የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 0-2 መቻል

“እንደሚሆን እንጠብቅ ነበር ፣ ያንንም ነው ያገኘነው” አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ

“የፈለግነውን ነገር ሳናገኝ ወጥተናል” አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት

መቻል በመጨረሻ ደቂቃ ጎሎች ምሽቱን ወልቂጤ ከተማን 2-0 ካሸነፈበት ጨዋታ መቋጨት በኋላ ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኞች ጋር ቆይታን አድርጋለች።

አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ – መቻል

ስለ ድሉ…?

“ጥሩ ነው ጨዋታው ፣ ወልቂጤ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን አሸንፎ ነው የመጣው ስለዚህ ጨዋታው ጠንካራ እንደሚሆን እንጠብቅ ነበር ፣ ያንንም ነው ያገኘነው።”

ተከላካዮችን አልፎ ግብ ለማስቆጠር ረጅም ደቂቃን ማስቆጠራቸው…

“እግርኳስ እኮ ዘጠና ሲደመር ስለሆነ ጊዜ ፈጀ አንልም እኛ ፤ ዘጠናው እስካላለቀ ድረስ። ስለዚህ ምንድነው ዘጠና ደቂቃም አልቆ በባከነም ጎል ስለምታገባ የጨዋታው አካል ነው እና እነርሱ ወደ ኋላ ተመልሰው ጥቅጥቅ ብለው ስለሆነ ያ ነገር ደግሞ ከእኛ ጎል ማግባት ፍላጎት ፣ ጉጉት ተጫዋቾች ኳሱን ቶሎ ቶሎ ከዕረፍት በፊት ይጥሉት ነበረና ያንን ከዕረፍት በኋላ አርመነዋል።”

በጨዋታው ስሜታዊ ስላረጋቸው ነገር …

“እንደዚህ ይከሰታል ፣ አንዳንዴ ምክንያቱም እንደ አሰልጣኝ ውጤቱን ትፈልገዋለህ እና አንድ ጊዜ ነው የተፈጠረው ተማምነናል ከዳኞቹም ጋር ብዙ አይደለም ንክኪው ፣ ለእኛ ነው ፋውሉ የሚገባው የሚል ነው።”

ናይጄሪያዊው አጥቂ ቺጂኦኪ ናምዲ ከረጅም ሳምንታት በኋላ የመጀመሪያ ጎልን ማስቆጠሩ …

“ምንድነው ከአንድ ሀገር ወደ አንድ ሀገር ስትመጣ የሀገሩን ራሱ አመጋገብ ፣ ባህል ፣ ከተጫዋቾች ጋር በቋንቋ መገናኘት እነዚህ ሁሉ ተፅዕኖ አላቸው። አሁን እየለመደ ሲመጣ ግን ወደ ጎል አግቢነቱ ይመለሳል ፣ ስለዚህ አሁን ጎል ማግባት ጀምሯል አሁንም ከዚህ በኋላ ይቀጥላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።”

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

“ጨዋታው እንደጠበቅነው ጥሩ ነው ማለት ባይቻልም ግን የፈለግነውን ነገር ሳናገኝ ወጥተናል። ሜዳ ላይ በነበረው እንቅስቃሴ ግን ተጫዋቾቹ ጥሩ ነገር አድርገው አሳይተውናል ፣ የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት ቢያንስ ይዘን ነበር ለመውጣት የፈለግነው። ግን ዞሮ ዞሮ ባለቀ ሰዓት ገብቶብን ተሸንፈናል ጨዋታው ጥሩ ነበር በአጠቃላይ በጣም።”

አቻ ውጤትን በጨዋታው ስለመፈለግ…

“ካገኘን አቻ በአጋጣሚ ደግሞ ካገኘን አግብተን ለመጨረስ ነበር ሜዳ ላይም የነበረው ያ ነበር። አሁን የሚያስፈልገን ነጥብ ስለሆነ ቅድሚያ ለዛ ሰጥተን ነው የመጣነው።”