ሪፖርት | ፋሲል ከነማ ወሳኝ ድል ተቀዳጅቷል

በምሽቱ ተጠባቂ ጨዋታ ዐፄዎቹ ጊት ጋትኩት በራሱ መረብ ላይ ባስቆጠራት ግብ ሲዳማ ቡናን 1-0 በመርታት የመጀመሪያ ድላቸውን አሳክተዋል።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ ተጠባቂው የሲዳማ ቡና እና የፋሲል ከነማ ጨዋታ ሲደረግ በአቻ ውጤቶች ጨዋታቸውን አጠናቀው ለዛሬው ጨዋታ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ካለፈው የጨዋታ አቀራረባቸው ውስጥ በተመሳሳይ በሦስት ተጫዋቾች ላይ ቅያሪን አድርገዋል። ፋሲሎች እዮብ ማቲያስ ፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ይሁን እንዳሻውን አሳርፈው ዮናታን ፍሰሀ ፣ ቃልኪዳን ዘላለም እና ናትናኤል ገብረጊዮርጊስን ሲያስገቡ በሲዳማ ቡና በኩል በዛብህ መለዮ ፣ እንዳለ ከበደ እና ቡልቻ ሹራ አርፈው ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና አቤኔዘር አስፋው ተተክተው ገብተዋል።

ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች ሲዳማዎች በፈጣን ቀጥተኛ ኳሶች ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ለመውጣት ሲሞክሩ ፋሲሎች በአንጻሩ በርካታ ስኬታማ ቅብብሎችን በማድረግ እና የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። ሆኖም 10ኛው ደቂቃ ላይ በሲዳማ ቡና በኩል ማይክል ኪፖሩል በፋሲል ከነማ በኩል ደግሞ ሱራፌል ዳኛቸው ከሳጥን አጠገብ ሙከራ አድርገው ሁለቱንም ግብ ጠባቂዎቹ በቀላሉ ይዘዋቸዋል።

በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ዐፄዎቹ 19ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን ለመምራት እጅግ ተቃርበው ነበር። በፈጣን ሩጫ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ የደረሰው ቃልኪዳን ዘላለም ጥሩ ሙከራ አድርጎ የግቡ የግራ ቋሚ መልሶበታል። በሴኮንዶች ልዩነትም ጌታነህ ከበደ ሳጥን ውስጥ ያደረገውን ሙከራ የመሃል ተከላካዩ ደስታ ደሙ ተደርቦ አምክኖበታል።

አልፎ አልፎ ፋሲሎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሰው የሚያደርጉትን ቅብብል ስህተት በመጠቀም በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ የግብ ዕድል ለመፍጠር የሚሞክሩት ሲዳማዎች ጨዋታው ወደ ዕረፍት ሊያመራ በተጨመሩ የባከኑ ደቂቃዎች ውስጥ ግብ የሚያስቆጥሩበት ወርቃማ አጋጣሚ አግኝተው ነበር። ከሲዳማ ቡና የግብ ክልል በረጅሙ የተሻማውን ኳስ የፋሲል ተከላካዮች ግብ ጠባቂው ከጀርባ ይይዘዋል ብለው በመዘናጋት የተውትን ኳስ በጥሩ ሩጫ ያገኘው ማይክል ኪፖሩል ከማቀበል አማራጭ ጋር ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ በሚደረገው ብርቱ ፉክክር ጨዋታው በመጠኑ ተሻሽሎ ሲቀጥል የአጋማሹ የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራም 53ኛው ደቂቃ በሲዳማዎች አማካኝነት ተደርጓል። አበባየሁ ዮሐንስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኬ መልሶበታል።

ፋሲል ከነማዎች በተለይም በቀኙ የማጥቂያ መስመራቸው ተደጋጋሚ ፈጣን የማጥቃት ሸግግሮች ወደ ሳጥን ቢደርሱም ንጹህ የግብ ዕድል ለመፍጠርም ተቸግረው ተቸግረዋል። ሆኖም 68ኛው ደቂቃ ላይ ግን ጨዋታውን መምራት የሚችሉበት ዕድል አግኝተው ነበር።ጌታነህ ከበደ ቃልኪዳን ዘላለም በግሩም ዕይታ ሰንጥቆ ባቀበለው ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ መልሶበት የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

መጠነኛ ፉክክር እየተደረገበት የቀጠለው ጨዋታ እየተቀዛቀዘ ሄዶ በመጨረሻ 10 ደቂቃዎች ግን ድጋሚ ተጋግሎ ቀጥሏል። 80ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ከመሃል በተሰነጠቀለት ኳስ ከሳጥን አጠገብ በድጋሚ ጥሩ የግብ ዕድል ቢያገኝም በዘገየ ውሳኔ ሳይጠቀምበት ሲቀር በአንድ ደቂቃ ልዩነት በሲዳማ ቡና በኩል ተቀይሮ የገባው ይስሃቅ ካኖ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ጥሩ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኪ መልሶበታል።

ጨዋታው በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል ተብሎ ሲጠበቅ ግን 88ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲሎች የማሸነፊያ ግብ አስቆጥረዋል። ተቀይሮ የገባው ኤልያስ ማሞ ያገኘውን የቅጣት ምት ወደ ሳጥን ሲያሻግረው የሲዳማው የመሃል ተከላካይ ጊት ጋትኩት በግንባሩ ገጭቶ ለማስወጣት ሲሞክር ተጨርፎ ራሱ ግብ ላይ አርፏል። ጨዋታውም በፋሲል ከነማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱም ለዐፄዎቹ የመጀመሪያ ድል ሆኖ ተመዝግቧል።