የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሜዳ ለውጥ ያደርጋል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ጨዋታዎች ላይ የቦታ ለውጥ አድርጓል።

የ2016 ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰባት ሳምንታትን አገባዶ ዛሬ በስምንተኛ ሳምንት ጨዋታዎች እንደሚቀጥል ይጠበቃል። ይህ ከመሆኑ ቀደም ብሎ ግን አወዳዳሪው አካል የ9ኛ እና 10ኛ ሳምንታት ላይ የቦታ ለውጥ ማድረጉን ይፋ አድርጓል።

አክሲዮን ማህበሩ የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እስከ ስምንተኛ ሳምንት ድረስ ሊጉን አስተናግዶ በቀጣይ ሳምንታት ውድድሩ ወደ ድሬዳዋ ያመራ እንደነበር አስታውሶ የድሬዳዋ ስታዲየም ማጠቃለያ ግንባታ ሥራ እስኪስጠናቀቅ የሜዳ ለውጥ ማድረግ ማስፈለጉን ገልጿል።

በዚህም መሰረት የ9ኛ እና 10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እዛው አዳማ ላይ እንደሚከናወኑ አስታውቋል። በጨዋታዎቹ ላይ የቦታ እንጂ የቀን ለውጥ ሳይደረግባቸው በበፊቱ መርሐ ግብር መሰረት እንደሚከናወኑም ጠቁሟል።