የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ቅጥር ምን ሊሆን ይችላል ?

የሰሞኑ ወቅታዊ ጉዳይ እየሆነ ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ቅጥር ዙርያ ፌዴሬሽኑ ምን አስቧል ?

ባሳለፍነው ዓመት ከዋልያዎቹ ዋና ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር በስምምነት የተለያየው ፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዳሬክተሩን ዳንኤል ገብረማርያምን በጊዛዊ አሰልጣኝነት በመሾም ብሔራዊ ቡድኑን ሲመራ መቆየቱ ይታወሳል። የቴክኒክ ዳሬክተሩ በጊዛዊነት የተረከቡትን ሥራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ብሔራዊ ቡድኑ ያለፉትን አንድ ወራት አሰልጣኝ አልባ ሆኖ መቆየት ችሏል።

ፌዴሬሽኑ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ለመቅጠር ሂደቶች ላይ መሆኑን እና አሰልጣኝ ገብረመድህንን በዋና አሰልጣኝነት ለመቅጠር ፍላጎት መኖሩን በዚህም አሰልጣኙን እና የኢትዮጵያ መድን አመራሮችን ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ፌዴሬሽኑ ማናገሩን ሆኖም ክለቡ ውል ያላቸው በመሆኑ ከአሰልጣኙ አስፈላጊነት አንፃር አሳልፎ እንደማይሰጥ መገለፁን መዘገባችን ይታወቃል።

አሁን ሶከር ኢትዮጵያ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ በፌዴሬሽኑ እና በኢትዮጵያ መድን እንዲሁም አሰልጣኝ ገብረመድህን መካከል ውይይት ተደርጓል። ይህውም አሰልጣኝ ገብረመድህን የውል ዘመናቸው እስኪጠናቀቅ ድረስ ክለቡን የማሰልጠን ስራቸውን እየሰሩ በተጨማሪ ብሔራዊ ቡድኑን ደርበው እንዲሰሩ የማስማማት ስራ እየተሰራ ሲሆን አሰልጣኙ የውል ዘመናቸው በዚህ ዓመት መጨረሻ ሲጠናቀቅ ሙሉ ለሙሉ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ተረክበው እንዲሰሩ ለማድረግ መታሰቡን አረጋግጠናል።

በዚህም መነሻነት በቅርቡ በዚህ ጉዳይ በሦስቱም ወገን መካከል ስምምነት ከተደረሰ አሰልጣኙ በይፋ ቡድኑን በመረከብ በቀጣይ ህዳር ወር ለሚኖረው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።