ሪፖርት | ወላይታ ድቻ ወደ ድል ተመልሷል

በሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ወላይታ ድቻ በአብነት ደምሴ ድንቅ ግብ ኢትዮጵያ መድንን 1-0 መርታት ችሏል።

ቀን 9 ሰዓት ላይ በሳምንቱ ቀዳሚ መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ መድን እና ወላይታ ድቻ ሲገናኙ ሁለቱም ቡድኖች ከሁለተኛ ሳምንት ጨዋታቸው በተመሳሳይ የአንድ ተጫዋች ለውጥ አድርገዋል። መድኖች አዲስ ተስፋዬን አሳርፈው ከሀዋሳ ጋር በስምምነት ተለያይቶ ክለቡን ከቀናት በፊት በተቀላቀለው ሰይድ ሀሰን ሲተኩ ወላይታ ድቻዎች ከአዳማው ጨዋታ አንፃር ዘላለም አባተን አስቀምጠው ባዬ ገዛኸኝን በመተካት ለጨዋታው ቀርበዋል።

ጨዋታው በሴኮንዶች ውስጥ በወላይታ ድቻው ቢኒያም ፍቅሩ ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ ተደርጎበት በሁለቱም በኩል ባለ የጋለ የጨዋታ ስሜት ጅማሮውን ሲያደርግ በሁለቱም በኩል ፈጣን የማጥቃት ሽግግሮችን እያስመለከተ ቀጥሏል። ሆኖም 11ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ መድኖች ዋነኛ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው መነሻ የሆነውን የመስመር አጥቂውን ሀቢብ ከማልን ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት በአቡበከር ወንድሙ ቀይረው ለማስወጣት ተገደዋል።

ከአጋማሹ ሩብ ደቂቃዎች በኋላ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ በኩል ብልጫውን የወሰዱት ድቻዎች 14ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን የተሻለ የመጀመሪያ ሙከራ አድርገዋል። ፍፁም ግርማ በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ፀጋዬ ብርሃኑ በግራ እግሩ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መልሶበታል።


ጨዋታው 21ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ በጦና ንቦቹ አማካኝነት ግብ ተቆጥሮበታል። ቢኒያም ፍቅሩ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ባዬ ገዛኸኝ አረጋግቶ ወደኋላ በመመለስ ለአብነት ደምሴ ሲያቀብል አብነትም ከሳጥን ውጪ በአስደናቂ ሁኔታ አክርሮ የመታው ኳስ የግብ ጠባቂውን አቡበከር ኑራ እጅ ጥሶ መረቡ ላይ አርፏል።

ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ይዘው ለመውጣት የሚሞክሩትን ኳስ ባልተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ውጤታማ ለማድረግ የተቸገሩት መድኖች 34ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። ቢኒያም ፍቅሩ ከቀኝ መስመር ባሻገለት ኳስ ንጹህ የማግባት ዕድል ያገኘው ፀጋዬ ብርሃኑ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ 10 ደቂቃዎች ውስጥ የጨዋታውን ሚዛን በመቆጣጠር ወደፊት ተጭነው የተጫወቱት ኢትዮጵያ መድኖች 41ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን ለግብ የቀረበ ሙከራቸውን አድርገዋል። ወገኔ ገዛኸኝ ከአቡበከር ወንድሙ በተቀበለው ኳስ ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ መልሶበታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ግን ሁለት ሙከራዎች ተደርገውበታል። በቅድሚያም 52ኛው ደቂቃ ላይ በመድኖች በኩል ብሩክ ሙሉጌታ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያሬድ ዳርዛ ኳሱ ዓየር ላይ እንዳለ ከፍ አድርጎ በመምታት ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ሲወጣበት በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ የወላይታ ድቻው አበባየሁ ሀጂሶ ከቀኙ የሜዳ ክፍል ከሳጥን አጠገብ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል።


የአቻነት ግብ ለማስቆጠር በተረጋጋ የኳስ ቅብብል መታተራቸውን የቀጠሉት ኢትዮጵያ መድኖች 57ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። ወገኔ ገዛኸኝ ከያሬድ ዳርዛ በተቀበለው ኳስ ከሳጥን አጠገብ ያደረገውን ግሩም ሙከራ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ በጥሩ ቅልጥፍና አግዶበታል።

በመጀመሪያ አጋማሽ ከነበራቸው የማጥቃት እንቅስቃሴ በመጠኑ እየተቀዛቀዙ የሄዱት ወላይታ ድቻዎች 72ኛው ደቂቃ ላይ በአጋማሹ የተሻለውን ለግብ የቀረበ ሙከራቸውን አድርገዋል። ባዬ ገዛኸኝ ወደ ግራው የሜዳ ክፍል ካጋደለ ቦታ ላይ በተገኘው የቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።


በኢትዮጵያ መድን በኩል ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ኦሊሴማ ቺኔዱ 76ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ወደ ግብ ያሻገረው ኳስም የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶበታል። ሆኖም ከዚህ ሙከራ በኋላ ብርቱ ፉክክር በተደረገባቸው የመጨረሻ ደቂቃዎች በማጥቃቱ እንቅስቃሴ የተሻለ ብልጫ የነበራቸው የጦና ንቦቹ 86ኛው ደቂቃ ላይም መሪነታቸውን የሚያጠናክሩበት ወርቃማ ዕድል ፈጥረው ነበር። ብዙዓየሁ ሠይፈ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ቢኒያም ፍቅሩ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ በግሩም ቅልጥፍና አግዶበታል። ይህም የጨዋታው የመጨረሻ ዒላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው በወላይታ ድቻ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።