ሪፖርት | የአሜ መሐመድ የግንባር ጎል ወልቂጤን ባለ ድል አድርጓል

ወልቂጤ ከተማ በቅያሪ ተጫዋቾቹ ዕገዛ ሀምበርቾን በመጨረሻ ደቂቃ ጎል 1-0 በመርታት ተከታታይ ድልን አሳክቷል።

ወልቂጤ ከተማ የዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን ከሻሸመኔ ላይ ሲያገኝ ከተጠቀመው አሰላለፍ ውስጥ በሁለቱ ላይ ለውጥን ሲያደርጉ የቀይ ካርድ ቅጣት ያለነት ተስፋዬ መላኩን በጌቱ ኃይለማርያም እና ዳንኤል ደምሴን በበቃሉ ገነነ ሲተኳቸው ከፋሲሉ ሽንፈት አንፃር ሀምበርቾዎች ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ቅያሪ ቀይ ካርድ የተመለከተው ቴዎድሮስ በቀለ ፣ ብሩክ ቃልቦሬ እና የኋላሸት ፍቃዱ ወጥተው ፀጋሰው ድማሙ ፣ ኤፍሬም ዘካርያስ እና ዳግም በቀለ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ብትንትን ያለ የማጥቃት ቅርፅን ተላብሶ ጅምሩን ባደረገው የቡድኖቹ ጨዋታ የመጀመሪያዎቹ ሀያ አንድ ደቂቃዎች ሜዳ ላይ ከሚታዩ ወጥ ያልሆኑ ቅብብሎች ውጪ ዕድሎች ተፈጥረው ለማየት እምብዛም ያልታደልንበት ነበር። በተወሰነ መልኩ ሀምበርቾ ወደ መስመር በሚጣሉ እና ከቆሙ ኳሶች የግብ ምንጫቸውን ለማግኘት ወልቂጤዎች በረጃጅም ኳሶች ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ለመድረስ ቢታትሩም ከነበራቸው ደካማ ትጋቶች አኳያ የአጨዋወት መንገዳቸው የተሳኩ አልነበሩም። 22ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው እንደደረሰ የመጀመሪያዋን ጥራት ያላትን የግብ ሙከራ በሀምበርቾ በኩል ተመልክተናል። ቶሎሳ ንጉሴ ከግራ በኩል የተገኘውን የማዕዘን ምት ሲያሻማ ኤፍሬም ዘካርያስ በግንባር ገጭቶ ግብ ጠባቂው ፋሪስ ዕላዊ በጥሩ ቅልጥፍና ተቆጣጥሯታል።

ፍሪያማ ያልሆኑ ጥረቶችን እያስመለከተን የቀጠለው ቀሪዎቹ የጨዋታ ደቂቃዎች በአንድ ሁለት ቅብብል ከወልቂጤ በተሻለ መልኩ መነሻቸውን ከመስመር በማድረግ ለመጫወት ጥረቶችን ያደርጉ የነበሩት ሀምበርቾዎች በተደጋጋሚ የተጋጣሚያቸው ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በድግግሞሽ ሲደርሱ ብናስተውልም በቡድኑ የአጥቂ ተሰላፊ ተጫዋቾች ከነበራቸው ደካማ አፈፃፀሞች አኳያ የተገኙ ዕድሎችን በመጠቀም ረገድ አልታደሉም። ደብዛዛ እንቅስቃሴ እና አንድ ኢላማዋን የጠበቀች ሙከራን ብቻ ያስተዋልንበት የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ያለ ጎል ተገባዷል።

