መረጃዎች | 12ኛ የጨዋታ ቀን

የሊጉ ሁለተኛ ሳምንት መቋጫ የሆኑት የነገ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል።

ባህር ዳር ከተማ ከ መቻል

ባህር ዳር ከተማ እና መቻልን የሚያገናኘው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ 09:00 ላይ ይጀምራል።

ከባለፈው የውድድር ዓመት በእጅጉ የሚቀራረብ አጨዋወት ይዘው በመድን 3-2 የተሸነፉት የጣና ሞገዶቹ ዘንድሮም ይበልጥ በሽግግሮች ላይ የተመሰረተ የሚመስል አቀራረብ ይዘው ዓመቱን ጀምረዋል። ከመድን ጋር ሁለት ግቦች አስቆጥረው ሽንፈት ባስተናገዱበት ጨዋታ በተጠቀሰው አቀራረብ ለመጫወት የሞከሩት ባህር ዳሮች በአማካይ ክፍሉ ላይ ፍሬው ሰለሞን የመሰለ ለቀጥተኛ አጨዋወትም የሚመች ፈጣሪ ተጫዋች መያዛቸው ቡድኑ ተገማች እንዳይሆን ይረዳዋል። አማካዩ በተሸነፉበት ጨዋታ ለሀብታሙ ታደሰ የፈጠራቸው ዕድሎችም ለዚህ ማሳያ ናቸው። ሆኖም ቡድኑ የግብ ዕድሎችን በመጠቀም ረገድ ያሉበትን ክፍተቶች ማስተካከል ቀዳሚ የቤት ሥራው መሆን አለበት። አሰልጣኝ ደግአረግም ይህንን የቡድኑ ችግር በድህረ ጨዋታ ላይ አንስተውታል። በነገው ጨዋታም ይህንን ችግር ከመቅረፍ በተጨማሪ ሦስት ግቦችን ያስተናገደው የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ላይ ማስተካከያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ሀድያን በገጠሙበት ጨዋታ ኳስ ለመቆጣጠር የሚሞክር ቡድን ያስመለከቱን መቻሎች ሰፊ የማጥቃት አማራጭ ያለው የጥቃት መንገዱ ተገማች ያልሆነ አቀራረብ አላቸው። በተጋጣሚያቸው ሀድያ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ያስቆጠሯቸው ሦስት ግቦችም የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ጥራት ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ነበሩ። አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በነገው ጨዋታም ተመሳሳይ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ቢጠበቅም ባለፈው ጨዋታ በቀላሉ ግብ ዕድሎች የተፈጠሩበትን ቡድናቸው ሚዛን ማስጠበቅ ግድ ይላቸዋል። ሀድያዎች በጨዋታው ወደ ግብነት ያልቀየሯቸው በርካታ የግብ ዕድሎችም የመቻል የመከላከል አደረጃጀት ድክመት ማሳያ ናቸው።

ባህርዳር ከተማዎች ከቡድኑ ጋር ከሌለው ዱሬሳ ሹቢሳ ውጭ በጉዳትም ሆነ በቅጣትም የሚያጡት ተጫዋች የለም። በመቻል በኩል በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ካለውና በቅርቡ ልምምድ ከጀመረው ፍፁም ዓለሙ ውጭ ሙሉ ቡድን ለጨዋታው ዝግጁ ነው።

ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም በስድስት አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን አስር ግቦች ያስመዘገቡት መቻሎች ሦስት ጊዜ ፣ ሰባት ግቦች ያስቆጠሩት የጣና ሞገዶቹ ደግሞ አንድ ጊዜ ድል ሲያደርጉ የተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ። ተጋጣሚዎቹ አምና ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች በድምሩ 10 ግቦች መቆጠራቸውም አይዘነጋም።

ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ሲመራው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ በረዳት ዳኝነት እንዲሁም ኤፍሬም ደበሌ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።


ሻሸመኔ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

ወላይታ ድቻን ገጥመው አንድ ለባዶ በተሸነፉበት ጨዋታ የውድድር ዓመቱን በሽንፈት የጀመሩት አዲስ አዳጊዎቹ ሻሸመኔዎች የመጀመርያ ነጥብ ማስመዝገብን አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ። በጨዋታው መስመሩን ለጥጠው በማጥቃት እና በቀጥተኛ ኳሶች ለመጫወት የሞከሩት ሻሸመኔዎች በአጨዋወቱ በርካታ የግብ ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም። ቡድኑ ከቆሙ ኳሶች ካደረጋቸው ዕድሎች ውጭ በክፍት ጨዋታ ንፁህ ዕድሎች ለመፍጠር ሲቸገር ነበር። በነገው ጨዋታም ከባለፈው በተሻለ የግብ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችላቸው አቀራረብ ይዘው መቅረብ ይኖርባቸዋል።

ሀዋሳ ከተማዎች ዐፄዎቹን ገጥመው አቻ በተለያዩበት ጨዋታ በአጨዋወትም በአደራደርም ሁለት የተለያየ ቡድን አሳይተውናል። አራት ተከላካዮች አሰልፈው በጀመሩት የመጀመርያው አጋማሽ ለስህተቶች የተጋለጠና ለተጋጣሚ በርካታ የግብ ዕድሎች የፈጠረ አጨዋወት ነበራቸው። ምንም እንኳ የፋሲል ግቦች ከቆሙ ኳሶች የተቆጠሩ ቢሆኑም በክፍት ጨዋታ እንቅስቃሴ የተፈጠሩት ዕድሎችም ጥቂት አልነበሩም። በሁለተኛው አጋማሽ ግን 3-5-2 የሚመስልና በአጥቂ ክፍል ላይ የተሰለፉትን ዓሊ ሱሌማን እና ሙጂብ ቃሲም መሰረት ያደረገ አጨዋወት ተከትለው ወደ ጨዋታው የተመለሱበትን ግቦችም ማስቆጠር ችለዋል። በጨዋታውም ከተጋጣሚ ተከላካይ ክፍል ጀርባ የተፈጠረውን ክፍት ቦታ የተጠቀሙበት መንገድ የሚደነቅ ነበር።

አሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉ በነገው ጨዋታ የሚከተሉትን አጨዋወት ለመገመት አዳጋች ቢሆንም በሁለተኛው አጋማሽ ውጤታማ ያደረጋቸውን የተጫዋቾች ምርጫ ወደ ሜዳ ይዘው የሚገቡበት ዕድል ይኖራል ተብሎ ይገመታል። ከዚህ በተጨማሪ የቻርለስ ሉክዋጎ ለጨዋታው ዝግጁ መሆን ለሀይቆቹ መልካም ዜና ነው።

ሻሸመኔ ከተማ በጉዳትም ሆነ በቅጣት በነገው ጨዋታ የሚያጣው ተጫዋች የለም። በሀዋሳ ከተማ በኩል ባለፈው ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው በረከት ሳሙኤል ይህንን ጨዋታ በቅጣት አይሰለፍም። በተቃራኒው ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ እና አማካዩ ሚካኤል ኦቶ የወረቀት ጉዳዮችን በማጠናቀቃቸው ለዚህ ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።

ይህ ጨዋታ ለመሀል ዳኛ መስፍን ዳኜ የመጀመሪያው የሊግ ጨዋታ ሲሆን ለዓለም ዋሲሁን እና ሸረፈዲን አልፈኪ በረዳት ዳኝነት ፣ እያሡ ፈንቴ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተሰይመዋል።