የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ መድን 0-1 ወላይታ ድቻ

“በፍላጎት ብቻ በልጠውናል ፣ መሸነፋችን አይበዛብንም” አሰልጣኝ ገብረመድህን ሐይሌ

“ብዙ ሩጫ እና ፍትጊያ እንደሚጠብቀን እናውቅ ነበር ፣ በጠበቅነው ደረጃ ነው ያገኘናቸው ” አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ

ወላይታ ድቻ የሊጉ ሁለተኛ ድሉን በአብነት ደምሴ ማራኪ ጎል ኢትዮጵያ መድንን 1ለ0 መርታት ከቻለበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኞቹ ጋር ቆይታ አድርጋለች።

አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ – ወላይታ ድቻ

ስለ ጨዋታው እና ተጋጣሚያቸው ስለነበረው አቀራረብ..

“ጠንካራ ፉክክር የታየበት ጨዋታ ነበር ፣ ጥሩ ነው ለእኛ። ተመሳሳይ ነው የአጨዋወት ዘይቤያችን በዕድሜም ተመጣጣኝ ወጣት የበዛበት ቡድን ነው። ብዙ ሩጫ እና ፍትጊያ እንደሚጠብቀን እናውቅ ነበር ፣ በጠበቅነው ደረጃ ነው ያገኘናቸው ከባድ ነበር።

ከአዳማ ጋር ከነበረው ጨዋታ አንፃር ስለ ተሻሻሉ ነገሮቻቸው…

“ዛሬ ጎል ማስቆጠር ችለናል ፣ ባለፈው ጨዋታ ትንሽ ብስለት ይጎድላቸዋል። የእኛ ልጆች የተጋጣሚያችን ጎል ጋር ሲደርሱ ትንሽ መረጋጋት እና ቆም ብሎ ማሰብ ማስተዋል ይጎላቸዋል ያም ከዕድሜ ጋር የሚመጣ ነበር ነው።”

ስለ ዛሬው ጨዋታ ጠንካራ ጎኖቻቸው…

“እንደ ቡድን ነው እኛ የምንጫወተው እና ሁሉም ቦታ ጠንካራ ነበር ፣ ተከላካዩም ጎል አላስተናገደም ፣ ግብ ጠባቂያችን እንደዚሁ ጠንካራ ነው ፣ አማካያችንም ጥሩ ስለሆነ ነው። የጠራ የጎል ሙከራን ዕድል እንኳን መፍጠር ያልቻለው ተጋጣሚያችን ጥብቅ ስለነበር እንደ ቡድን በጋራ ስለተጫወትን ሁሉም ዲፓርትመንት ላይ ጥሩ ነበርን እንደ ቡድን።”

ስለ አብነት ደምሴ አስደናቂ ጎል…

“አብነት አምናም ካቻምናም በርካታ ጎሎችን ያገባል ፣ እንደዚህ አይነት ከርቀት የሚመታቸው ኳሶች በጣም ግሩም ግሩም የሆኑ ኳሶች ናቸው። በጣም ድንቅ ጎል ነው ያገባው ተደንቄበታለሁ።”


አሰልጣኝ ገብረመድህን ሐይሌ – ኢትዮጵያ መድን

ስለ ጨዋታው…

“ጠንካራ ጉልበት ያለው የበዛበትም ጨዋታ ነው። በጣም ጠንካራ ሆነው ቀርበዋል ወላይታ ድቻ ፣ ያለፉትን ሁለት ያደረግነው ጨዋታ ጠንካራ ስለነበረ ከእዛ መነሻነት በጣም ጠንክረው ነው የመጡት እኛ ደግሞ በዛው ልክ ወርደን ነው የመጣነው ፣ ይሄ የስነ ልቦና ጫና ነው ይሄ ግን መሻሻል እንዳለበት ነው ፣ አሁን ተጫዋቾቻችን ወደ አሸናፊነት እንዲመለሱ ማድረግ ነው በጊዜ መሆኑ በጣም ጥሩ ነው ግን ምንጊዜም ቢሆን እንደዚህ አይነት ነገሮች አሸናፊነት ስሜትን በየጊዜው አሸናፊ አሸናፊ እየሆንክ መሄድ አለብህ መርካት የለብህም ፣ በአንድ እና ሁለት ጨዋታ ፣ በፍላጎት ብቻ በልጠውናል መሸነፋችን አይበዛብንም።”

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሐቢብ ከማል መጎዳቱ በእንቅስቃሴ ላይ ስለፈጠረው ተፅዕኖ…

“አዎ በጊዜ ነው ይሄ ምንም የማይታበይ ሀቅ ነው። ከጅምሩ እንደዚህ አይነት ለውጥ ስታደርግ ብዙ ነገሮች ናቸው የሚያስቸግሩት እናም ፈጣጠነ በአላስፈላጊ ሰዓት ነው የቀየርነው ፣ ሁለተኛ ያሰብነውን ስራ ለመስራትም አስቸጋሪ ነበር እና ምንም ጥርጥር የለውም።”

በቡድኑ ውስጥ ጉዳት ስለገጠማቸው አብዱልከሪም ፣ ተካልኝ እና አዲሱን በተመለከተ…

“ተፅዕኖው ቀላል አይባልም። ቀደም ብዬ እንዳልኩት በጣም ሐይል የበዛበት ጨዋታ የነበረው ፣ ወደፊት ደግሞ እንደዚህ አይነት ዛሬ የተጎዱብን በሙሉ ለቀጣይ አገግመው እንዲመጡ ደግሞ ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን ግን ተፅዕኖው ቀላል አይባልም።”