ፕሪምየር ሊግ | ቁጥራዊ መረጃዎች

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለት የጨዋታ ሳምንታት በተካሄዱት 16 ጨዋታዎች የተመዘገቡ ቁጥራዊ መረጃዎችን እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2016 የውድድር ዓመት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታድየም መካሄድ ከጀመረ ሁለት ሳምንታት ተቆጥረዋል። በተካሄዱት አስራ ስድስት ጨዋታዎች 40 ግቦች ሲቆጠሩ ፤ ከነዚህ ውስጥ 26ቱ ግቦች በመጀመርያ ሳምንት ፤ የተቀሩት 14 ግቦች ደግሞ በሁለተኛው ሳምንት ከመረብ ጋር ተዋህደዋል። በአጠቃላይ ከተቆጠሩት ግቦች ውስጥ ሁለት በራስ ላይ የተመዘገቡ ግቦች ይገኙባቸዋል፤ የወልቂጤው ዳንኤል ደምሱና የሀዲያው ከድር ኩሉባሊም ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።

በአጠቃላይ በሁለቱም የጨዋታ ሳምንታት ከተቆጠሩ 40 ግቦች አምስቱ በፍፁም ቅጣት ምት የተገኙ ሲሆኑ አምስቱም በሁለት ጨዋታዎች ብቻ የተሰጡ ናቸው። ሦስቱ መቻል እና ሀዲያ ሆሳዕና ባገናኘው ጨዋታ፤ ሁለቱ ደግሞ ባህርዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ መድንን ባገናኘው ጨዋታ የተሰጡ ሆነዋል።

እስካሁን ድረስ ከተካሄዱት ጨዋታዎች 12ቱ በመሸናነፍ ሲጠናቀቁ የተቀሩት 4 ደግሞ በአቻ ውጤት ያለቁ ናቸው። አዳማ ከተማን እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ያገናኘው ጨዋታ ብቸኛው ባዶ ለባዶ የተጠናቀቀ ሲሆን ሦስት ለሦስት የተጠናቀቀው እና ስድስት ግቦች የተስተናገዱበት የሀዋሳ ከተማ እና ፋሲል ጨዋታ ደግሞ በርካታ ግቦች የተቆጠሩበት ጨዋታ ሆኗል። በሁለተኛው ሳምንትም ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህርዳር ከተማ ብቻ ከአንድ ግብ በላይ አስቆጥረው ጨዋታቸውን ማሸነፍ የቻሉ ክለቦች ናቸው።

በርካታ ግቦች ያስቆጠረ ቡድን

የአምና ሻምፒዮኖቹ ፈረሰኞች በርካታ ግቦች በማስቆጠር በቀዳሚነት ተቀምጠዋል። ወልቂጤ ላይ አራት ግቦች አስቆጥረው ሊጉን ጀምረው በሁለተኛው ሳምንት ሀምበሪቾ ላይ ሁለት ግቦች ማስቆጠር የቻሉት ፈረሰኞቹ በሁለቱም ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ከመረብ ጋር አዋህደዋል። ክለቡ በአማካይ በጨዋታ ሦስት ግቦች ማስቆጠር ሲችል በሁለተኛነት ከተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በሁለት ግቦች ልቀው በአንደኝነት ተቀምጠዋል።

በርካታ ግቦች የተቆጠረበት ቡድን

በመጀመርያው ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ አራት ግቦች ፤ አቻ በተለያዩበት ሁለተኛ ጨዋታ ደግሞ አንድ ግብ ያስተናገዱት ወልቂጤዎች አምስት ግቦች በማስተናገድ በርካታ ግቦች የተቆጠረባቸው ሆነዋል። ከተቆጠረባቸው አምስት ግቦችም አንዱ በራስ ላይ የተቆጠረ ግብ ነበር።

ግብ ያላስተናገዱ ቡድኖች

ባካሄዷቸው ሁለት ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገዱ ሦስት ክለቦች ናቸው። ሲዳማ ቡናና ድሬዳዋ ከተማን በተመሳሳይ አንድ ለባዶ ያሸነፉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በሁለቱ ጨዋታዎች ግብ አልተቆጠረባቸውም። በሊጉ መክፈቻ ጨዋታ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ባዶ ለቦዶ ተለያይተው በሁለተኛው ሳምንት ወላይታ ድቻን አንድ ለባዶ ያሸነፉት አዳማ ከተማዎች በተመሳሳይ መረባቸውን አላስደፈሩም። ሦስተኛው ግብ ያላተናገደ ቡድን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው። አዲስ አዳጊዎቹ አዳማ ከተማና ሀዲያ ሆሳዕናን ገጥመው ምንም ግብ አላስተናገዱም።

ሦስቱ ክለቦች በመከላከሉ ረገድ በጎ ቁጥሮች ቢያስመዘግቡም ያስቆጠሩት የግብ መጠን ግን አናሳ ነው። አዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ180 ደቂቃዎች በየፊናቸው አንድ አንድ ግቦች አስቆጥረዋል። ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው ከሁለቱ ክለቦች በአንድ የግብ መጠን ከፍ ብለው ሁለት ግቦች ማስቆጠር ችለዋል።

ግብ ያላስቆጠረ ቡድን

አዲስ አዳጊዎቹ ሻሸመኔ ከተማዎች ከወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር አልቻሉም ፤ በሊጉም ኳስና መረብ ያላገናኙ ብቸኛ ክለብ ሆነዋል። ቡድኑ ምንም እንኳ ግብ ማስቆጠር ቢሳነውም ግብ ባለማስተናገድ ረገድ ግን ጥሩ ጎን አለው። አንድ ግብ ብቻ ካስተናገዱት ወላይታ ድቻዎች ቀጥለው ጥቂት ግብ በማስተናገድ ከሌሎች ክለቦች ጋር በጋራ በሁለተኛነት ተቀምጠዋል።

የዲስፕሊን ቁጥሮች

እስካሁን በተካሄዱት ጨዋታዎች 52 የቡድን አባላት የማስጠንቀቅያ ካርድ ተመዞባቸዋል። የሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾች ዘጠኝ ካርዶች በመመልከት ቀዳሚ ሲሆኑ የሀምበሪቾ ዱራሜ እና ኢትዮጵያ መድን ተጫዋቾች በአምስት ካርዶች ይከተላሉ። ፍሬዘር ካሳ፣ ብሩክ ቃልቦሬ፣ ሙጂብ ቃሲም እና አዲሱ ተስፋዬ ደግሞ በሁለቱም ጨዋታዎች በተከታታይ ማስጠንቀቂያ ካርድ የተመለከቱ ተጫዋቾች ናቸው። የሀዋሳ ከተማው በረከት ሳሙኤል እና ሙሉቀን አዲሱም በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጡ ተጫዋቾች ሆነዋል።