ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማ በመጀመርያው ሳምንት ድል አድርጓል

የአሰልጣኝ አስራት አባተ ውጤታማ ቅያሪ ብርቱካናማዎቹ ከመመራት ተነስተው ሀምበሪቾን በመርታት ሙሉ ሦስት ነጥብ እንዲያሳኩ አስችሏል።

ሁለት የተለያየ መልክ በነበረው ጨዋታ በኃይል አጨዋወቶች እና በበርካታ ሙከራዎች ታጅቦ የተካሄደ ነበር። አዲስ አዳጊዎቹ ሙሉ ብልጫ በታየበት የመጀመርያው አጋማሽ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች ተጭነው በመጫወት በርካታ የግብ ዕድሎችን የፈጠሩበት ነበር። ከኳስ ውጭ እጅግ የተቀናጀ አደረጃጀት የነበራቸው ሀምበሪቾዎች ተጋጣሚያቸው ኳሱን እንዳይቆጣጠር ከማድረግም ባለፈ በርካታ ዕድሎች ፈጥረዋል።

ከእነዚህም ዳግም በቀለ አሻግሮት የኋላሸት ፍቃዱ ከተከላካዮች ጀርባ ሮጦ ከፍ አድርጎ የሞከራት እና ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ በጥሩ መንገድ የመለሳት ኳስ ትጠቀሳለች።  የኋላ ኋላም የኳስ ቁጥጥር ብልጫም መውሰድ የቻሉት ሀምበሪቾዎች በረከት ወንድሙ በተሰለፈበት የግራ መስመር በርካታ ዕድሎችን ፈጥረዋል። ምንያምር ከመስመር አሻምቶት ሳጥን ውስጥ የነበረው የኋላሸት በግሩም መንገድ መትቶት የድሬዳዋው ተከላካይ እያሱ ከግቡ መስመር የመለሰው እና አፍቅሮት ሰለሞን ሙከራ አድርጎ መረቡን ታኮ የወጣበት ኳስ ይጠቀሳል። የሀምበሪቾ ዋነኛ የማጥቃት መሳርያ የነበረው በረከት ወንድሙ ከመስመር አሻምቷት ዳንኤል የመለሳት ኳስም ሌላ ክለቡን ቀዳሚ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች።

በመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ዕቅዳቸውን ለመተግበር የተቸገሩት ድሬዳዋዎች በአጋማሹ የፈጠሩት የጠራ የግብ ዕድል አንድ ብቻ ነበር። ካርሎስ ዳምጠው ከዳዊት እስጢፋኖስ የተቀበለውን ኳስ መትቶት ተከላካዮች ተደርበው ወደ ውጭ ያወጡት ሙከራም ብቸኛው የጠራ የግብ ዕድል ነበር።

በጨዋታው ጫና ፈጥረው በርካታ የግብ ዕድሎችን የፈጠሩት ሀምበሪቾዎች በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ባደረገው የኋላሸት አማካኝነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ተጫዋቹ ከርቀት ተመትታ የግቡን አግዳሚ ገጭታ የተመለሰች ኳስ አግኝቶ ነበር ግሩም ግብ ያስቆጠረው።

ከመጀመርያው አጋማሽ ለየት ያለ እንቅስቃሴ በታየበት የሁለተኛ አጋማሽ ተጫዋቾች ቀይረው አጋማሹን የጀመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ተሻሽለው የቀረቡበት በአንፃሩ ሀምበሪቾዎች ከመጀመርያው አጋማሽ ተቀዛቅዘው የታዩበት ነበር።

በ52ኛው ደቂቃም ተቀይሮ የገባው ኤልያስ አሕመድ በተከላካይ ስህተት ያገኘውን ኳስ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ተጫዋቾች ቀይረው ካስገቡ በኋላ የተሻለ ለማጥቃት የቻሉት ብርቱካናማዎቹ ቀይረው ያስገቧቸው ተጫዋቾች በፈጠሩት ጫና 64ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን የሚመሩበት ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ኤፍሬም አሻሞ ከኤልያስ የተቀበለውን እና በጥሩ መንገድ ተጫዋቾች ቀንሶ ያሻገረውን ኳስ በግቡ አፋፍ የነበረው ቻርለስ ሙሴጌ አግኝቶ በማስቆጠር ብርቱካናማዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ በሙከራዎች ያልታጀበ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። ብርቱካናማዎቹ ጥንቃቄ መርጠው ውጤታማ ባደረጋቸው የመስመር አጨዋወት የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ሲሞክሩ በአካል ብቃት ወርደው የታዩት ሀምበሪቾዎች ደግሞ ከሳጥን ውጭ ግብ ለማግኝት ጥረት አድርገዋል።

በሀምበሪቾ በኩል በፍቃዱ ያደረጋቸው ሁለት ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። ተጫዋቹ ከርቀት አክርሮ መቶት ግብ ጠባቂው የያዘበት እና አቤል አሻግሮት አብዱለጢፍ በደምብ ያላፀዳው ኳስ አግኝቶ መቶት ወደ ውጭ የወጣው ኳስ ይጠቀሳሉ። በድሬዳዋ በኩልም ኤልያስ አሕመድ ከርቀት አክርሮ መቶት ግብ ጠባቂው የመለሰበት ኳስ ይጠቀሳል።

ጨዋታው በዚህ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማዎች በመጀመርያው ሳምንት ሙሉ ሦስት ነጥብ ሲያሳኩ በጨዋታው በርካታ ዕድሎች ያመከኑት አዲስ አዳጊዎቹ ሀምበሪቾዎች ደግሞ ከሌሎች አዳጊዎች በተለየ በሊጉ የመጀመርያ ጨዋታ ግብ ማስቆጠር ችለዋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ቀድመው አስተያየታቸውን የሰጡት አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ በጨዋታው በርካታ ዕድሎች እንዳመከኑ ጠቅሰው በቅድመ ውድድር ብዙ ጨዋታ ካለማድረጋቸው አንፃር ውጤቱ ብዙም አስከፊ እንዳልሆነ ተናግረዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም በሁለተኛው አጋማሽ አጥቅተው ለመጫወት ያወጡት ዕቅድ በተፈለገው መንገድ እንዳልተተገበረ እና ባልተጠበቀ መንገድ ያስተናገዱት ግብ የተጫዋቾቹን መንፈስ እንደረበሸው ጠቅሰው በቀጣይም እነዚህን ችግሮች ቀርፈው እንደሚቀርቡ ገልፀዋል። ድል የቀናቸው የድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝ አስራት አባተ በበኩላቸው ጨዋታውን እንደጠበቁት ከባድ እንደነበር ገልጸው ተጋጣሚያቸው ፈታኝ እንደነበር ተናግረዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም ቡድናቸው በመጀመርያው አጋማሽ ተረጋግቶ የመጫወት ችግር እንደታየበት እና በሁለተኛው አጋማሽ ችግራቸውን መቅረፋቸው ለውጤቱ መገኘት ትልቅ አስተዋፅዖ እንደነበረው አመላክተዋል።