የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ | የ 8ኛ ሣምንት ምርጥ 11

የስምንተኛ ሣምንት ጨዋታዎች ላይ በመመርኮዝ ይህንን ምርጥ ቡድን ሠርተናል።

ግብ ጠባቂ

አቡበከር ኑራ – ኢትዮጵያ መድን

ጎልተው የወጡ ግብ ጠባቂዎች ማግኘት አዳጋች በሆነበት በዚህ ሳምንት ውስጥ አቡበከር ኑራ በንፅፅር የተሻለ ሆኖ አግኝተነዋል። ቡድኑ ከድል ለታረቀበት ጨዋታ ከኋላ ሆኖ ቡድን በመምራት እና በፍጥነት ኳሶችን በማስጀመር ጎል ሳይቆጠርበት በመጨረሻ ደቂቃዎች በተገኙ ጎሎች ቡድኑ አሸንፎ እንዲወጣ በማስቻሉ ምርጫ ውስጥ እንዲካተት ሆኗል።

ተከላካዮች

ብርሀኑ በቀለ – ሲዳማ ቡና

በዘንድሮ ዓመት አዲሱ ክለቡን የተቀላቀለው ብርሃኑ ምንም እንኳን በቀደመ አቋሙ ባይገኝም ከዚህ ቀደም በሚታወቅበት አቋም ራሱን ለማግኘት እየጣረ ይገኛል። ሲዳማ ቡና ወላይታ ድቻ ላይ የ 4ለ1 ወሳኝ ድል ተቀዳጅቶ የመጀመሪያ ሦስት ነጥቡን ባሳካበት ጨዋታ ላይ ብርሃኑ በቀለ በመከላከሉ በኩል የተሳካ ጊዜን በማሳለፉ የሣምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ መካተት ችሏል።


እንዳለ ዮሐንስ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በአሰልጣኝ በጸሎት በመከላከሉ በኩል የፈቱዲን ጀማል አጣማሪ እንዲሆን የመጀመርያ ምርጫ የነበረው ካሌብ አማንክዋሀ ጉዳት ካስተናገደ በኋላ የመጫወት ዕድል ያገኘው እንዳለ በጥሩ ግልጋሎት ቦታውን እያስከበረ ይገኛል። ንግድ ባንክ ከኢትዮጵያ ቡና ፈታኝ ጥቃት ቢሰነዘርበትም በንቃት በመከላከል የራሱን አስተዋጽኦ በማበርከቱ ምርጫ ውስጥ ተካቷል።

ምንተስኖት ከበደ – ሻሸመኔ ከተማ

ሻሸመኔ ከተማዎች ከአዳማ ጋር ባደረጉት እና በውድድር ዓመቱ ሁለተኛውን የአቻ ውጤት አስመዝግበው ነጥባቸውን 2 ባደረሱበት ጨዋታ የመሃል ተከላካዩ ብቃት አስደናቂ ነበር። የአዳማ አጥቂዎች በፈጣን ሽግግር ለማጥቃት በሚሞክሩበት ወቅት ኳሶችን የሚያቋርጥበት እና የአንድ ለአንድ ግንኙነቶችን ሲያሸንፍበት የነበረው መንገድ በቦታው ያለ ተቀናቃኝ ተመራጭ አድርጎታል።

ፍራኦል መንግሥቱ – ባህር ዳር ከተማ

በተከታታይ ጨዋታዎች ባልተገደበ የማጥቃት እንቅስቃሴ ትኩረት ሳቢ ክህሎት የሚያሳየው የመስመር ተከላካዩ ፍራኦል ባሳለፍነው ሣምንትም የጣና ሞገዶቹ  ድሬዳዋ ከተማን 2ለ1 በረቱበት ጨዋታ ካደረገው እንቅስቃሴ ባሻገር የቡድኑን የመጀመሪያውን ግብም በስሙ አስመዝግቧል።

አማካዮች

ግርማ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና

ሀዲያዎች ዐፄዎቹን በመርታት የመጀመርያ ሦስት ነጥባቸውን ባሳኩበት ጨዋታ ግርማ በቀለ ለቡድኑ እፎይታ የሰጠች አንድ ጎል ከማስቆጠሩ ባሻገር ቡድኑ ሦስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ የነበረው ታታሪነት መልካም የሚባል ነበር። በወጣት ተጫዋቾች እየተገነባ ባለው የሀዲያ ሆሳዕና ስብስብ ውስጥ የባለ ብዙ ልምዱ ግርማ በቀለ ሚና ጎልቶ በመታየቱ በዚህ ቦታ ልንመርጠው ችለናል።

