ከፍተኛ ሊግ | ይርጋጨፌ ቡና ድል ተቀዳጅቷል

በኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ ምክንያት ቀደም ብሎ በተደረገው የ 8ኛ ሣምንት ቀዳሚ ጨዋታ ይርጋጨፌ ቡና ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማን 2-0 ረቷል።

በኢትዮጵያ ዋንጫ ሦስተኛ ዙር ጨዋታ እሁድ 9፡30 ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ጨዋታ ለሚጠብቀው ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ሲባል ከተያዘለት መርሐግብር ቀደም ብሎ ዛሬ 03፡30 ላይ የይርጋጨፌ ቡና እና የኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ጨዋታ ተደርጓል።

ጥሩ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ኮልፌዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ ተጭነው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል። በዚህ እንቅስቃሴያቸውም 19ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ዋቸሞ ጳውሎስ ላይ በተሠራው ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት ዮናስ ወልዴ በግሩም ሁኔታ ቢመታውም በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል።

ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሲሞክሩ የነበሩት ይርጋጨፌዎችም 27ኛው ደቂቃ ላይ ባልተጠበቀ ሁኔታ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ጌታሁን ሸርኮ ከመሃል ሜዳ በአስደናቂ ሁኔታ አክርሮ የመታው ኳስ መረቡ ላይ አርፎ በውድድሩ ከታዩ ድንቅ ግቦች መሃል አንዱን ማስቆጠር ችሏል።

ግብ ከተቆጠረባቸው ከአስር ደቂቃዎች በኋላም የአቻነት ግብ ፍለጋ ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ኮልፌዎችም ተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ሲችሉ በተለይም በሁለት አጋጣሚዎች ከሚካኤል ዳኛቸው በተሻገሩ ኳሶች ፈታኝ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም ሳይጠቀሙባቸው ቀርተው ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።

ከዕረፍት መልስ በተሻለ የራስ መተማመን ጨዋታውን መቆጣጠር የቻሉት ይርጋጨፌዎች 62ኛው ደቂቃ ላይም አማኑኤል ከበደ ከግራ መስመር በተሻገረለት እና ባስቆጠረው ግብ መሪነታቸውን ማጠናከር ችለዋል።

ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር ባልተረጋጋ የማጥቃት እንቅስቃሴ እየተዳከሙ የሄዱት ኮልፌዎች 66ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። ፈቲ ረሃም ከሳጥን ውጪ ያደረገው ግሩም ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ ተመልሶበታል። በቀሪ ደቂቃዎችም ኮልፌ ቀራኒዮዎች የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ተጭነው ለመጫወት ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቶ ጨዋታው በይርጋጨፌ ቡና 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የምድቡ ቀሪ ጨዋታዎች በመጪው ሰኞ (ታኅሣሥ 15) እና ማክሰኞ(ታኅሣሥ 16)  ይካሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።