ሪፖርት | ወላይታ ድቻ ሊጉን በድል ጀምሯል

ወላይታ ድቻ በፀጋዬ ብርሃኑ ብቸኛ ግብ ሻሸመኔ ከተማን በመርታት የውድድር ዓመቱን በድል ከፍቷል።

የሊጉ የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ የሆነው መርሐግብር ሻሸመኔ ከተማን ከወላይታ ድቻ ያገናኘ ነበር። ቡድኖቹ በክረምቱ ካስፈረሟቸው ተጫዋቾች መካከል የሊጉ እንግዳ ቡድን ሻሸመኔ ስምንት በአንፃሩ ወላይታ ድቻ አራቱን በቋሚ አሰላለፋቸው አካተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ፈጠን ባሉ እንቅስቃሴዎች ጅምሩን ያደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ከሚታወቁበት ቀጥተኛ አጨዋወት ኳስን በመያዝ ሲጫወቱ የታዩት ወላይታ ድቻዎች አንፃራዊ ብልጫን በተጋጣሚያቸው ላይ ወስደው ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል። ቡድኑ ኳስን በተቃራኒ የሜዳ ክፍል ላይ በሚይዝበት ወቅት በግራ በኩል ወደ ተሰለፈው ፀጋዬ ብርሃኑ አመዝኖ ለማጥቃት ቢሞክርም የተጫዋቹ የውሳኔ ልልነት በቀላሉ ይገኙ የነበሩ ዕድሎች እንዲባክኑ አድርጓል።

16ኛ ደቂቃ ላይ አማካዩ ብዙዓየሁ ሰይፈ ከመሐል ሜዳ የሰነጠቀለትን ኳስ ፀጋዬ ብርሃኑ አግኝቶት ከግራ ወደ ውስጥ ሲያሳልፍ ነፃ ቦታ ላይ የነበረው አብነት ደርሶት በቀጥታ ወደ ጎል መቶ ኳሷ አቅጣጫዋን ቀይራ ወጥታለች። ወደ ጨዋታ ውስጥ ለመግባት ዘለግ ያሉ ደቂቃዎች የወሰደባቸው ሻሸመኔዎች በሽግግር የጨዋታ መንገድ ኳሶችን ወደ መስመር በማስጠጋት አልፎም ደግሞ  በተሻጋሪ ለመጫወት ቢጥሩም መጨረሻ ላይ ኳሱ የሚደርሳቸው ተጫዋቾች ይታይባቸው ከነበረው የውሳኔ ድክመት አኳያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራን ለማድረግ አልቻሉም። በብዙ ረገድ ከነበሩ ወጥ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች ውጪ በሙከራዎች ያልታጀበው ቀዳሚ አጋማሽም ግብ ሳይቆጠርበት ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ጨዋታው ከዕረፍት እንደተመለሰ ግብ ያስመለከተን በአንድ ደቂቃ ውስጥ ነበር። 48ኛው ደቂቃ ላይ ኳስን ያስጀመሩት ድቻዎች ከራሳቸው ሜዳ ይዘው የወጡትን ኳስ ብዙዓየሁ ሰይፈ ወደ ግራ ሲያሻግር ፀጋዬ ብርሀኑ አንድ ጊዜ ብቻ ገፋ በማድረግ ዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ ሳይድ ኬኒ መረብ ላይ አሳርፎ ድቻን መሪ አድርጓል።

 

ጎል ካስተናገዱ በኋላ በተለይ ከቆሙ ኳሶች መነሻቸው አድርገው ወደ ማጥቃት ተሳትፎው የገቡት ሻሸመኔዎች አከታትለው ሁለት አጋጣሚዎችን ፈጥረዋል። 53ኛው ደቂቃ በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት አሸብር ውሮ ሲያሻማ ተከላካዩ ናትናኤል ናሲሮ በራሱ ላይ ለማስቆጠር ተቃርቦ ኳሷ በንክኪ ወደ ውጪ ልትወጣ ችላለች። ከአንድ ደቂቃ መልስ በሌላ ሙከራቸው ኢዮብ ገብረማርያም ከማዕዘን አሻምቶ አሸናፊ ጥሩነህ በግንባር ገጭቶ ኳሷ የግቡን ቋሚ ብረት ታካ ወጥታለች።

በጨዋታው የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ጫናን ፈጥረው ለመጫወት ጥረት ወደ ማድረጉ የገቡት ወላይታ ድቻዎች የእንቅስቃሴ የበላይነቱን ቢወስዱም የሚፈጥሯቸውን ዕድሎች በአንፃሩ በማስቆጠሩ ረገድ ውስንነቶች ታይቶባቸዋል። ቢኒያም ፍቅሬ ከመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የደረሰውን ኳስ ከግቡ ፊት ለፊት ሆኖ ቢያገኘውም ብረት የመለሰበት ብዙዓየሁ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ አግዳሚውን ታካ ከወጣች በኋላ ባሉት ቀሪ ደቂቃዎች ተጨማሪ ግብ ሳንመለከት ጨዋታው በወላይታ ድቻ 1ለ0 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሻሸመኔ ከተማው አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ በጨዋታው የጠበቁትን እንቅስቃሴ አለማድረጋቸውን ጠቅሰው ይህ ሊገጥማቸው እንደሚችል ቀድመው ገምተው እንደነበር ጠቁመዋል። እንደ መጀመሪያ ጨዋታ ነጥብ ላለመጣል ጥረት አድርገው እንዳልተሳካም በንግግራቸው ገልፀዋል። የወላይታ ድቻው አቻቸው ያሬድ ገመቹ በበኩላቸው ጥሩ ጨዋታ ነበር ካሉ በኋላ ማጥቃቱም ሆነ መከላከሉም ላይ ጥሩ ስለመሆናቸው ጠቁመው የተገኙ የግብ ዕድሎችን ከመጨረስ አኳያ የብስለት መጉደል መኖሩን ነገር ግን የዛሬው ውጤት ለቀጣይ የስነ ልቦና ጥንካሬን እንደሚፈጥር አልሸሸጉም።