ዳዊት ተፈራ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ለተከታታይ ሦስተኛ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት በሚያደርጉት ጉዞ ውስጥ ዳዊት ተፈራ ከረጅም ጊዜ ጉዳት መልስ ወደ ጥሩ አቋሙ በመመለስ የቡድኑ የመሐል ክፍል ዋና ሰው እየሆነ መጥቷል። ፈረሠኞቹ ሀዋሳ ከተማን ሲረቱ የማጥቃት እንቅስቃሴውን ሲዘውር የዋለው ዳዊት አቤል ያለው አከታትሎ ላስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች በሚገርም ዕይታ አመቻችቶ ያቀበለበት መንገድ አስደናቂ ነበር።

ባሲሩ ኦማር – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሣምንት ሣምንት በማይዋዥቅ አቋም የብዙዎችን ትኩረት ከሚስቡ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ጋናዊው አማካይ ባሲሩ ንግድ ባንኮች ኢትዮጵያ ቡና ላይ የ 2ለ1 ድል በመቀዳጀት የሊጉ መሪነታቸውን ሲያስቀጥሉ ለመጀመሪያው ግብ አመቻችቶ ማቀበል ሲችል የቡድኑን ሁለተኛ ግብም ማስቆጠር ችሏል።

አጥቂዎች

አሸናፊ ጥሩነህ – ሻሸመኔ ከተማ

ሻሸመኔዎች ከአዳማ ጋር አንድ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ለቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው የመስመር አጥቂው በሁለት አጋጣሚዎች የግብ ዕድሎችን መጠቀም ባይችልም ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመግባት ሲያደርገው የነበረው እንቅስቃሴ ማራኪ እና ፈታኝ ነበር። ቡድኑ ላስቆጠረው ግብም ቁልፍ መነሻ የነበረ በመሆኑ በምርጥ ቡድናችን ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል።

ተመስገን ብርሃኑ – ሀዲያ ሆሳዕና

ነብሮቹ በውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድላቸውን ፋሲል ከነማን 2-1 በመርታት ሲያሳኩ የፈጣኑ የመስመር አጥቂ ተመስገን ብቃት የሚደነቅ ነበር። ወደ ሳጥን የሚያርጋቸው ሩጫዎቹ ለተጋጣሚ ቡድን ፈታኝ የነበረው ተጫዋቹ ከእንቅስቃሴው ባሻገር የቡድኑን የመጀመሪያ ግብም በግሩም አጨራረስ ማስቆጠር መቻሉ በቦታው ተመራጭ አድርጎታል።

አቤል ያለው – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ባሳለፍነው ዓመት በጥሩ የውድድር ዓመት በማሳለፍ ቡድኑን ባለ ዋንጫ ያደረገው አቤል የዘንድሮ አቋሙ ደግሞ እጅግ ይለያል። በወጥ አቋም እስከ ስምንተኛው ሳምንት መዝለቅ የቻለው አቤል የሀዋሳን የመከላከል አጥር በማፈራረስ ሦስት ጎሎችን በማስቆጠር ሐት- ትሪክ ከመሥራቱ ባሻገር የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን በስምንት ጎሎች እየመራ በመገኘቱ በዚህ ምርጥ ስብስብ ውስጥ ያለ ተቀናቃኝ መካተት ችሏል።

አሰልጣኝ አረጋይ ወንድሙ – ሲዳማ ቡና

ሲዳማ ቡናዎች ወላይታ ድቻን በሰፊ የግብ ልዩነት 4ለ1 በመርታት ካሉበት የውጤት ማጣት ቀውስ በመጠኑ ሲያገግሙ አሰልጣኙ ጠንካራውን የወላይታ ድቻ የተደራጀ እና ዕረፍት የለሽ የሆነ እንቅስቃሴ ሰብረው የበላይነት የወሰዱበት መንገድ የሚደነቅ ነበር። አሰልጣኝ አረጋይ ወንድሙ ከሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ጋር ተፎካክረው በጨዋታው በወሰዱት አሳማኝ ብልጫ ይህንን ምርጥ ቡድን እንዲመሩ አስችሏቸዋል።

ተጠባባቂዎች

ፔፔ ሰይዶ – ባህርዳር ከተማ
ቃልአብ ውብሸት – ሀዲያ ሆሳዕና
ዳዊት ማሞ – መቻል
ያሬድ ካሳየ – ኢትዮጵያ መድን
ከነዓን ማርክነህ – መቻል
በዛብህ መለዮ – ሲዳማ ቡና
ቻላቸው መንበሩ – ሻሸመኔ ከተማ
ያሬድ ዳርዛ – ኢትዮጵያ መድን