ሪፖርት | መቻል ወደ ድል ተመልሷል

በሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር መቻል በበረከት ደስታ ድንቅ ግብ ወላይታ ድቻን 1-0 ረቷል።

በሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር በወላይታ ድቻ እና መቻል መካከል ሲደረግ ወላይታ ድቻዎች በመድን ላይ ድል ያስመዘገበውን ቡድን ለውጥ ሳያደርጉበት ወደ ሜዳ ሲገቡ ከንግድ ባንኩ ጨዋታ አንፃር መቻሎች የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል። በዚህም አስቻለው ታመነ ፣ ግሩም ሀጎስ እና እና ሳሙኤል ሳሊሶ ወጥተው በምትካቸው ነስረዲን ኃይሉ ፣ ግርማ ዲሳሳ እና ከነዓን ማርክነህ ገብተዋል።

ለተመልካች ማራኪ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታው በተጀመረ በሴኮንዶች ውስጥ መቻሎች በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ግብ ሊያስቆጥሩ ነበር። በረከት ደስታ በግራ መስመር እየገፋ የወሰደውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ያገኘው ከነዓን ማርክነህ በግንባሩ ገጭቶ ከመሬት በማንጠር ጥሩ ሙከራ ቢያደርግበትም የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። ያንኑ ሲመለስ ያገኘው ቺጂኦኬ ናምዲም ኃይል በሌለው ሙከራ የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በአንድ ደቂቃ ልዩነት ደግሞ ድቻዎች ባደረጉት የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ፀጋዬ ብርሃኑ ከአበባየሁ ሀጂሶ በተቀበለው ኳስ ከሳጥን አጠገብ ያደረገውን ግሩም ሙከራ ግብ ጠባቂው አልዌንዚ ናፊያን አስወጥቶበታል።

ክፍት በነበረው ጨዋታ በሁለቱም በኩል የማያቋርጡ ተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። በዚሁ እንቅስቃሴም የመቻሉ ሽመልስ በቀለ ከግራው የሳጥን ጠርዝ ጀምሮ በግሩም ክህሎት እየገፋ ወደ መሃል ያመጣውን ኳስ ፈታኝ ባልሆነ ሙከራው አባክኖታል። ወላይታ ድቻዎች በአንጻሩ መሃል ሜዳው ላይ በሚያደርጉት ማራኪ ቅብብል በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ መውሰድ ሲችሉ 27ኛው ደቂቃ ላይ በብዙዓየሁ ሰይፈ እና በቢኒያም ፍቅሩ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር።

ጨዋታው 35ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ መቻሎች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሽመልስ በቀለ ሰንጥቆ ያቀበለውን ኳስ በረከት ደስታ ከሳጥን ውጪ በአስደናቂ ሁኔታ በመምታት ግሩም ግብ አድርጎታል። ጨዋታውን መምራት በጀመሩበት አጋጣሚ ወደ ተሻለ ግለት የመጡት መቻሎች ግብ ካስቆጠሩ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ከሳጠኑ የቀኝ ጠርዝ ላይ የነበረው ቺጂኦኬ ናምዲ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል።

በተደጋጋሚ የተጋጣሚን የግብ ሳጥን ቢፈትሹም እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በቂ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት ድቻዎች 44ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለውን ንጹህ የግብ ዕድላቸውን መፍጠር ችለው ነበር። ሆኖም ቢኒያም ፍቅሩ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ወደ ውስጥ ያሻገረለትን ኳስ ለማስቆጠር ትክክለኛ ቦታ ላይ ሆኖ ያገኘው ፀጋዬ ብርሃኑ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ የኳስ ኃይል የለሽነት ተጨምሮበት ግብ ጠባቂው አልዌንዚ ናፊያን ይዞበታል።

 

ከዕረፍት መልስ መቻሎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት ጨዋታውን ለማረጋጋት ሲሞክሩ ወላይታ ድቻዎች በአንጻሩ ተሻሽለው በመቅረብ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን አድርገው 54ኛው ደቂቃ ላይም ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። አበባየሁ ሀጂሶ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ያደረገው ድንቅ ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ቀስ በቀስ እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታ መቻሎች በኳስ ቁጥጥሩ የተወሰደባቸውን ብልጫ በመጠኑ ማስመለስ ሲችሉ ባልታሰበ የማጥቃት እንቅስቃሴም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር አንሰውም ቢሆን ለመግባት ተደጋጋሚ ጥረት አድርገዋል። በተለይም 80ኛው ደቂቃ ላይ ከነዓን ማርክነህ ከሳጥን አጠገብ ያደረገው እና በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት የወጣበት ሙከራ በአጋማሹ የተሻለው የመቻል ሙከራ ነበር።

በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ወላይታ ድቻዎች በድጋሚ ወደ ጨዋታው ግለት በመመለስ ባላቸው ኃይል ሁሉ ግብ ፍለጋ ተጭነው መጫወታቸውን ሲቀጥሉ 84ኛው ደቂቃ ላይም ተቀይሮ የገባው ዮናታን ኤልያስ ከሳጥን አጠገብ ጥሩ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው አልዌንዚ ናፊያን ይዞበታል። ይህም የተሻለው የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው በመቻል 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።