የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 2-0 ኢትዮጵያ ቡና

“ዋንጫ የሂደት ውጤት ስለሆነ አሁን ላይ ሆኜ እዛ ጫና ውስጥ እንዲገቡ አልፈልግም” አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

“ክለቡን በበላይነት እየመሩ ያሉ ሰዎች ቡድኑን ለምን በሚገባ ማዘጋጀት እንዳልቻልኩ ሊያብራሩልኝ ይገባል” አሰልጣኝ ኒኮላ ካቫዞቪች

ጥሩ ፉክክር ያስመለከተን የአፄዎቹ እና የቡናማዎቹ ጨዋታ በፋሲል ከነማ የ2ለ0 አሸናፊነት ከተቋጨ በኋላ አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቃለ ምልልስን አድርገዋል።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ – ፋሲል ከነማ

ስለ ጨዋታው …

“ተጋጣሚያችን ቡና ጥሩ ቡድን ነው ያላቸው በጣም ኢነርጂ ያለው ተጭነው ነው የሚጫወቱት ስለዚህ ያንን አውቀን ተዘጋጅተን ነበር የመጣነው። በእነርሱም በኩል ጥሩ ፉክክር ነበረው በሁሉም ረገድ ብልጫ ለመውሰድ በተለይ ከዕረፍት በፊት በጣም ለመታገል ሞክረናል። ጥሩ ዕድሎችንም ለመፍጠር ሞክረናል ፣ ግን ክሊኒካል አልነበርንም። በተለይ የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ያገኘናቸው ዕድሎች ነበሩ ፣ ከዛ አንፃር ክፍተት ነበረብን ሁለተኛው አርባ አምስት ግን በተለይ እነርሱ ትተውት የሚመጡት ቦታ ላይ በሦስት ተከላካይ እንደ መጫወታቸው ከጀርባቸው እና ወደ መስመር አካባቢ ያሉ ክፍተቶች ነበሩ ፣ እነዛን ክፍተቶች በአግባቡ ተጠቅመናል ፣ ጎልም ማግኘታችን የበለጠ ስነ ልቦናችን ከፍ እንዲል አድርጎታል ጥሩ ጨዋታ ነበር።”

ካለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንፃር ዛሬ የተሻሉ መሆናቸው…

“ቡድን እያደረ እያደረ የሚቆየው ፣ ኢትዮጵያ ቡናን ካየህው የዘንድሮው እና የአምናው ፣ የአቻምናው ቡድን ነፀብራቅ ነው ማለት ትችላለህ ፣ በተለይ አምና በርካታ ወጣት እና ብዙ ተጫዋቾችን አዘዋውሮ ነበር ፣ ቡድኑ እስኪዋሀድ ድረስ ጊዜ ወስዶባቸው ነበር። አሁን ግን ጥሩ የመግባባት ደረጃ ላይ ደርሰዋል ማለት ትችላለህ ያ የሚያሳይህ በቆየህ ቁጥር የበለጠ እየተግባባህ ትመጣለህ የበለጠ እየተቀናጀህ ትመጣለህ ፣ የአንዱን ፍላጎት ሌላኛው እያወቀ ይመጣል ያም ይመስለኛል የበለጠ እየቆየን ስንመጣ ከዚህ የተሻልን እንሆናለን አሁንም ብዙ ክፍተቶች እንዳሉብን አይቻለሁ ፣ እነርሱ ላይ ደግሞ የበለጠ መስራት አለብን።”

ስለ አማኑኤል ገብረሚካኤል …

“አማኑኤል ከጎል ርቆ ነበር ፣ ተደጋጋሚ ጉዳት ከማስተናገዱ ጋር ተያይዞ እኛም ብንሆን የእርሱን ስነ ልቦና ለመጠበቅ ብዙ ስራዎችን እየሰራን ነው። ልጁም ምቹ ነው ለስራ ቀና የሆነ ሰው ስለሆነ ፣ የምትሰጠውንም ነገር በአግባቡ የሚቀበልህ ሰው ነው። ብዙ ነገር እንጠብቃለን ከእርሱ ትልቅ ተጫዋች ነው ዘንድሮ አይደለም ጎል ማግባት የጀመረው ፣ ስለዚህ ወደዛ ከፍታው እንዲመለስ የምችለውን እንረዳዋለን። ዛሬ ግን ከጓደኞቹ ጋር ትልቅ መስዋዕትነት ከፍሏል ፣ ልዩነትም ፈጥሯል ፣ በዚህ ደስተኛ ነኝ እርሱንም እንኳን ደስ አለህ ማለት እፈልጋለሁ።”

