ከፍተኛ ሊግ | ወሎ ኮምቦልቻ አዲስ አሰልጣኝ ሾሟል

የከፍተኛ ሊጉ ክለብ ወሎ ኮምቦልቻ የአዲስ አሰልጣኝ ቅጥር ፈፅሟል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ላይ ከሚሳተፉ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ወሎ ኮምቦልቻ የተጠናቀቀውን ዓመት በምድብ ‘ሀ’ ስር ተደልድሎ በዓመቱ ባስመዘገባቸው 28 ነጥቦች በደረጃ ሰንጠረዡ 9ኛ ላይ ተቀምጦ የቋጨ ሲሆን ዓምና ከነበረው ተሳትፎው በተሻለ መልኩ ዘንድሮ ተፎካካሪ ለመሆን በማሰብ የክለቡ ቦርድ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የአዲስ አሰልጣኝ ቅጥር በዛሬው ዕለት ስለ መፈፀሙ ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ የላከው መረጃ ይጠቁማል። ክለቡን በዋና አሰልጣኝነት እንዲመሩ የተሾሙት ደግሞ አሰልጣኝ ደረጀ በላይ ሆነዋል።

የቀድሞው የሰበታ ከተማ ፣ ጅማ አባቡና ፣ ኢትዮጵያ መድን ፣ ወልቂጤ ከተማ እና ሀላባ ከተማ አሰልጣኝ ደረጀ በተለይ በጅማ እና ወልቂጤ ቆይታቸው ቡድኖቹን ወደ ፕሪምየር ሊጉ በማሳደግ የሚታወቁ ሲሆን ያለፈውን ዓመት ወደ ቀድሞው ክለባቸው ይርጋጨፌ ቡና በመመለስ ካሳለፉ በኋላ ወደ ወሎ ኮምቦልቻ አምርተዋል።