትን አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹን በመቅጠር እንዲሁም ተጨማሪ ሁለት ረዳት አሰልጣኞችን በማከል እና በቡድኑ ውስጥ የነበሩ ወሳኝ ተጫዋቾችን ውላቸውን በማራዘም ጅምራቸውን አድርገዋል። የአሰልጣኝ ቅጥርን ፣ የነባር ተጫዋቾችን ውልም ካደሱ በኋላ ፊታቸውን ወደ አዳዲስ ተጫዋቾች በማዞር በጥቂት ዝውውሮች ላይ ቡድኑ ራሱን አሳትፏል። ባዬ ገዛኸኝ ፣ አብነት ደምሴ ፣ ፀጋዬ ብርሃኑ ፣ ብዙዓየሁ ሰይፈ እና ፍፁም ግርማን የስብስቡ አካል ሲያደርግ በክረምቱ በሶዶ ከተደረገ የውስጥ ውድድር በአንደኛ ሊጉ ይሳተፉ የነበሩ ሦስት ተጫዋቾችን ጨምሮ ከታችኛው ቡድኑ ወደ አምስት የሚጠጉ ወጣት ተጫዋቾችን በማካተት በአዲሱ አሰልጣኝ መሪነት ከነሐሴ 10 ጀምሮ በክለቡ መቀመጫ ከተማ ሶዶ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ሲሠራ አሳልፏል። በቡድኑ ካሉ ጥቂት ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ውጪ በየዓመቱ ወጣቶችን ያማከለ የቡድን ግንባታ ላይ የሚያተኩረው ድቻ ዘንድሮም ያንን ባህል በማስቀጠል ለፕሪምየር ሊጉ ውድድር ዝግጅቱን አገባዷል። ካደረጋቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች በበለጠ  በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ላይ ብዙ ጨዋታዎች ያደረገው ክለቡ በውድድሩ ላይ ከተለመደው አጨዋወት ወጣ ባለ አቀራረብ የኳስ ንክኪዎች ላይ አዘውትሮ ያስተዋልን ሲሆን አሰልጣኝ ያሬድም ጥሩ ቡድን መገንባት መቻላቸውን ታዝበናል። ምን አልባትም በዚህ የአቋም መፈተሻ ውድድር ላይ የብዙዓየሁ እና አብነትን የመሐል ሜዳ ጥምረት ከቢኒያም ፍቅሬ ጋር በማቆራኘት ያደጉትን ስብጥር በፕሪምየር ሊጉ ላይ የሚደግሙ ከሆነ ከነገው የሻሸመኔ ጨዋታ አንዳች ነገርን ሊያገኙ የሚችሉበት መንገድ እንዳለ መናገር ይቻላል።

ሀምበሪቾ ከ ድሬዳዋ ከተማ

– በሌላኛው የሳምንቱ አራተኛ ጨዋታ አመሻሽ 12፡00 ላይ አዲስ አዳጊውን ሀምበሪቾ ዱራሜን ከ ድሬዳዋ ከተማ የሚያገናኘው ጨዋታ ትኩረትን ይስባል። ወደ ሀገሪቱ ትልቁ የሊግ ዕርከን ለማደግ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ብቅ ለማለት ሲሞክር የነበረው ሀምበሪቾ ዱራሜ በለስ ቀንቶት በሦስተኛው ዓመቱ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ በነገው ዕለት መሳተፉን ይጀምራል። አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞን በ2014 የውድድር ዘመን ወርሀ መጋቢት ላይ ከቀጠረ በኋላ በጥቅሉ እስከ ተጠናቀቀው ዓመት ድረስ ወደ 36 በሚሆኑ ጨዋታዎች ያልተሸነፈው ቡድኑ ይህንኑ ጥንካሬውን አስቀጥሎ 2015’ን በተደለደለበት የከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ በጠንካራ ተሳትፎው ገፍቶበት ከገላን ከተማ ጋር ትንቅንቅ ውስጥ ገብቶ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ያስመዘገባቸው ውጤቶች አግዘውት ለመጀመሪያ ጊዜ በፕሪምየር ሊጉ ላይ ለመታየት በቅቷል። ቡድኑ በክረምቱ ራሱን ለማጠናከር እንቅስቃሴዎችን የጀመረው በእጅጉ ዘግይቶ ነበር ማለት ይቻላል። ከታችኛው የሊግ ዕርከን ያሳደጉትን አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞን ጨምሮ ረዳቶቹንም ጭምር አስቀጥሎ  ወደ ዝውውሩ በመግባት ከከፍተኛ ሊጉ የኋላ ኋላ ደግሞ ከፕሪምየር ሊጉ በጥቅሉ ወደ 12 አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም በክለቡ የነበሩ ወሳኝ ተጫዋቾችም ውላቸው ተራዝሞላቸዋል። ቡድኑ በዝውውር ገበያው ከከፍተኛ ሊጉ ማናዬ ፋንቱ ፣ ንጋቱ ጎዴቦ ፣ አፍቅሮት ሰለሞን ፣ አብዱሰላም የሱፍ ፣ የኋላሸት ሰለሞን እና ደረጀ አለሙን ከፕሪምየር ሊጉ ደግሞ ብሩክ ቃልቦሬ ፣ ፀጋሰው ድማሙ ፣ አቤል ከበደ ፣ ኤፍሬም ዘካሪያስ ፣ ቴዎድሮስ በቀለን እንዲሁም የጋና ዜግነት ያለውን ግብ ጠባቂው ፓጆ ፓሎምን ወደ ስብስቡ አካቷል። ከፋይናንስ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከሌሎች የሊጉ ክለቦች አኳያ የቅድመ ውድድር ዝግጅት በመጀመሩ ረገድ የዘገየው ቡድኑ ከጳጉሜ 2 ጀምሮ ላለፉት 27 ቀናት ብቻ በሀዋሳ ከተማ ሀብል ሆቴል መቀመጫቸውን አድርገው ልምምዳቸውን ሲከውኑ የነበሩ ሲሆን በማስከተል ወደ አዳማ አምርተው ቀጥለዋል። በነበራቸው ዝግጅት ካደረጓቸው ጥቂት የወዳጅነት ጨዋታዎች ውጪም በየትኛውም የአቋም መፈተሻ ውድድሮች ላይ ሳይካፈሉ ነገ ድሬዳዋ ከተማን በሊጉ ‘ሀ’ ብለው ይገጥማሉ። በከፍተኛ ሊግ ውድድር ወቅት በጠንካራ አቋሙ ዓመቱን የቋጨው ሀምበሪቾ አሰልጣኙ በወቅቱ አዘውትረው ይጠቀሙበት  የነበረውን የጨዋታ መንገድ በተለይ በመስመሮች እና በተሻጋሪ ኳሶች ማጥቃቱን የሚያሳየን ከሆነ የመጀመሪያ ተሳትፎውን በሚያደርገው የነገ ጨዋታው አንድ የተለየ  ነገርን ሊያገኝ እንደሚችል መገመት ይቻላል። ነገር ግን ቡድኑ ከነበረበት የዝግጅት ጊዜ ማጠርም ሆነ የወዳጅነት ጨዋታዎችን በአማራጭነት አለማድረጉን ተከትሎ እንግዳ በሆነበት ፕሪምየር ሊግ ላይ አይናፋርነቱ ጎልቶ እንዳይመጣም ያሰጋል።

– በፕሪምየር ሊጉ ላይ በተከታታይ ስድስት ዓመታት በደረጃ ሰንጠረዡ የታችኛው ቦታ ላይ ከሚዳክሩ ክለቦች መካከል ድሬዳዋ ከተማን አለመጥራት አይቻልም። ቡድኑ በእነዚህ ዓመታት አጀማመሩን በስልነት ሲያደርግ ብናይም የኋላ ኋላ የሚታዩበት የውጤት ማሽቆልቆሎች አብረውት እየተጓዙ በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ተአምራዊ በሆኑ ቅፅበቶች ሊጉ ላይ ሲሰነብት ስንመለከት አሳልፈናል። የ2015 የሊግ ጉዞውን አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይን በመቅጠር የውድድር ዓመቱን ቢያጋምሱም አሰልጣኙ ከክለቡ ጋር በገቡት ውል መሠረት ውጤታማ መሆን አልቻሉም በሚል መነሻነት አሰልጣኙን በማንሳት በምትኩ አስራት አባተን በቦታው በመተካት ዓመቱን ለማጠናቀቅ ችለዋል። ቡድኑ የአሰልጣኝ ለውጥን ካደረገ በኋላ በጥቂት ጨዋታዎች ላይ መልካም የሚባሉ ውጤቶችን ቢያሳየንም ውድድሩ ወደ ሀዋሳ ካቀና በኋላ ባሉት ጨዋታዎች ላይ እየተንሸራተተ መጥቶ በድጋሚ ወደ አዳማ ውድድሩ ተመልሶ በተለይ በ29ኛው ሳምንት አርባምንጭ ከተማን እስኪያሸንፍ ድረስ የመውረድ ስጋት ውስጥ ሆኖ በመጨረሻም 10ኛ ደረጃ ላይ በ40 ነጥቦች ተቀምጦ ለከርሞው በሊጉ ላይ መቆየቱን አረጋግጦ እንደነበር ይታወቃል። ከወረደ በኋላ በድጋሚ በሊጉ ላይ ተመልሶ ለስምንተኛ ተከታታይ ዓመት ዘንድሮም በፕሪምየር ሊጉ ላይ የሚካፈለው የምስራቁ ተወካይ ድሬዳዋ ከተማ ከአሰልጣኝ አስራት አባተ ጋር ኮንትራት ስላለው አሰልጣኙም ቡድኑን እየመሩ እንዲቀጥሉ ካደረገ በኋላ ራሱን ወደ ማጠናከሩ በመግባት ወደ ስምንት የሚጠጉ አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም ውላቸው ያለቁ ተጫዋቾችም ውል ተራዝሟል። በወጥነት ሲያገለግል የነበረውን አጥቂው ቢኒያም ጌታቸውን ቡድኑ ቢያጣም እንደ ተመስገን ደረሰ ፣ ሔኖክ አንጃ ፣ ቴዎድሮስ ሀሙ ፣ ኤፍሬም አሻሞ እና ካርሎስ ዳምጠውን ከፕሪምየር ሊጉ ዳግማዊ አባይ ፣ ሀምዲ ቶፊክ እና ዘርዓይ ገብረሥላሴን ደግሞ ከከፍተኛ ሊጉ መቀላቀል የቻለ ሲሆን የአሰልጣኝ ቡድኑን ለማጠናከር ደግሞ  የቀድሞው የምድር ባቡር አሰልጣኝ እና የወጣት ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ የነበሩትን ዚያድ ሁሴንን የቴክኒክ ዳይሬክተር በማድረግ ወደ ዝግጅት ገብቶ ልምምዱን ሲሰራ ሰንብቷል። እንዳለፈው ዓመትም ዘንድሮ መቀመጫውን በሐሮማያ የኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በማድረግ ነሐሴ 10 ሲል ዝግጅት የጀመረው ቡድኑ በልምምዶቹ መሐል በሐረር አካባቢ ካሉ ቡድኖች ጋር ካደረጋቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች  በተጨማሪ ወደ ሀዋሳ አምርቶ በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ላይ ተሳትፎ አድርጎም ነበር። በውድድሩ ላይ ቡድኑ በምድብ ጨዋታዎች ላይ በሽግግር የጨዋታ ሒደት ለመጫወት ሲሞክር በጉልህ ብንመለከትም የኋላ መስመር ተሰላፊዎቹ ከነበራቸው ድክመት አንፃር ሁለት ጨዋታዎችን በተከታታይ ሲሸነፍ አስተውለናል። በአንፃሩ በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ወልቂጤን ሲያሸንፍ ይበልጥ ትኩረቱን ማጥቃት ላይ አድርጎ በተደራጀ መልኩ ሲያደርግ ይታይ የነበረውን እንቅስቃሴ በነገው የሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ከደገመ ነጥብን ይዞ ሊወጣ እንደሚችል ይጠበቃል።