ኢትዮ ኤሌክትሪክ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን የስብስቡ አካል አድርጓል

ባሳለፍነው ዓመት የፕሪምየር ሊጉ ተሳታፊ የነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለከፍተኛ ሊግ ተሳትፎው በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የገዘፈ ስም ካላቸው ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ተመልሶ በ2015 መሳተፍ ቢችልም በመጣበት ዓመት በሦስት የተለያዩ አሰልጣኞች ሲመራ ከቆየ በኋላ በመጨረሻም ወደ ከፍተኛ ሊጉ ለመውረድ መገደዱ ይታወሳል። ክለቡ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ከሀገሪቱ ትልቁ የሊግ ዕርከን መውረዱ ከተረጋገጠ በኋላ የቀድሞው የሐረር ቢራ ፣ ዳሽን ቢራ ፣ ስሑል ሽረ እና ድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝ የነበሩትን አሰልጣኝ ሳምሶን አየለን መቅጠሩ የሚታወስ ሲሆን ቡድኑም ወደ ፕሪምየር ሊጉ በድጋሚ ይመለስ ዘንድ በከፍተኛ ሊግ በሚኖረው ቆይታ በአዲሱ አሰልጣኝ መሪነት ወደ 20 የሚጠጉ አዳዲስ ተጫዋቾችን ስለ ማስፈረሙ ለሶከር ኢትዮጵያ ክለቡ በላከው መረጃ አመላክቷል።

ክለቡን የተቀላቀሉ ተጫዋቾችን ስንመለከት የቀድሞው የባህርዳር ከተማ ፣ ሰበታ እና ድሬዳዋ አማካይ ዳንኤል ኃይሉ ፣ የአዲስ አበባ ፣ ሲዳማ ቡና እና ቤንች ማጂ ቡና የመስመር አጥቂ እሱባለው ሙሉጌታ ፣ የመቻል ፣ ሰበታ እና ወልድያ ተከላካይ ሙሉቀን ደሳለኝ ፣ የደቡብ ፖሊስ ፣ ነቀምት እና ንግድ ባንክ ተከላካይ ጌቱ ባፋ ፣ የቀድሞው የፋሲል ፣ ድሬዳዋ እና ወልድያ አማካይ መጣባቸው ሙሉ ፣ በኢትዮጵያ ቡና ፣ ገላን እና መድን የተጫወተው አማካዩ ቢኒያም ካሳሁን ፣ በመቐለ እና አምና በደብረብርሃን ያሳለፈው አጥቂው ያሬድ ብርሀኑ ፣ በፍቃዱ እዝቅኤል አማካይ ከጋሞ ጨንቻ ፣ ሚኪያስ ካሳሁን ተከላካይ ከድሬዳዋ ከተማ ፣ በፋሲል ከነማ እና በወልድያ ቆይታ የነበረው ግብ ጠባቂው ቴዎድሮስ ጌትነት ፣ እንዳለ ዘውገ አማካይ ከንግድ ባንክ ፣ በአዳማ ፣ ወልዋል ፣ መቻል እና ለገጣፎ ለገዳዲ የምናውቀው ግብ ጠባቂው በሽር ደሊል ፣ መሳይ ሠለሞን አጥቂ ከሰንዳፋ ፣ ኤፍሬም ታምራት አጥቂ ከቤንች ማጂ ፣ ጌታሰጠኝ ሸዋ አማካይ ከንግድ ባንክ ፣ አቡበከር ከማል ተከላካይ ከቤንች ማጂ ፣ የቀድሞው የክለቡ አጥቂ አቤል ሀብታሙን ከንግድ ባንክ ፣ አንዋር ኑሩ አማካይ ከቡራዩ ፣ በጋሻው ክንዴ ከወልድያ እና ዮሴፍ አሰፋ ተከላካይ ከኮልፌ የክለቡ አዲስ ፈራሚዎች ሆነዋል።

ክለቡ ከአዳዲሶቹ በተጨማሪ የያሬድ የማነ እና ናትናኤል ሰለሞን ውል ሲያራዝም ቡድኑን ባሳለፍነው ዓመት አጋማሽ የተቀላቀሉ ሁለት የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች ማለትም ግብ ጠባቂው ካክፖ ሼረፈዲን እና አጥቂው ጎሜዝ ፖውል በከፍተኛ ሊጉ የትኛውም የውጪ ዝጋ ተጫዋች የማይጫወት ቢሆንም በክለቡ ቀሪ የ6 ወራት ስላላቸው ቡድኑን እንደሚያገለግሉም ተሰምቷል።