ቡድኑን በርካቶች ለዋንጫ ስለ መጠበቃቸው…

“ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችን ይዘናል ፣ ግን ጥሩ ተጫዋቾችን ስለያዝክ ብቻ ዋንጫ ትበላለህ ማለት አይደለም ፣ ብዙ ስራ ያስፈልግሃል። እነዛን ተጫዋቾች በራሱ ማዋሀድ ተጫዋቾቹ የቡድኑ ስሜት በውስጣቸው እስኪገባ ድረስ ጊዜ ይፈልጋል። ዋንጫ የሂደት ውጤት ስለሆነ አሁን ላይ ሆኜ እዛ ጫና ውስጥ እንዲገቡ አልፈልግም ፣ ግን ጥሩ ቡድን እንዳለን ጥሩ ቡድን እየገነባን እንዳለን ነው የሚሰማኝ ፣ ቀጣይ ሁለት ሦስት ዓመት የተሻለ ነገር ለመስራት ነው ዕቅዳችን ዘንድሮም ቢሆን ፉክክሩ ላይ እስከ መጨረሻው የምንችለው ጥረት ለማድረግ ዝግጁ ነን።”


አሰልጣኝ ኒኮላ ካባዞቪች – ኢትዮጵያ ቡና

ለጨዋታው ስላደረጉት ዝግጅት…

“ለጨዋታው ያደረግነው ዝግጅት በብዙ መልኩ ስህተቶች የነበሩት ነበር ለዚህም እኔ ሀላፊነቱን እወስዳለሁ። የአሰልጣኝ ቡድናችን አባላት ፋሲልን በዝርዝር ተንትነው አቅርበውልኛል ፣ ነገር ግን እኔ እንደ ዋና አሰልጣኝ ቡድኑን በተገቢ መልኩ አላዘጋጀሁም። ከእኔ በላይም ክለቡን በበላይነት እየመሩ ያሉ ሰዎች ቡድኑን ለምን በሚገባ ማዘጋጀት እንዳልቻልኩ ሊያብራሩልኝ ይገባል። ሁኔታውን የሚረዳ ሰው ዝግጅታችን ለምን ጥሩ እንዳልነበር ይገባዋል።”

በጨዋታው ሜዳ ላይ ስለነበራቸው እንቅስቃሴ…

“በቅድሚያ ፋሲሎችን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ድሉ የሚገባቸው ነበር ፣ ግቦች አስቆጥረን አቻ ብንለያይ እንኳን ከነበረን እንቅስቃሴ አንፃር አይገባንም። ፋሲሎች በሚገባ በሁሉም የጨዋታ ምዕራፎች ከጨዋታው ውጭ አድርገውናል ፤ እኛም እነሱ የነበራቸውን ጠንካራ መዋቅር ለማስከፈት ፍፁም ተቸግረን ነበር በጨዋታው ባልተለመደ መልኩ ከ6 ሰከንድ በላይ ኳሱን በእግራችን ለማቆየት ተቸግረን ነበር። በጨዋታው ከረጃጅም ኳሶች መነሻነት ሁለተኛ ኳሶችን መጠቀም በሚያስችል የቦታ አያያዝ ብልጫን ወስደውብን ነበር። ከዛ ባለፈም በጨዋታው በሽግግሮች ላይ የነበራቸውን ጥንካሬ መቆጣጠር ተስኖናል።”

በጨዋታው ስለ ተጠቀሙበት የአጥቂ መስመር ጥምረት…

“ከአምናው ቡና አንፃር በብዙ መልኩ የተለወጠ ቡናን ለመገንባት እየሞከርን ነው ፤ በዚህም ሂደት ብዙ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ መጀመርያ 11 አምጥተን እየተጠቀምን ነው። ቡድናችንን ከኃላ መስመር ተነስተን እየገነባን ነው ከኃላ ያሉት ሦስት ተከላካዮች ጥምረት በጣም ጥሩ የሚባል ነው ከእነሱ ፊትም ያሉት አምስት ተጫዋቾች እንቅስቃሴ በጣም ከፍ ባለ ደረጃ የሚነሳ ነው። ነገርግን አሁን ድረስ በምንፈልገው ልክ ጥሩ የሁለትዮሽ የአጥቂ ጥምረት መፍጠር አልቻልንም ፣ ዛሬ መስፍን እና ብሩክ ዕድል አግኝተው ነበር በቀጣይም የምንፈልገው ሁለትዮሽ ጥምረት እስኪመጣ ሙከራችን ይቀጥላል።”