ከዕረፍት መልስ ሲመለስ ምንም የተለየ አቀራረብን ሳናስተውል ጨዋታው ቀጥሏል። ወልቂጤ ከተማ ከቀዳሚው አጋማሽ ድክመቱ ወደ ጨዋታ በይበልጥ በመግባት ስንታየሁ መንግሥቱን ትኩረት ባደረጉ የአየር ላይ ኳሶች ለመጫወት ቢሞክሩም አጨዋወታቸው ፍሬያማ ያለ መሆኑን ተከትሎ ከደቂቃዎች በኋላ ስንታየሁን በአሜ ሊቀይሩ ተገደዋል። በአጋማሹ በእጅጉ ተቀዛቅዘው ሜዳ ላይ የሚታዩት ሀምበርቾዎች ወደ ቀኝ መስመር በማዘንበል አቤል ከበደን በይበልጥ በመጠቀም በጥልቀት ወደ ውስጥ በሚሻገሩ ኳሶች ዕድሎችን ሲፈልጉ ተስተውሏል። ሀምበርቾወች 57ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ከቀኝ ወደ ውስጥ እየገፋ ገብቶ የሰጠውን ዳግም ከማግኘቱ በፊት አዳነ በላይነህ ያወጣበትን እና እንዲሁም 77ኛው ደቂቃ ላይ አሁንም ሀምበርቾዎች አብዱሰላም የሱፍ የግብ ጠባቂው ፋሪስ ዕላዊን ከግብ ክልሉ ለቆ መውጣትን ተመልክቶ ወደ ግብ መቶ ኢላማዋን ሳትጠብቅ ኳሷ የወጣችበት በጨዋታው የተደረጉ ጥራት አልባ ሙከራዎች ሆነዋል።

የመጨረሻ አስር ደቂቃዎችን የተጫዋች ቅያሪዎችን በየቦታው በማድረግ አንድ ነገር ለማግኘት ራሳቸው ወደ ጨዋታ የከተቱት ወልቂጤዎች ባደረጉት የመጀመሪያ የጠራ አጋጣሚ ጎልን አግኝተዋል። 86ኛው ደቂቃ ላይ ከእጅ ውርወራ የደረሰውን ኳስ ዳንኤል መቀጮ በፍጥነት ተቀይሮ ለገባው አድናን ፈይሰል ሲያቀብለው ወጣቱ ተጫዋች ወደ ጎል መቶ ግብ ጠባቂው ፓሎማ ፓጆም ሲመልስ አጠገቡ የነበረው ሌላኛው ተቀያሪ ተጫዋች አሜ መሐመድ በግንባር ገጭቶ ኳሷን መረብ አሳርፏት ወልቂጤን መሪ አድርጓል። ጎል ከተቆጠረባቸው ከአንድ ደቂቃ በኋላ በተሻጋሪ ኳስ ሀምበርቾ በዲንክ ኬር የግንባር ኳስን ሞክረው የነበረ ቢሆንም ፋሪስ ዕላዊ በቀላሉ ተቆጣጥሯታል። ጨዋታው ወልቂጤ ከተማ ባደረጋቸው ቅያሪ ተጫዋቾች ታግዞ 1-0 አሸንፎ ወጥቷል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሀምበርቾው አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ ከሌላው ጊዜ አጨዋወታቸውን ቀይረው እንደቀረቡ ገልፀው ጨዋታው ባሰቡት ልክ እንዳልሄደ እና ጥሩ ጨዋታ እንዳልነበር ጠቁመው የተገኙ ዕድሎችን አለመጠቀማቸው በተቃራኒ ቡድን መነሳሳት በመፈጠሩ ተቆጥሮባቸው መሸነፋቸውን ጠቁመዋል። የወልቂጤ አቻቸው ሙሉጌታ ምህረት በበኩላቸው ሁለቱ አርባ አምስት ደቂቃዎች የተለያዩ እንደነበሩ ተናግረው የመጀመሪያው አርባ አምስት ሀምበርቾዎች የተሻሉ መሆናቸውን እና ቡድናቸውም ተጠንቅቆ እንዲጫወት ፈልገው ያ መሆን እንደቻለ እና በሁለተኛው አጋማሽ ኳስን በመቆጣጠር ተጫውተው ውጤት ማግኘት መቻላቸውን ከገለፁ በኋላ ተቀይረው የገቡ ሦስቱም ተጫዋቾች የታዘዙትን እንዳደረጉም አሰልጣኙ አክለዋል።