ሪፖርት | ሦስተኛው የጨዋታ ቀን በጀመረበት የጎል ፌሽታ ተጠናቋል

ብርቱ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ መቻል ሁለት ጊዜ አቻ መሆን ችሎ የነበረው ሀዲያ ሆሳዕናን 3-2 ረቷል።

በጥሩ ፉክክር የጀመረው ጨዋታ በቶሎ ግብ ያስተናገደ ሆኗል። 5ኛው ደቂቃ ላይ ዮሐንስ መንግሥቱ ከመሀል ያስጀመረው ጥቃት በሀዲያዎች ቢቋረጥም ሽመልስ በቀለ አግኝቶ ያሳለፈለትን ከነዓን ማርክነህ በቀኝ በኩል ሳጥን ውስጥ በመግባት ጎል አድርጎታል። ከግቡ በኋላ መቻሎች በኳስ ቁጥጥር የሆሳዕናን አቻ ለመሆን ያለመ ፈጠን ያለ ጥቃት በማርገብ ወደ ማጥቃት ለመሸጋገር ሲሞክሩ ተስተውሏል።

ሆኖም ነብሮቹ በቶሎ ወደ ጎል ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት በመቻሎች ስህተት ታጅቦ 13ኛው ደቂቃ ላይ አቻ አድርጓቸዋል። በዚህም መቻሎች በአግባቡ ማራቅ ያልቻሉትን ጥቃት ብሩክ ማርቆስ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ በመምታት አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ አድርጓል።

ሀዲያዎች ከአቻነቱ በኋላም ወደ ቀኝ ያመዘነ የማጥቃት ጥረታቸው ቀጥሎ 19ኛው ደቂቃ ላይ ሰመረ ሀፍተይ ከመስመር ላይ የመለሰለትን ዘካሪያስ ፍቅሬ አክርሮ ሞክሮ በግቡ ቋሚ ተመልሶበታል። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ መቻሎች በተቃራኒ ሳጥን የሰላ የማጥቃት እንቅስቃሴ አድርገው ዳግም ወደ መሪነት ሊሸጋገሩ ነበር። በዚህም ምንይሉ ወንድሙ ሽመልስ በቀለ የደረሰውን ድንቅ ኳስ መረብ ላይ አሳረፈ ተብሎ ሲጠበቅ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ጨዋታው 28ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሽመልስ በቀለ ረጅም ርቀት ኳስ በመግፋት እና ሦስት ተጫዋቾችን በማለፍ የፈጠረውን የግብ ዕድል ምንይሉ ደርሶት በአንድ ንክኪ ሁለተኛ ጎል አድርጎታል። በንፅፅር ቀዝቀዝ ያለው ቀሪው የአጋማሹ ክፍል የቡድኖቹ የማጥቃት ጥረቶች በተቃራኒ አቅጣጫ እየከሸፉ የተቋጨ ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ መቻሎች ከፍ ባለ የኳስ ቁጥጥር ክፍተቶችን ለማግኘት የታተሩበት አጀማመር ነበረው። ሆኖም ሽመልስ በቀለ 57ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ሙከራ እስኪያደርግ ድረስ ነብሮቹ የተጋጣሚያቸውን እንቅስቃሴ ተቆጣጥረው ቆይተዋል። ይልቁኑም በቀጣዩ ደቂቃ ሪችሞንድ ኦዶንጎ በረከት ደስታ በስህተት ወደ ኋላ የመለሰውን ነፃ ኳስ አግኝቶ በአግባቡ ሳይጠቀምበት ቀርትቷል።

ጨዋታው በመቻል የኳስ ቁጥጥር ቢቀጥልም ነብሮቹ በተደጋጋሚ ለጎል መቅረብ ችለው ነበር። ጥሩ ሲንቀሳቀስ የቆየው በየነ ባንጃ 64ኛው ደቂቃ ላይ በግብ ጠባቂው አናት ላይ ልኮት ወደ ውጪ የወጣው ፣ 65ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳ የተሻማ ቅጣት ምት ተጨርፎ በግቡ አግዳሚ በተመለሰበት እንዲሁም 75ኛው ደቂቃ ላይ በየነ ባንጃ ከሳጥን ውስጥ ሞክሮት ወደ ውጪ በወጣበት ቅፅበት ሀዲያዎች አቻ ሊሆኑ ተቃርበው ነበር። ሆኖም ተከታታይ ጥረታቸው 77ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቶ ሪችሞንድ ኦዶንጎ ላይ በተሰራ ጥፋት ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ብሩክ ማርቆስ ሁለተኛ ጎል አድርጎታል።

ተጋጣሚዎቹ ቅያሪዎችን በማድረግ በታደሰ ጉልበት ጥሩ የማጥቃት ሂደቶችን እያሳዩ በቀጠለው ጨዋታ የፍፁም ቅጣት ምቱ ተራ የመቻል ሆኗል። ምንይሉ ወንድሙ ሽመልስ በቀለ ላይ በተሰራ ጥፋት ያገኘውን ይህን አጋጣሚ 87ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አድርጎት መቻል ለሦስተኛ ጊዜ መሪ ሆኗል። በቀሪ ደቂቃዎችም መቻሎች ይህንን መሪነት አሳልፈው ሳይሰጡ ጨዋታውን በ3-2 ድል መጨረስ ችለዋል።

በአሰልጣኞች አስተያየት ከፈጠሩት የግብ ዕድል አንፃር ማሸነፍ ይገባቸው እንደደነበር ያነሱት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ጥሩ ጨዋታ እንደነበር ጠቁመው የፈጠሯቸውን የመከላከል ስህተቶች በማብራራት የተሰጠባቸው የፍፁም ቅጣት ምት እንዳልተዋጠላቸው የሚጠቁም አስተያየት ሰጥተዋል። በተመሳሳይ ጨዋታው ከጎሎች ብዛት አንፃር ጥሩ እንደነበር ያነሱት አሰልጣኝ ገብረክረስቶስ ቢራራም የቡድናቸውን የመከላከል ችግር ያነሱ ሲሆን “ሽመልስ ካለ ጎል አለ” ሲሉ የጨዋታው ኮከብ የነበረው አማካያቸውን አሞካሽተዋል።