ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | አርባምንጭ ከተማ ወደ መሪነት የተጠጋበትን ድል አስመዘግቧል

በምድብ ‘ለ’ የመጨረሻ ቀን አራት ጨዋታዎች ተደርገው አራቱም ጨዋታዎች በመሸናነፍ ሲጠናቀቁ ደሴ ከተማ ፣ ወሎ ኮምቦልቻ ፣ ቢሾፍቱ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ድል አድርገዋል።

ረፋድ 3 ሰዓት ሲል በጀመረው በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በሁለተኛ ቀን መርመግብር ደሴ ከተማ ምድቡን ሁለተኛ ሆኖ እየመራ የሚገኘውን ሸገር ከማን አሸንፏል። ሁለቱም ቡድኖች በጥንቃቄ በመከላከል የገቡበት የመጀመሪያ አጋማሽ ብዙ የግብ ሙከራዎች ሳያስመለከተን 0ለ0 በሆነ ውጤት የተጠናቀቀ ሲሆን ሸገር ከተማ ወደ መሪነት ለመጠጋት ኳስን ተቆጣጥሮ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስዶ ዕረፍት ወጥተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ጨዋታውን ለመቀየር ጥረት አድርገዋል። ሸገር ከተማ በተደጋጋሚ አስቆጪ የግብ ሙከራዎችን አድርጎ ሳይጠቀም ቀርቷል። ደሴ ከተማ በአንፃሩ የተጨዋች ቅያሪ ካደረገ በኋላ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገ ሲሆን በተለይም ፀጋ ደርቤ ተቀይሮ ከገባ በኋላ ጨዋታውን ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል።

ከመጀመሪያው አጋማሽም ጀምሮ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የታየው ሙሉጌታ ካሳሁን በ80ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ከገባው ከብሩክ ብርሃኑ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ወደግብነት ቀይሮ መሪ እንዲሆኑ አስችሏል።

የመጀመሪያ ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ወደ ጨዋታ በመመለስ ጥሩ እንቅስቃሴ ያስመለከተው ደሴ ከተማ በድጋሚ ተቀይሮ በገባው ፀጋ ደርቤ አማካኝነት ወደ ግብ የተመታውን ኳስ የሸገር ከተማው በረኛ ተፍቶት ከተቀያሪ ወንበር የተነሳው ብሩክ ብርሃኑ በ87ኛው ደቂቃ ኳስና መረብ አገናኝቶ 2-0 በሆነ ውጤት አሸንፎ እንዲወጡ አስችሏል።

ከዚህ ጨዋታ በማስከተል 5 ሰዓት ላይ በተደረገው መርሐግብር ወሎ ኮምቦልቻ ከደረጃ ሰንጠረዥ ፈቀቅ ማለት የቻለበትን ነጥብ ከባቱ ከተማ ወስዷል። ብዙ የግብ ሙከራዎች ባልታዩበት በዚህ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተስተውለዋል።

በአንደኛው አጋማሽ ከባቱ አንፃር ተሽሎ የገባው ወሎ ኮምቦልቻ አልፎ አልፎ ወደ ተቃራኒ ቡድን የሚሄደውን ኳስ ሳይጠቀም ቀርቷል። በ30ኛው ደቂቃ ቢላል ገመዳ በረኛው የተፋውን ኳስ ጠብቆ በማስቆጠር እየመሩ ዕረፍት እንዲወጡ አድርጓል።

በሁለኛው አጋማሽ ባቱ ከተማ የአቻነት ግብ ፍለጋ ከተቃራኒው ቡድን ተሽሎ የገባ ሲሆን በፊት መስመር ተጫዋቾቻቸው አማካኝነት በተደጋጋሚ አስቆጪ የሚባሉ ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አግኝተው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።

ጨዋታው እስካለቀበት ድረስ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ ጫና ፈጥሮ የተጫወተው ባቱ ከተማ የአቻነት ግብ ለማግኘት አብዝቶ ቢጥርም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠረ ግብ 1ለ0 በሆነ ውጤት ሽንፈት አስተናግደዋል።

