የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቴክኒክ ዳሬክተርን አስመልክቶ ፌዴሬሽኑ ምላሽ ሰጥቷል

👉  “ከሀገር ስለመውጣታቸው መረጃው የለኝም”

👉 “የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የእግርኳስ ተቋም ነው ፤ የፖለቲካ ድርጅት አይደለም”


👉  “ለእሳቸው ኢትዮጵያ ባለውለታ ናት ብዬ አስባለሁ”

ኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረማርያም ከወራት በፊት ፌዴሬሽኑ ባወጣው የቅጥር ማስታወቂያ መሰረት ከተወዳደሩት ባለሙያዎች መካከል ከፍተኛ ነጥብ በማግኘት የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ዳይሬክተር በመሆን መሾማቸው ይታወሳል። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በስምምነት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኃላፊነታቸው ከተነሱ በኋላ ለተወሰኑ ጨዋታዎች የብሔራዊ ቡድኑ ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ በመሆን ደርበው ሲሰሩ የቆዩት ኢንስትራክተር ዳንኤል  ከብሔራዊ ቡድኑ ቆይታቸው ከተጠናቀቀ በኋላ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ቡድን መሪ በመሆንም እያገለገሉ ነበር። ምንም እንኳን ከጉዳዩ ባለቤት ከኢንስትራክተር ዳንኤል ያገኘነው ማረጋገጫ ባይኖርም ከሀገር ኮብልለው በአሜሪካ እንደሚገኙ ሰምተናል። በዚህ ጉዳይ እና ሌሎች ተዛማች ጉዳዮች ዙሪያ በፌዴሬሽኑ በኩል ምላሽ እንዲሰጡን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁንን አናግረን ተከታዮን ምላሽ ሰጥተውናል።


ቴክኒክ ዳይሬክተሩ ከሀገር ስለ መውጣታቸው ፌዴሬሽኑ በጉዳዩ ዙሪያ ስላለው መረጃ…?

“ከሀገር ስለመውጣታቸው መረጃው የለኝም ፤ ነገር ግን ሕመም ላይ እንደነበሩ አውቃለሁ። በዛ ሒደት ላይ የሕመም ፍቃድ አስገብተው ነበር። ግን የጊዜ ገደቡ እየሰፋ መጥቷል። በቅርቡ የተለያዩ የሴት ብሔራዊ ቡድኖቻችንን ጨዋታዎች እየተከታተሉ ነበር። ወዲያውኑ ግን ቴክኒክ ዳይሬክተሩ የሚመለከታቸው እነዚህን ጨዋታዎችም መከታተል እንዳልቻሉ አውቀናል። ከሀገር ይውጡ አይውጡ እኔ መረጃው የለኝም። በሌላ መንገድ የማውቃቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ከዚህ ቀደም የ “አትሌት ኢን አክሽን” ድርጅት ስልጠና አመቻችቶ እንደነበር አውቃለሁ። ነገር ግን አንድ ሰው ከሀገር ወጥቶም ከሆነ በአግባቡ ለሚሠራበት ተቋም ጥያቄ ያቀርባል ዕረፍት ከሆኑ ወይም የስልጠና ፍቃድ ላይ ከሆኑ የስልጠና ፍቃድ ጠይቀው በአግባቡ ነው መሄድ ያለባቸው ብዬ አስባለሁ። ለእሳቸው ኢትዮጵያ ባለውለታ ናት ብዬ አስባለሁ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ባልነበረው ጊዜ ኃላፊነት ወስደው እንዲሠሩ ዕድሉን የሰጠች ሀገር ናት እና ይህንን ኃላፊነት ደግሞ በወቅቱ የተወጡ ናቸው እና እንደዚህ በቀላሉ ተነስተው ይሄዳሉ ብዬ አላምንም እውነት ለመናገር። ካለን ቀረቤታም አንጻር ይሄንን አንጠብቅም ፤ ሥራዎችም በጋራ ለመሥራት የሞከርንባቸው ጊዜያት እንዳሉ ስለማስታውስ ማለት ነው። ስለዚህ ከሀገር ወጥተዋል የሚለውን ለመቀበል ይቸግረኛል። ለማግኘት ግን በተለያዩ መንገዶች ሞክረን እንደነበር መግለጽ እችላለሁ።”

ቴክኒክ ዳሬክተሩን በተመለከተ ስለወጣው ማስታወቂያ…?

“ከቴክኒክ ዳሬክተሩ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን ለተወሰኑ ቀናት ያህል ህክምና ላይ እንደሆኑ አውቃለሁ። የህክምና ማስረጃም ለሰው ሐብት አስገብተው ነበር። የተቀመጠው የህክምና ፍቃድ ጊዜ እና ወደ ሥራ ያልተመለሱበት ሁኔታ ግልፅ ስላልነበር ማስታወቂያ ሊወጣ ችሏል። ማስታወቂያ ያወጣነው ከሰው ሐብት ጋር ተነጋግረን ምን ያህል ጊዜ ነው የህክምና ፍቃድ የጠየቀው? ከዛ በኋላስ ምን ያህል ጊዜ ነው የቀረ የሚለውን ተነጋግረን ነው። ወደ ስልካቸው ስንደውል ዝግ ስለነበር እና ማግኘት ስላልቻልን ማስታወቂያ አውጥተናል”።

በፌዴሬሽኑ የተለያየ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ ግለሰቦች በተደጋጋሚ ከሀገር ወጥቶ መቅረት እየተስተዋለ ስለመሆኑ እና ምቹ ሁኔታም የለም ተብሎ ስለሚነሳው ሀሳብ ፌዴሬሽኑ ምላሹ ምንድን ነው…?

“የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የእግርኳስ ተቋም ነው ፤ የፖለቲካ ድርጅት አይደለም። እኛ ምቹ የሆነ የሥራ ሁኔታ  እንዲኖር እንፈልጋለን ። እዛ ውስጥ ጫናዎች ሲመጡ ጫናዎቹን ተቋቁሞ መሥራት የሰውየውን አቅም እና ብቃት የሚጠይቅ ጉዳይ ይመስለኛል። እንግዲህ አሁን ሌሎች ሀገራት ላይ ተኪዶ ይመጣል እና እሳቸው እኮ ከዚህ ቀደም ግብፅ ሄደው መጥተዋል ፤ ግብፅ ሄደው አልጠፉም። ሞዛምቢክም ሄደዋል  አልጠፉም። ሌሎችም በተመሳሳይ ደርሰው መጥተዋል። ስለዚህ አልጠፉም በዚያን ጊዜ አመቺ ካልሆነ መጥፋት ትችላለህ እንግዲህ ሀገር መርጠህ አይደለም የምትጠፋው ብዬ ስለማስብ። ከጥቅም ጋር የሚያያዝ ይመስለኛል ለራስ ቅድሚያ በመስጠት የሆነ የተሻለ አካባቢ ላይ መሥራት እፈልጋለሁ ከማለት ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ እንጂ እነዚህ ሌሎች የጠቀስካቸውን አካላት በጠቅላላ እኮ ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ደርሰው መጥተዋል። ለምን እነዛ ሀገራት ላይ አልጠፉም? የተሻለ ነገር ፍለጋ እንዳለ እንደ ሀገር ስናያቸው ለግል የማሰብ ነገር ይኖራል። ይሄ የሰውኛ ባሕሪይ ይመስለኛል እንጂ በፍጹም የሚያሠራ ሁኔታ ሳይኖር የቀረባቸው ጊዜያት አሉ ብዬ አላስብም። ለወደፊት በዝርዝር የምናወራቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። እንደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የምናነሳቸው ነገሮች ይኖራሉ። ነገር ግን እኛ እንደውም ብዙ ነገሮችን ለማመቻቸት ነው ጥረት ያደረግነው ብለን ነው የምናስበው። የአሜሪካ ቪዛም የመጣው እኮ በእኛ ነው ፤ ስለዚህ ዕድሎችን ከግል ዕድገት እና ሁኔታ ጋር የምታያይዝ ከሆነ ትንሽ ከባድ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ። አቶ ዳንኤልንም ጥሪ አወጣን እንጂ አሰናበትናቸው አላልንም። የጥሪ ማስታወቂያ ነው ያወጣነው ፤ ያንንም ዐይተው ምክንያታቸውን አቅርበው ሥራቸውን ይቀጥላሉ ብለን ነው የምናስበው።”

ከሀገር የመኮብለል ችግሮችን ለማስቀረት ፌዴሬሽኑ ምን ይላል…? ቀጣይ ባዶ በሆነው በቴክኒክ ዳይሬክተር ቦታ ምን ታስቧል…?

“ይህ በቀጣይ የሚታይ፣ የምንወያይበት ይሆናል። እንደዚህ የሆነ ጥቅም ፣ ዕድል ሲያገኙ ከሀገር የሚኮበልሉ ፣ ከሀገር የሚወጡ ወይም የግልን ጥቅም ብቻ የማየት ነገር እንዳይኖር እኛ ማየት ያለብን ይመስለኛል። እኛ ሰው የሚበለፅግበት ሳይሆን ብዙዎቹ ስልጠና የሚያገኙበት የአሰልጣኝ ስልጠና ኮርሶቻችን የሚዳብርበት እና የሀገራችን እግርኳስ ሊያሳድጉ የሚችሉ ሌሎች አካላትን መመልከት የሚኖርብን ይሆናል ብዬ አስባለው። አሁንም ግን እርሳቸው ወደ መደበኛ ሥራ ገበታቸው ይመለሳሉ የሚል ቀናዊ የሆነ ሀሳብ አለኝ።

*ኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረማርያም በዚህ ዙርያ ሀሳብ እንዲሰጡን ካሉበት ቦታ ሆነው ሊደርሳቸው የሚችል መልዕክት ያስቀመጥን ሲሆን ምላሽ እንደሰጡን ይዘን እንደምናቀርብ ከወዲሁ መግለፅ እንፈልጋለን።