የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | 2ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሣምንት ጨዋታዎች ላይ በመመስረት ተከታዩን ምርጥ ቡድን ሰርተናል።

አሰላለፍ : 4-3-3

ግብ ጠባቂ

ፋሲል ገብረሚካኤል- ቅዱስ ጊዮርጊስ

የፈረሠኞቹ አዲስ ፈራሚ የሆነው ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን በመጀመርያ አሰላለፍ በመግባት ከቡድኑ ጋር በፍጥነት በመላመድ ከፍ ያለ ግልጋሎት እየሰጠ ይገኛል። በዚህ ሳምንት አዲስ አዳጊውን ሀምበሪቾን በረቱበት ጨዋታ የተደረጉ ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን በተደጋጋሚ ከማዳኑ ባሻገር የበረከት ወንድሙን የፍጹም ቅጣት ምት በድንቅ ቅልጥፍና መመለስ በመቻሉ በምርጥ ስብስባችን ልናካትተው ችለናል።

ተከላካዮች

ፍፁም ፍትሕዓለው – ባህር ዳር ከተማ

የባህር ዳር ከተማ ግራ መስመር ተጫዋቹ ፍራኦል መንግሥቱ በጉዳት አለመኖሩን ተከትሎ ከተለምዷዊ የመሐል ተከላካይነት ቦታው ወደ ግራ መስመር ተጫዋች እንዲሆን የገባው የክለቡ የታዳጊ ፍሬ የሆነው ፍጹም መስመሩን በተረጋጋ ሁኔታ በመቆጣጠር በመከላከሉ በኩል ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አድርጓል ። ለቡድኑ ውጤት ማማር የራሱን አስተዋፅኦ በማድረጉም በቦታው ልንመርጠው ችለናል።

ያሬድ ባየህ – ባህር ዳር ከተማ

የጣና ሞገዶቹ የውድድር ዓመቱን የመጀመርያው ድላቸውን ባስመዘገቡበት ጨዋታ ያሬድ ባየህ የመቻልን የማጥቃት እንቅስቃሴ በንቃት በመከላከል ፣ አካባቢውን በመቆጣጠር ፣  በአንድ ለአንድ ግንኙነት ኳሶችን ከመንጠቁ በተጨማሪ በጥሩ የራስ መተማመን የቡድኑን አጋሮችን  በማገዝ በኩል የነበረው ድርሻ በጉልህ የሚታይ ነበር።

ወልደአማኑኤል ጌቱ – ኢትዮጵያ ቡና

አዲሱ የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ኒኮላ ካቫዞቪች ወደ ቡድኑ ከመጡ በኋላ ከፍተኛ መሻሻል እያሳየ የሚገኘው የኋላ ደጀኑ ወልደአማኑኤል ጌቱ ቡናማዎቹ በተከታታይ ላሳኳቸው ድሎች የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። በብዙዎች ዘንድ አድናቆት እየተቸረው የሚገኘው ወልደ አማኑኤል የድሬዳዋን የአጥቂ ክፍል የጠሩ የግብ ዕድሎችን እንዳይፈጥሩ ከማድረጉ ባለፈ ወደ ፊት ኳሶችን ይዞ በመሄድ የጎል ዕድሎች ለመፍጠር ያደርገው የነበረው ጥረት ተመራጭ አድርጎታል።

አብዱልከሪም መሐመድ- ኢትዮጵያ መድን

በቀኝ ተከላካይነት ብዙ አማራጭ ባልነበረበት 2ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ መድን ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ሲወጣ የእርሱ እንቅስቃሴ የተሻለ ነበር። አብዱልከሪም የሚያደርጋቸው ቀጥተኛ ሩጫዎች እና ወደ ሳጥን የሚያደርሳቸው ኳሶች ደግሞ ለቡድኑ የቀኝ መስመር የበላይነት ትልቁን ድርሻ ይወስዱ ስለነበሩ በምርጥ አስራ አንድ ሊካተት ችሏል።

አማካዮች

ናትናኤል ዘለቀ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ፈረሠኞቹ አዲስ አዳጊውን ሀምበሪቾ ዱራሜን ሲረቱ የአማካዩ ሚና የጎላ ነበር። በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ አንድ ለአንድ የተገናኘባቸውን አጋጣሚዎች ሙሉ በሙሉ በማሸነፍ የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ ለተከላካዮች ስኬታማ ሽፋን ሲሰጥ አቤል ያለው ላስቆጠራት የመጀመሪያ ግብም አመቻችቶ ላቀበለው አማኑኤል ኤርቦ ግሩም የዓየር ላይ ኳስ በማቀበል ቁልፍ መነሻ ነበር።

