ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | መሪው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከታታይ ሽንፈት አስመዝግቧል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ‘ሀ’ ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ በድጋሚ ሲሸነፍ አዲስ አበባ ከተማ እና ነቀምቴ ከተማ በነጥብ ተስተካክለውታል።

የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ስልጤ ወራቤን ከሀላባ ከተማ አገናኝቷል። የሀላባ ከተማ የበላይነት የታየበት ጨዋታ ተመልክተናል። በጨዋታው ስልጤ ወራቤ በጣም ወደ ኋላ አፈግፍጎ እና ኳስን ለተጋጣሚው በመተው ጫና ውስጥ ራሱን ሲከት ተስተውሏል። በአንፃሩ ሀላባ ከተማ ኳስን ተቆጣጥሮ በሙሉ የበላይነት ጫና ፈጥሮ ተጫውቷል። በ26ኛው ደቂቃ ሀላባ ከተማ ተጫዋች የሆነው ምትኩ ባንዳ በጥሩ ቅብብል ያገኘውን ኳስ በግሩም አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮታል። ከግቡ መቆጠር በኋላም ሀላባ ከተማ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ይበልጥ ጫና የፈጠረ ሲሆን በ37ኛው ደቂቃ ምትኩ ባንዳ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ አሸናፊ በቀለ ግብ አስቆጥሯል።

ከዕረፍት መልስ ስልጤ ወራቤ የተጫዋች ቅያሪ ያደረገ ቢሆንም ከመጀመሪያው አጋማሽ ተሽሎ መቅረብ ተስኖታል። በአንፃሩ ሀላባ ከተማ በከፍተኛ ጥረት እና የማሸነፍ ስሜት ሲጫወቱ ተስተውሏል። በ61ኛው ደቂቃ ሀላባ ከተማ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ አሸናፊ በቀለ በራሱ ጥረት ጥሩ ግብ ማስቆጠር ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ስልጤ ወራቤ ግብ ለማስቆጠር የተወሰነ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው በሀላባ ባሳከው ድል ነጥቡን 11 አድርሶ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሁለተኛ የምድቡ ጨዋታ የነበረው እና ከፍተኛ ትንቅንቅ የተመለከትንበት ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከጅማ አባ ቡና አገናኝቷል። በጨዋታው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጥሩ የሆነ የኳስ አጨዋወት እና ፍሰት ወደ ግብ ለመሄድ ጥረት ሲያረግ በአንፃሩ ጅማ አባ ቡና ፈጣን በሆነ አጨዋወት የግብ እድልን ከመስመር በማሻገር ለመፍጠር ሲጥሩ ተስተውሏል። ጨዋታው በተጀመረ በ1ኛው ደቂቃ ጅማ አባ ቡና በጴጥሮስ ገዛኸኝ ማካኝነት ግልፅ የግብ ዕድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው አጋጣሚ ይታወሳል። በአጋማሹ ተመጣጣኝ እና ከፍተኛ ፉክክር የተመለከትንበት ቢሆንም ምንም ግብ ሳይቆጠር ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ለአይን ሳቢ እና ከመጀመሪያው አጋማሽ በጣም የተሻለ አጨዋወት ተመልክተናል። በ47ኛው ደቂቃ የጅማ አባ ቡና ተጫዋች የሆነው እስጢፋኖስ ተማም ጴጥሮስ ገዛኸኝ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ወደ ግብ ቀይሯል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ እና ጫና በመፍጠር ጥረት አድርገዋል። በ59ኛው ደቂቃ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በተጫዋቹ ቢንያም ካሳሁን ላይ በተሰራ ጥፋት ያገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ቢንያም ካሳሁን አስቆጥሯል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የተነቃቁ ሲሆን ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጫናቸውን ቀጥለዋል። በ72ኛው ደቂቃ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመልሶ ማጥቃት ያገኘውን ኳስ ያሬድ ብርሀኑ በራሱ ጥረት በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ መቀየር ችሏል።

