መረጃዎች| 9ኛ የጨዋታ ቀን

የሦስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀምራሉ። ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል።

ኢትዮጵያ መድን ከ ወላይታ ድቻ

በሁለተኛው ሳምንት ድል ያላስመዘገቡትን ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘው የሳምንቱ የመጀመርያ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ከሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦች ሰብስበው በሦስተኛ ደረጃነት የተቀመጡት መድኖች ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች በአመዛኙ በፈጣን ሽግግሮች ለማጥቃት የሚሞክሩ ሲሆን አራት ግቦች ማስቆጠራቸው እና የነገው ተጋጣሚያቸው አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደ ቡድን እንደመሆኑ በፊት መስመር ላይ የሚጠብቃቸው ፈተና ቀላል ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም። በነገው ጨዋታ ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ ይሰጣሉ ተብለው የማይገመቱት አሰልጣኝ ገብረመድኅን በነገው ጨዋታቸው ለወትሮ አስቸጋሪ የሆነውን በሽግግሮች ላይ የተመሰረተ አጨዋወት መተግበራቸው አይቀሬ ነው። ሆኖም ከባለፈው የውድድር ዓመት ጀምሮ በቡድናቸው ላይ ለሚስተዋለው የመከላከል ችግር መፍትሄ ማበጀት ይጠበቅባቸዋል።


በተደረጉት ሁለት ጨዋታዎች አንድ ግብ አስቆጥረው አንድ ግብ ያስተናገዱት ወላይታ ድቻዎች በሁለተኛው ሳምንት በአዳማ ከደረሰባቸው ሽንፈት ለማገገም ኢትዮጵያ መድንን ይገጥማሉ። ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ኳስን ለመቆጣጠር ጥረት የሚያደርግ ቡድን ያስመለከቱን አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ እንደ አቅርቦቱ ዕድሎችን ወደ ግብነት የመቀየር ትልቅ ክፍተት የሚታይበትን የአጥቂ ክፍላቸው ስልነት ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በርካታ ዕድሎች የፈጠረው ቡድን በ180 ደቂቃዎች ያስቆጠረው የግብ መጠን አናሳ መሆኑ የችግሩን ትልቅነት ማሳያ ነው። ከዚ በተጨማሪ እስካሁን ድረስ አንድ ግብ ብቻ በማስተናገድ ጥሩ ቁጥር ያስመዘገበው የቡድኑ የተከላካይ ክፍል ነገ የሚገጥመው ግቦች ለማስቆጠር የማይሰንፈው መድን እንደመሆኑ ጥንካሬውን ለማስቀጠል ትልቅ ፈተና ይጠብቀዋል።

ኢትዮጵያ መድን እና ወላይታ ድቻ ከዚህ ቀደም አራት ጊዜ ተገናኝተዋል። እኩል አንድ አንድ ጊዜ ተሸናንፈው በሁለቱ አቻ ተለያይተዋል። በአራቱ ግንኙነትም ድቻ አምስት መድን ደግሞ ሦስት ግብ አስቆጥረዋል።

በወላይታ ድቻ በኩል ተከላካዮቹ አናጋው ባደግ እና መልካሙ ቦጋለ ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው። በኢትዮጵያ መድን በኩል መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ሲዳማ ቡና ከ ፋሲል ከነማ

በአዲሱ የውድድር ዓመት ድል ያላስመዘገቡ ሁለት ክለቦች የሚያገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ማግኘት ከሚገባቸው ስድስት ነጥቦች አንድ ነጥብ ብቻ ያሳኩት ሲዳማ ቡናዎች በተመሳሳይ በውድድር ዓመቱ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘት ካልቻሉት ፋሲል ከነማዎች ይገጥማሉ። በጉዳት ምክንያት በተመናመነ የአጥቂ አማራጭ ጨዋታቸውን ለማድረግ የተገደዱት ሲዳማዎች አቻ በተለያዩበት የመጨረሻ ጨዋታ ንፁህ የግብ ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም። በተለይም በአማካዩ እና በአጥቂ ክፍሉ ላይ የነበረው የላላ መናበብ እና የዋና አጥቂዎቹ መጎዳት ቡድኑ የግብ ዕድሎች እንዳይፈጥር አድርጎታል። አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በነገው ጨዋታም መሰል ችግሮች ቀርፈው የግብ ዕድሎች መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።


በሁለት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦች ሰብስበው በአስራ አንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፋሲል  ከነማዎች የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ለማግኘት አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ። በመጨረሻው መድንን በገጠሙበት ጨዋታ በአንፃራዊነት የተሻለ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም እንቅስቃሴው ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማግኘት በቂ አልነበረም ፤ ለዚ እንደምክንያት የሚነሳው ደግሞ ቡድኑ በሁለቱም ጨዋታዎች የተስተዋለበት ሙሉ ዘጠና ደቂቃ በወጥነት የመጫወት ችግር ነው።

ቡድኑ ምንም እንኳ በሁለቱም ጨዋታዎች በድምር  አራት ግቦች ማስቆጠር ቢችልም ከሚፈጥራቸው ዕድሎች፣ በአጥቂ ክፍሉ ላይ ካለው የተጫዋቾች ጥራት እና ከግብ መገኛ አማራጮች ብዛት አንፃር የግብ መጠኑ አናሳ ነው። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከዚ በተጨማሪ አሁንም ከስህተቶች ያልፀዳው የተከላካይ ክፍላቸው ላይ  ማስተካከያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው አሥራ ሁለት ጨዋታዎች አንድም በአቻ የተጠናቀቀ ጨዋታ የሌለ ሲሆን አሥራ ዘጠኝ ግቦች ያሉት ፋሲል ከነማ ለሰባት አሥራ አራት ግቦች ያሉት ሲዳማ ቡና ደግሞ ለአምስት ጊዜያት አሸንፈዋል።

በሲዳማ ቡና በኩል አጥቂዎቹ ይገዙ ቦጋለ እና ፊሊፕ አጃህ ጉዳት ምክንያት አይሰለፉም፤ ባለፈው ጨዋታ በቀይ ካርድ የወጣው ሙሉቀን አዲሱ በበኩለ በቅጣት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይሳተፍም። በፋሲል ከነማ በኩል መረጃዎች ለማጣራት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።