ዊልያም ሰለሞን – አዳማ ከተማ

ባለፈው የውድድር ዓመት ሁለተኛ ዙር ውድድር ላይ በርካታ ጨዋታዎች ላይ መሳተፍ ያልቻለው ዊልያም አዳማ ወላይታ ድቻን በረታበት ጨዋታ ግን በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ ቢገባም ድንቅ በሆነ የግል ብቃቱ ታግዞ ቡድኑ መሃል ሜዳው ላይ የተወሰደበትን ብልጫ በማስመለስ እና የማጥቃት እንቅስቃሴውን በማነቃቃት አዳማዎች ላሳኩት ድል ወሳኝ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ኤልያስ ለገሰ – አዳማ ከተማ

አዳማ ከተማ ወላይታ ድቻ ላይ የ 1-0 ድል ሲቀዳጅ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያደረገው እና እንደ ዊልያም ሁሉ በቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ሚና የነበረው ኤልያስ ከረፍት የለሽ እንቅስቃሴው ባሻገር ቡድኑ ያሸነፈበትን ግብም ግሩም በሆነ የተረጋጋ አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል።

አጥቂዎች

አማኑኤል ኤርቦ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በያዝነው የውድድር ዓመት ፈረሠኞቹን የተቀላቀለው የመስመር አጥቂው በቀኙ የሜዳ ክፍል ላይ ከኳስ ጋር ማራኪ እንቅስቃሴ ማድረግ ሲችል ከእንቅስቃሴው ባሻገር በርካታ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር አቤል ያለው ላስቆጠረው ግብ አመቻችቶ ማቀበል ሲችል ሁለተኛውን ግብ ደግሞ ራሱ በጥሩ ቦታ አያያዝ ማስቆጠር መቻሉ ከውጤታማነቱም አንጻር ያለ ተቀናቃኝ በቦታው ተመራጭ ሆኗል።

እዮብ ዓለማየሁ – ሀዋሳ ከተማ

በሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ኃይቆቹ አዲስ አዳጊውን ሻሸመኔ ከተማን 1-0 ሲረቱ አሰልጣኝ ዘርዓይ በሚሰጡት ቦታ ሁሉ እየተቀያየረ በሁሉም ቦታዎች ጠንካራ እንቅስቃሴ ማድረን የቻለው እዮብ ከሳጥን ውጪ ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን ለድል ሲያበቃ ይበልጥ ውጤታማ በነበረበት የግራ የመስመር አጥቂ ቦታ ላይ በምርጥ 11 ስብሰባችን ውስጥ ሊካተት ችሏል።

አቤል ያለው – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በአማካይ 1.75 ግቦች ብቻ በተቆጠሩበት የጨዋታ ሳምንት የአጥቂ መስመር ተጫዋቾች ጎልተው ያልወጡበት ነበር። ሆኖም ግን በአንጻራዊነት አቤል የተሻለ ብልጫ ወስዷል። ጊዮርጊሶች ሀምበሪቾን 2-1 በረቱበት ጨዋታ በግል ብቃቱ ታግዞ ለተመልካች ማራኪ እንቅስቃሴ ያደረገው ፈጣኑ አጥቂ የቡድኑን የመጀመሪያ ግብም በግንባሩ በመግጨት መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል።

አሰልጣኝ – ይታገሡ እንዳለ

አዳማ ከተማ ወላይታ ድቻን 1-0 ሲያሸንፍ ቡድኑ በመጀመሪያው አጋማሽ ከራሱ የሜዳ ክፍል ለመውጣት ቢቸገርም ትዕግሥት በተሞላበት ተደጋጋሚ ኳስ ከኋላ መስርቶ የመጫወት ሂደት በመቀጠል በሁለተኛው አጋማሽም እጅግ ስኬታማ የሆኑ ቅያሪዎችን በማድረግ እና በያዙት የጨዋታ መንገድ ቡድናቸውን ለውጤት ያበቁት አሠልጣኝ ይታገሡ የሁለተኛውን ሳምንት ምርጥ ቡድናችንን እንዲመሩ መርጠናቸዋል።

ተጠባባቂዎች

ፍሬው ጌታሁን – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
በፍቃዱ ዓለማየሁ – ኢትዮጵያ ቡና
ፍሬዘር ካሳ – ባህር ዳር ከተማ
አሚር ሙደሲር – ኢትዮጵያ መድን
አበባየሁ ሀጂሶ – ወላይታ ድቻ
ከነዓን ማርክነህ – መቻል
ፍሬው ሰለሞን – ባህርዳር ከተማ
ሀቢብ ከማል – ኢትዮጵያ መድን