ጅማ አባ ቡና ከተቆጠረበት በኋላ በከፍተኛ ተነሳሽነት ግብ ለማስቆጠር ባደረጉት ጥረት በ81ኛው ደቂቃ ከተቀያሪ ወንበር የተነሳው ያሬድ መሀመድ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ግብ ጠባቂውን በማታለል በግሩም አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል። ቀሪውን ደቂቃ እልህ በተሞላበት ጨዋታ ለመሸናነፍ ከፍተኛ ፉክክር አድርገዋል። ይህንን ተከትሎ በ87ኛው ደቂቃ በተፈጠረ ግጭት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ናትናኤል ሰለሞን እና ከጅማ አባ ቡና ያሬድ መሀመድ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተዋል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረ ደቂቃ ጅማ አባ ቡና በፈጣን መልሶ ማጥቃት ተቀይሮ የገባው ኩሰ ሞጮራ ቡድኑን አሸናፊ ያረገች ግብ አስቆጥሯል ። ጨዋታውም በአባ ቡና 3-2 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ቡድኑ ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ መጠጋት ችሏል። በአንፃሩ ተከታታይ ሽንፈት ያገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከተከታዮቹ ጋር በግብ ክፍያ ብቻ እንዲለያይ ሆኗል።

የዕለቱ ሦስተኛ ጨዋታ ንብን ከአዲስ አበባ ከተማ አገናኝቷል። በጨዋታው በሁለቱም ቡድኖች በኩል ቀዝቀዝ ያለ እና በመፈራራት የተጫወቱበት ጨዋታ ነው ። በሙከራም ረገድ አነስተኛ የሆነ እንቅስቃሴ ተመልክተናል። አዲስ አበባ ከተማ በተወሰነ መልኩ ወደ ፊት ለመሄድ ጥረት ያደረገ ቢሆንም ኳሶቹ በተደጋጋሚ ሲቆራረጥ ተመልክተናል። ንብም መለሶ ማጥቃትን ምርጫ በማድረግ የተጫወቱ ቢሆንም በተቀናጀ ሁኔታ የማጥቃት ሙከራ ተመሰንዘር ተቸግረዋል።

ከእረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች ከመጀመሪያው አጋማሽ ተሻሽለው እና ግብ ለማስቆጠር ጥሩ ጥሩ እንቅስቃሴ አስመልክተውናል። አዲስ አበባ ከተማ ኳስን በተሻለ ተቆጣጥሮ በተደጋጋሚ ወደ ግብ እየደረሰ የግብ እድል የፈጠረ ቢሆንም ኳስን ከመረብ ማዋሀድ ተስኖታል። ንብም በመልሶ ማጥቃት የተወሰነ የግብ ሙከራ ቢያደርጉም ወደ ግብ መቀየር ተስኗቸዋል። ይህንንም ተከትሎ በ78ኛው ደቂቃ የንብ ተጫዋች የሆነው ናትናኤል ግልፅ የግብ እድል ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ተመልሶበታል። ያለግብ በተጠናቀቀው ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ ምድቡን መምራት የሚችልበትን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ሞጆ ከተማን ከነቀምቴ ከተማ አገናኝቷል። ነቀምቴ ከተማ ተሽለው በተገኙበት ጨዋታ የኳስ ቁጥጥር በመብለጥ የተሻለ የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውሏል። ሞጆ ከተማም ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ወደ ግብ ለመድረስ ሞክረዋል። በ10ኛው ደቂቃ የነቀምቴ ከተማ ተጫዋች የሆነው ተመስገን ዱባ ያሻማውን ኳስ ሮቦት ሳለሎ በግንባር ግብ ማስቆጠር ችሏል። ብዙም ሳይቆይ በ18ኛው ደቂቃ ነቀምቴ ከተማ በመስመር ኳስን ይዞ በመሄድ ወደ ግብ ክልል ተሻምቶ ምኞት ማርቆስ ዳግም በግንባር ግብ ማስቆጠር ችሏል።  አጋማሹም በዚሁ ውጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴን አስመልክተውናል። ሞጆ ከተማ አልፎ አልፎ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ወደ ጨዋታው ሚመልሳቸውን ግብ ማግኘት አልቻሉም። ነቀምቴ ከተማም የወሰደውን የግብ የበላይነት ለማስጠበቅ ጥንቃቄን መርቶ ተጫውቷል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው የመጀመሪያ ደቂቃ የነቀምቴው ተመስገን ዱባ በግል ጥረት ግሩም ግብ አስቆጥሯል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ የዳኛው ፊሽካ በሚጠበቅበት ደቂቃ ሞጆ ከተማ ያገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አሚር ራመቶ አስቆጥሯል። ነቀምቴ ከተማ ባሳካው የ3-1 ከመሪዎቹ ጋር በነጥብ ተስተካክሎ በግብ ክፍያ 3ኛ ደረጃን ይዟል።