የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 0-0 ድሬዳዋ ከተማ

ያለ ጎል ከተጠናቀቀው የሀይቆቹ እና የብርቱካናማዎቹ የምሽቱ መርሐ ግብር በኋላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ስለ ጨዋታው …

“ጨዋታው ትንሽ እንደጠበቅነው አልነበረም። ምክንያቱም የእኛ ተጋጣሚ ወርዶ ሲጫወት ስለነበር ፣ ያንን ለማስከፈት ያደረግነው እንቅስቃሴ ብዙም አርኪ አልነበረም ፣ ምን አልባት በዛ መንገድ አላሰብነውም ቡድኑን ፣ በምናገኘው ክፍተት ግን አግኝተናል መጠቀም ባንችልም እንደ እንቅስቃሴ ግን ዛሬ እንደፈለግነው አልነበረም ማለት ይቻላል።”

እስከ አሁን ስለ ተደረጉ ጨዋታዎች…

“እያንዳንዱ ጨዋታ ዝም ብለህ የምታሸንፈው አይደለም ብዙ ስራ ይጠብቅሀል ፣ እያንዳንዱ ቡድን ተጠናክሯል ፣ ከስር የመጡ ቡድኖች ራሱ በጣም ጠንካሮች ናቸው ፣ በዛው ልክ ከአሁን በኋላ መዘጋጀት እንዳለብን ነው የሚሰማኝ።”

በዛሬው ጨዋታ የቡድኑ ጠንካራ ጎን…

“በመልሶ ማጥቃት ለመሄድ ነበር ያሰብነው ፣ ስበናቸው ያንን ቦታ ማግኘት አልቻልንም። በኳስ ቢውልድ አድርገን እንወጣለን ግን የመጨረሻው ፓርት ላይ እነርሱ ሸሽተው ስለ ሚጫወቱ ያንን ማግኘት አልቻልንም እንደ እንቅስቃሴ ኳሱን ጀምረን የምንወጣበት መንገድ ጠንካራ ጎን ነበር ብዬ አስባለሁ።”

አሰልጣኝ አሥራት አባተ – ድሬዳዋ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

“በጣም ጠንካራ ጨዋታ ነበር የነበረው ፣ ከሽንፈት ነው የመጣነው እና በቡና ጨዋታ ላይ የተሻሉ ዕድሎች ነበሩን ያን አልተጠቀምንም እና በዚህኛው ጨዋታ ቁጭት ነበረን ፣ ጠንካራ ቡድን ነው የገጠምነው ፣ ከዕረፍት በፊት በርካታ ኳሶች አግኝተን መጠቀም አልቻልንም እርሱን ብንጠቀም ኖሮ ውጤቱ ይሄ አይሆንም ነበር ፣ ግን ጠንካራ ጨዋታ ነው።”

በጨዋታው በቂ የጎል ዕድል የመፍጠር ውስንነት …

“ከዕረፍት በፊት ብዙ ከሦስት አራት በላይ የጎል ዕድሎች ፈጥረናል ፣ ጎልም ማግባት ችለናል ከጨዋታ ውጪ ተባለ እንጂ ከዕረፍት በኋላ ግን ትንሽ ውጥረት ያለበት ጨዋታ ነው። በሚባለው መልኩ ዕድሎች አልፈጠርንም እንዲሁ የገጠምነው ቡድን ደግሞ ጠንካራ ነው ያንን እንድናደርግም አላስቻለንም።”

ካለፉት ጨዋታዎች ጀምሮ በአጥቂ እና አማካይ ቦታ ላይ በተደጋጋሚ ስለሚደረጉ ለውጦች…

“አሁንም ቢሆን ወጥ ነው። ካለፈው ዓመት ጀምሮ ካየነው ኤልያስ ፣ ሔኖክ ፣ ዳዊት እንዲሁም ደግሞ ቻርለስ አሁንም ኤፍሬም እና ካርሎስ አሉ ፣ አዲስ ስለሆኑ በለቀቁት ስለ ተተካ ነው ፣ ያንኑ ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነው። ቡድኑ ነባር ተጫዋቾቹን ነው በአብዛኛው ያስቀረው ፣ ስለዚህ በጨዋታ እየታረመ የሚመጣ ቡድን ነው።”