አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ረዳታቸውን አሳውቀዋል

በቅርቡ የሲዳማ ቡና አሰልጣኝ የሆኑት ዘላለም ሽፈራው ምክትል አሰልጣኛቸውን ሾመዋል።

ሲዳማ ቡናን ለአንድ ዓመት በዋና አሰልጣኝነት ለማሰልጠን የተስማሙት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በትናንትናው ዕለት የእንኳን ደህና መጡ እና ከቡድኑ አባላት ጋር የትውውቅ መርሐግብር የተካሄደ ሲሆን አብረዋቸው የሚሠሩትን ምክትል አሰልጣኛቸውንም በይፋ አስተዋውቀዋል።


በምክትል አሰልጣኝነት ቡድኑን ያገለገሉት እና ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎችን በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት የመሩት አረጋዊ በርሄ ከቡድኑ ጋር መለያየታቸው ሲታወቅ በምትካቸውም አዲሴ ካሳ ረዳት አሰልጣኝ ሆነው መሾማቸው ታውቋል።

አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ከ1993 እስከ 2002 ድረስ ከአሰልጣኝ ከማል አህመድ ጋር ምክትል በመሆን አብረው መሥራት የቻሉ ሲሆን በእነዚህ ዓመታት ሀዋሳ ከተማ በ1996 እና 1999 የሊጉ ሻምፒዮን እንዲሁም በ1997 የጥሎ ማለፉ አሸናፊ ሲሆን በምክትልነት የቡድኑ አባል ነበሩ። ደቡብ ፖሊስን፣ በከፍተኛ ሊግ ወልቂጤ ከተማን ከመሩ በኋላ 2011 ወደ ሀዋሳ ከተማ በመመለስ በዋና አሰልጣኝነት ሲመሩ ቆይተው በከፍተኛ ሊግ ከፋ ቡና እና ቡታጅራ ከተማን ሲያሰለጥኑ በመቆየት አሁን የሲዳማ ቡና ምክትል በመሆን ሥራቸውን የሚጀምሩ ይሆናል።

በተያያዘ ዜና አሰልጣኝ ዘላለም በተጨማሪነት አንድ ረዳት አሰልጣኝ ወደ ቡድኑ ለማምጣት በሂደት ላይ መሆናቸው ያወቅን ሲሆን ጉዳዮ ሲጠናቀቅ የምናሳውቅ ይሆናል።