ቀን ስምንት ሰዓት ላይ በተደረገው ጨዋታ ቢሾፍቱ ከተማ ያለ ወትሮው ከ2 በላይ ግብ በማስቆጠር ተጋጣሚውን ካፋ ቡናን አሸንፏል። ጨዋታው እንደጀመረ በኳስ ቁጥጥር ፍፁም የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ የተጫወተው ቢሾፍቱ ከተማ በ11ኛው ፣ በ18ኛው እና በ24ኛው ደቂቃ ግቦችን አከታትሎ ያስቆጠረ ሲሆን ለካፋ ቡና ከሽንፈት ያልታደገቻቸውን ግብ ያቤፅ ፍሬው አስቆጥሯል።

በጨዋታ ቁጥጥር በልጠው የተገኙት ቢሾፍቱ ከተማዎች በ11ኛው ደቂቃ ኳስን እየገፉ ወደፊት በመሄድ በፍሬገነት ኤርሚያስ አማካኝነት ኳስና መረብ አገናኝተው መሪ ሆነዋል። ግቡ ከገባባቸው በኋላ መረጋጋት ያቃታቸው ካፋ ቡናዎች በተከላካዮቻቸው መካከል በተፈጠረው አለመግባባት የሠሩትን ስህተት በብልጠት በመጠቀም አብዱላዚዝ ኳሷን አግኝቶ ዕድሉን ተጠቅሞ ሁለተኛ ግብ በማስቆጠር 2-0 እንዲመሩ አድርጓል።

ተጨማሪ ግብ ፍለጋቸውን የቀጠሉት ቢሾፍቱ ከተማዎች በድጋሚ ኳስን እየገፋ በመሄድ በእርስ በርስ ቅብብሎሽ በሁለተኛው ግብ አስቆጣሪ በአብዱላዚዝ አማካኝነት ሶስተኛውን ግብ አስቆጥረው ሦስት ለባዶ መምራት ችለዋል።

ካፋ ቡና በአንፃሩ በ32ኛው አጋማሽ ኳስን እየገፉ በመሄድ በያቤፅ ፍሬው አማካኝነት ኳስና መረብ አገናኝተው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉ ሲሆን ዕረፍት 3ለ1 በሆነ ውጤት በመጨረስ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለኛው አጋማሽ ብዙም የግብ ሙከራዎች ያላስመለከተ የተቀዛቀዘ አጋማሽ የተመለከተን ሲሆን ቢሾፍቱ ከተማ ነጥቡን ለማስጠበቅ በመከላከል ሲጫዎቱ ተስተውለዋል። ባቱ ከተማዎችን ይሄ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ሲያደርጉ አልተስተዋሉም። በመሆኑም ጨዋታው በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች 3-1 በሆነ ውጣት በቢሾፍቱ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል ።

በውጥረት የተሞላው የሰባተኛ ሳምንት ማሳረጊያ የሆነው  የ10 ሰዓቱ ጨዋታ በአርባምንጭ አሸናፊነት ተጠናቋል። በሁለቱም አጋማሽ የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ የጨዋታ ነበላይነት ያሳዩት አዞዎቹ ወደ መሪነት የተጠጉበትን ነጥብ አዲስከተማ ክፍለከተማን 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ አስመዝግበዋል።

!

በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ኳስን ተቆጣጥረው የጨዋታ ብልጫ ወስዶ ግቦችን ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል። ሆኖም ግን አዲስ ከተማ ክፍለከተማ በዛሬው ዕለት ትንሽ ተዳክመው የገቡ ሲሆን በተከላካዮቻቸው አማካኝነት በተሠራው ጥፋት ሽንፈት አስተናግደዋል።

ጨዋታው ከጀመረ በ19ኛው ደቂቃ አህመድ ሁሴን ኳስን እየገፋ ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል በሚገባበት ቅፅበት የአዲስ አበባ ከተማ ተከላካዮች ጥፋት ሰርተውበት ፍፁም ቅጣት ምት አግኝቷል። ፍፁም ቅጣት ምቱን አሸናፊ ተገኝ በመምታት አስቆጥሮ የጨዋታው ብቸኛ ግብ እንዲሆን አስችሏል።

ወሳኝ ሦስት ነጥብ ለማሳካት በቁርጠኝነት የገቡት አርባምንጭ ከተማዎች እስከ መጨረሻው ደቂቃ ተጨማሪ ግብ ፍለጋ የግብ ሙከራ ሲያደርጉ ቢስተዋሉም በመጀመሪያው አጋማሽ ያገኙትን ግብ በመጠቀም 1ለ0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ደረጃቸውን አሻሽለዋል።