የኢትዮጵያ ዋንጫ | በጎል በተንበሸበሸው የጨዋታ ቀን የጦና ንቦቹ እና ፈረሰኞቹ ድል አድርገዋል

የኢትዮጵያ ዋንጫ ሦስተኛ ዙር ዛሬም ቀጥሎ ሲውል ወላይታ ድቻ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ የ 5ለ2 ድል ተጋጣሚዎቻቸውን ረተዋል።

07፡30 ላይ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በተደረገው የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ሀዲያ ሆሳዕና እና ወላይታ ድቻ ሲገናኙ ጨዋታው ገና በሁለተኛ ደቂቃ ግብ ተቆጥሮበታል። ተከላካዮች ሲቀባበሉ በሠሩት ስህተት ኳስ ያገኘው ቢኒያም ፍቅሬ በግራ እግሩ መሬት ለመሬት የመታው ኳስ ግብ ሆኖ የጦና ንቦቹን መሪ ማድረግ ቢችልም በአስር ደቂቃዎች ልዩነት ግን ነብሮቹ ወደ መሪነት ተመልሰዋል። መለሰ ሚሻሞ 5ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ከተሰጠ የቅጣት ምት 13ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በግራ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ሳሙኤል ዮሐንስ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ሁለት ግቦችን በግንባሩ በመግጨት ማስቆጠር ችሏል። ብርቱ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታም ድቻዎች 29ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። አብነት ደምሴ ከግራ መስመር ባሻገረለት ኳስ ቢንያም ፍቅሬ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የግራ ቋሚ መልሶበታል።

ከዕረፍት መልስ ወላይታ ድቻዎች እጅግ ተሻሽለው በመቅረብ እና ፍጹም የበላይነት በመውሰድ አራት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል። በቅድሚያም 50ኛው ደቂቃ ላይ አብነት ደምሴ ረጅም ርቀት ላይ ከተገኘ የቅጣት ምት አክርሮ በመምታት ግሩም ግብ ማስቆጠር ሲችል 63ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ዮናታን ኤልያስ ከጸጋዬ ብርሃኑ ተሻግሮለት ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ የደረሰውን ኳስ በተረጋጋ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎት ቡድኑን ወደ መሪነት መልሷል።

ጨዋታውን መምራት ከጀመሩ በኋላም በተሻለ የራስ መተማመን ፈጣን የማጥቃት ሽግግሮችን ማድረጋቸውን የቀጠሉት የጦና ንቦች 75ኛው ደቂቃ ላይም መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ከራሳቸው የግብ ክልል በረጅሙ የተሻማውን ኳስ የሀዲያ ተከላካዮች ሳያጸዱት ቀርተው ኳስ የደረሰው ተቀይሮ የገባው ብሥራት ዓለሙ በሳጥኑ የግራ ክፍል ያስገባውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ግብ ጠባቂው ቢመልሰውም ኳሱን ያገኘው ቢኒያም ፍቅሬ በቀላሉ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር ከነበራቸው ግለት እየተቀዛቀዙ የሄዱት ሀዲያዎች ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመግባት ሲቸገሩ ይባስ ብሎም 78ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። ተቀይሮ የገባው ዘላለም አባተ ከቢኒያም ፍቅሬ የተቀበለውን ኳስ በግሩም ሁኔታ እየገፋ ወስዶ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ መሬት ለመሬት በመምታት ማስቆጠር ሲችል ጨዋታውም በወላይታ ድቻ 5ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ወላይታ ድቻ ወደ ሩብ ፍጻሜው የተቀላቀለ አምስተኛ ቡድን ሆኗል።

በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሻሸመኔ ከተማ ሲገናኙ ለተመልካች ማራኪ የሆነ እንቅስቃሴ በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ ፈረሠኞቹ ፍጹም የበላይነቱን መውሰድ ችለዋል። የጨዋታው የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራም 16ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ ቢኒያም በላይ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ሲወጣበት በሦስት ደቂቃዎች ልዩነትም ከዳዊት ተፈራ የተሻገረለትን ኳስ ከተከላካይ እና ግብ ጠባቂ ጋር ታግሎ ያሸነፈው አቤል ያለው ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ ተመልሶበታል።

ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ሲጫወቱ የነበሩት ሻሸመኔዎች 23ኛው ደቂቃ ላይ በመጀመሪያው የጠራ የግብ ዕድላቸው ግብ አስቆጥረዋል። አሸናፊ ጥሩነህ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው አብዱልቃድር ናስር ኳሱ ዓየር ላይ እንዳለ በግሩም አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል። ጊዮርጊሶች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ይበልጥ ማጠናከር ሲችሉ 27ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው አማኑኤል ተርፉ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ የግቡ አግዳሚ ሲመልስበት በአንድ ደቂቃ ልዩነትም ረመዳን የሱፍ ግሩም ሙከራ አድርጎ በተመሳሳይ በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል።

 

በየ ጥቂት ደቂቃዎች አስፈሪ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን የቀጠሉት ፈረሠኞቹ 29ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። በረከት ወልዴ ከረጅም ርቀት ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው አቤል ያለው ተገልብጦ በመምታት በድንቅ አጨራረስ አስቆጥሮታል። 38ኛው ደቂቃ ላይም ቢኒያም በላይ ከአቤል ያለው ጋር የተቀባበለው እና ከሳጥን አጠገብ አስደናቂ በሆነ ክህሎት የመታው ኳስ መረቡ ላይ አርፏል። የመጀመሪያው አጋማሽም በጊዮርጊስ 2-1 መሪነት ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል 53ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ያለው ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ መሬት ለመሬት በመምታት ያደረገውን ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ ሲመልስበት በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ግን ራሱ አቤል ያለው በተከላካይ ስህተት ያገኘውን ኳስ ከሳጥን አጠገብ በተረጋጋ አጨራረስ ግብ አድርጎት የፈረሠኞቹን መሪነት ማጠናከር ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ ተቀዛቅዘው ፍጹም ብልጫ የተወሰደባቸው ሻሸመኔዎች 66ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ተስፋዬ በግንባሩ ገጭቶት በግቡ የግራ ቋሚ ከወጣው ኳስ ተጨማሪ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ 73ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። ሄኖክ አዱኛ በግራ መስመር ከሳጥን አጠገብ የተገኘውን የቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

የመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች መጠነኛ ፉክክር ሲደረግባቸው 78ኛው ደቂቃ ላይ የሻሸመኔው አጥቂ አለን ካይዋ ከቅጣት ምት ግሩም ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርግም 83ኛው ደቂቃ ላይ ከሴኮንዶች በፊት ከሄኖክ አዱኛ የተሻገረለትን ኳስ አግኝቶ ሳይጠቀም የቀረው ተቀይሮ የገባው አማኑኤል ኤርቦ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን መካስ ሲችል ጨዋታው በፈረሠኞቹ 5-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሩብ ፍጻሜው የተቀላቀለ ስድስተኛ ቡድን መሆኑን አረጋግጧል።