የኢትዮጵያ ዋንጫ መረጃዎች | የሦስተኛ ዙር አራተኛ ቀን ጨዋታዎች

የሦስተኛ ዙር የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ፍፃሜውን ያገኛል ፤ ጨዋታዎቹን አስመልክተን ያቀረብናቸውን መረጃዎች እነሆ !

ሀዋሳ ከተማ ከ መቻል

በሁለት የተለያየ ወቅታዊ አቋም የሚገኙ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ ሰባተኘውን አላፊ ቡድን ይለያል።

በሁለተኛው ዙር ዓአሊ ሱሌማን በተገኙ ሁለት ግቦች ቤንች ማጂ ቡናን ሁለት ለአንድ አሸንፈው ወደ ሦስተኛው ዙር የተሻገሩት ሀዋሳ ከተማዎች በፕሪምየር ሊጉ ከገጠማቸው ሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች ለማገገምና በውድድሩ ለመቀጠል መቻልን ይገጥማሉ። ሽንፈት በገጠማቸው የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ያስተናገደው ክለቡ አምስት ተከታታይ የሊግ ድል ካላቸው መቻሎች የሚገጥመው ፈተና ቀላል ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም።

መቻሎች በመጀመርያው ዙር ወልቂጤ ከተማን ሁለት ለባዶ በማሸነፍ ነበር ወደዚ ጨዋታ የበቁት። በነገው ዕለትም ባለፉት ዓመታት ክለቡ በተደጋጋሚ ጊዜ ያሳካውን የኢትዮጵያ ዋንጫ በድጋሜ ለማሸነፍ በሚያደርገው ጉዞ ሀዋሳ ከተማን ይገጥማል። በባህርዳር ከተማ ከደረሰባቸው ሽንፈት በኋላ ባደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች አምስት ተተከታታይ ድሎችና አንድ የአቻ ውጤት በማስመዝገብ በጥሩ የአሸናፊነት ጉዞ ያሉት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ውጤታማ ጉዟቸውም ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

የሦስተኛው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ በሁለት የሊግ ዕርከን የሚገኙትን የመዲናዋ ክለቦች ያገናኛል።

በቃልጌታ ምትኩ ብቸኛ ግብ ኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸንፈው ወደ ሦስተኛው ዙር የተሻገሩት ኮልፌ ቀራንዮዎች በከፍተኛ ሊጉ ከቀናት በፊት በይርጋጨፌ ቡና ከደረሰባቸው ሽንፈት መልስ ኢትዮጵያ ቡናን ይገጥማሉ። ኮልፌዎች በከፍተኛ ሊጉ በአራት ነጥቦች አስራ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፤ በነገው ዕለትም ወልድያ ከተማ ላይ አራት ግቦች ካስቆጠረው የኢትዮጵያ ቡና የማጥቃት ክፍል ጋር ይፋጠጣሉ።

ወልድያን በሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፈው ወደ ሦስተኛ ዙር የተሻገሩት ቡናማዎች ዛሬ በይፋዊ የሬዲዮ ፕሮግራማቸው ይፋ ባደረጉት መሰረት ከአሰልጣኝ ለውጥ በኋላ የመጀመርያው ጨዋታቸውን ነገ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በሰርብያዊው አሰልጣኝ ስር አምስት ድል አልባ የሊግ ጨዋታዎች ያሳለፉት ቡናማዎቹ በከፍተኛ ሊግ ሰንጠረዥ ግርጌ ከተቀመጠው ኮልፌ ቀራንዮ ከባድ ፈተና ይጠብቃቸዋል ተብሎ አይገመትም። ቡድኑ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ከሚያደርገው ጥረት በዘለለ ክለቡ በጊዜያዊ አሰልጣኝ እየተመራ ወደ ጨዋታው እንደመግባቱ በርካታ ትኩረት የሚስቡ ጉዳዮች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል፤ ከእነሱ ውስጥም አሰልጣኙ የሰርብያዊው አሰልጣኝ አጨዋወት እና የጨዋታ መንገድ ይዞ ይቀጥላል ወይስ ቡድኑ ቀድሞ ወደ ሚታወቅበት አጨዋወት ይመለሳል የሚለው ትኩረት ሳቢ ጉዳይ ነው።