የኢትዮጵያ ዋንጫ | የሁለተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ዋንጫ ሦስተኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲደረጉ አርባምንጭ ከተማ እና አዳማ ከተማ ወደ ሩብ ፍጻሜው የተቀላቀሉበትን ድል አስመዝግበዋል።

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ባህር ዳር ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ሲገናኙ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ጥሩ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ የጣና ሞገዶቹ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ሲችሉ 27ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ሱሌይማን ትራኦሬ ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ፍጹም ጥላሁን ያደረገውን ሙከራ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነትም ዓባይነህ ፌኖ ተጨማሪ የግብ ዕድል አግኝቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

አርባምንጭ ከተማዎች በአጋማሹ የመጀመሪያውን ንጹህ የግብ ዕድላቸውን 41ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጥሩ አህመድ ሁሴን ይዞ በሚገባበት ሰዓት ጥፋት የተሠራበት በሚመስል መልኩ ኳሱን ሳይጠቀምበት ሲቀር ኳሱን በድጋሚ ያገኘው ሰለሞን ሀብቴ ያደረገውን ሙከራ የመሃል ተከላካዩ ፍሬዘር ካሳ በግንባሩ በመግጨት አግዶበታል።

ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች ተጭነው ለመጫወት ቢሞክሩም የግብ ዕድሎችን ግን መፍጠር አልቻሉም። 76ኛው ደቂቃ ላይም በባህር ዳር ከተማ በኩል ተቀይሮ የገባው ሀብታሙ ታደሰ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ሲቀር አርባምንጮችም አህመድ ሁሴንን ትኩረት ባደረጉ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ተስተውሏል።

መጠነኛ እና ብርቱ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ አዞዎቹ ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨመሩ ደቂቃዎች ውስጥ ባህር ዳር ከተማዎች ያገኙት የማዕዘን ምት በተከላካዮች ሲመለስ አህመድ ሁሴን ያስጀመረውን ግሩም የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ራሱ ወደ ግብነት ቀይሮ 1-0 በሆነ ውጤት መርታት ችለዋል። ውጤቱን ተከትሎም አርባምንጭ ከተማ ወደ ሩብ ፍጻሜው የተቀላቀለ ሦስተኛ ቡድን መሆኑን አረጋግጧል።

በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ቢሾፍቱ ከተማ እና አዳማ ከተማ ሲገናኙ ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ 20ኛው ደቂቃ ላይ አዳማዎች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ቢሾፍቱዎች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ሁለት ጥሩ የጎል ማስቆጠር እድል ቢያገኙም ሳይጠቀሙ የቀሩ ሲሆን በአንፃሩ አዳማዎች በመጀመርያ ዕድል ጎል ማግኘት ችለዋል። በዚህም በ20ኛው ደቂቃ ሀይደር ሸረፋ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል በመግባት የተቆጣጠረው አሸናፊ ኤልያስ በቀጥታ መትቶ አስቆጥሮታል።

በዚህ ጎል የተነቃቃው የአዳማ የማጥቃት ክፍል በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት ሁለት ፈታኝ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችሎ ነበር። ግብ ካስተናገዱ በኋላ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ መሻሻል ያሳዩት ቢሾፍቱዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ካደረጉት የማጥቃት እንቅስቃሴ ተጨማሪ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።

ከዕረፍት መልስ ብልጫውን የወሰዱት አዳማዎች 48ኛው ደቂቃ ላይ ቦና ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ሐይደር በግንባር ገጭቶ የግቡ ቋሚ ሲመልስበት ቦና በድጋሚ ለመቆጣጠር ሲሞክር ሳጥን ውስጥ በተሠራበት ጥፋት ያገኙትን የፍጹም ቅጣት ምት ራሱ ቦና ዓሊ አስቆጥሮት መሪነታቸውን አጠናክረዋል። አጥቂው 59ኛው ደቂቃ ላይም በዛሬው ጨዋታ በሁሉም ጎሎች ላይ ተሳትፎ ከነበረው ሀይደር ሸረፋ ከረጅም ርቀት የተሻገረለትን ኳስ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ በደረቱ አብርዶ በማመቻቸት ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ከራሳቸው የግብ ክልል ውስጥ ስኬታማ ቅብብሎችን ለማድረግ ይሞክሩ እንጂ ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ የተቸገሩት ቢሾፍቱዎች ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተሻሉ የጎል እድሎችን በመፍጠር 90ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ ፍቅሩ ዓለማየሁ ሳምሶን ኮልቻ ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት ሲሣይ አማረ በግሩም ሁኔታ መረቡ ላይ አሳርፎታል። ጨዋታውም በአዳማ ከተማ 3-1 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ አዳማ ወደ ሩብ ፍጻሜ የተቀላቀለ አራተኛ ቡድን ሆኗል።