ከፍተኛ ሊግ | በምድብ ለ በተደረጉ ጨዋታዎች ጋሞ ጨንቻ እና ደሴ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል

ስምንተኛ ሳምንት በመጀመሪያ ቀን በተደረጉ ሶስት ጨዋታዎች ሁለቱ በመሸናነፍ ሲጠናቀቁ አንዱ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተገባዷል።

አራት ሰዓት ሲል የጀመረው የ8ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ብዙ  የግብ ሙከራዎች ያልታዩበት እና ሁለቱም ቡድኖች የመከላከል ባህሪ ይዘው የገቡበት የመጀመሪያ አጋማሽ አስመልክቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ተሽሎ የገባው ካፋ ቡና በ61ኛው ደቂቃ ያገኙትን ቅጣት ምት እሸቱ መና ወደግብ አሻምቶ መታሰቢያ ገዛኸኝ ከተከላካይ መስመር በመሄድ በግንባር ገጭቶ ኳስና መረብ አገናኝቶ ቀዳሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

ካፋ ቡና በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ወደ አዲስ ከተማ ክፍለከተማ በምሄዱበት ቅፅበት የአዲስ ከተማው ተጫዋች አብዱሰላም አማን በካፋ ቡናው ተጫዋች በቃሉ ተካ ላይ ጥፋት ሰርቶ በ70ኛው ደቂቃ  የቀይ ካርድ ሰላባ  በመሆን ከሜዳ ወቷል።

በጎዶሎ ተጫዋቾች ከ20 ደቂቃ በላይ የተጫወተው አዲስ ከተማ ክፍለከተማ  ምንም ያህል በጎዶሎ ቢጫወትም አቻ ለመሆን ጠንከር ያለ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ተስተውሏል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ቀርተው እያለ ተቀይሮ የገባው አህመድ አብዶ ከመስመር በእራሱ ጥረት ኳስን እየገፋ በመሄድ 90ኛው ደቂቃ  ኳስና መረብ አገናኝቶ ጨዋታው 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ጫና የበዛበት የ8 ሰዓቱ ጨዋታ በጋሞ ጨንቻ በላይነት ሲጠናቀቅ ቦዲቲ ከተማ ጥሩ የኳስ ቁጥጥር አድርጎ  የግብ እድሎችን ሳይፈጥር ቀርቶ ሽንፈት አስተናግዷል። በመጀመሪያ አጋማሽ ተመጣጣኝ ጨዋታ በታየበተ በዚህ ጨዋታ በኳስ ቁጥጥር ቦዲቲ ከተማ ቢበልጥም ጋሞ ጨንቻ ያገኙትን እድል በመጠቀም በ17ኛው ደቂቃ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ ብልጠት በመጠቀም የፊት መስመር ተጫዋች ያሬድ መኮንን ወደግብነት ቀይሮ እረፍት 1 ለ0 እየመሩ መውጣት ችለዋል።

ወደጨዋታ ለመመለስ የተጫዋች ቅያሪ ያደረጉት ቦዲቲ ከተማዎች በተደጋጋሚ ግብ የሚሆኑ ኳሶችን አግንተው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። አስቆጪ የግብ ሙከራ የሚባለውም በ59 ደቂቃ በከዲር ዳንሳ አማካኝነት ያደረጉ ሲሆን ከቦክስ ውጪ በመሆን አክርሮ የመታት ኳስ የግቡ አግዳም መልሶበታል። እንዲሁም በ65ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ህዝቅኤል ከበረኛው ጋር ተገናኝቶ ኳሷን  ወደግብ ቢያሻግርም በድጋም የግብ አግዳም መልሶባቸዋል።

ውጤቱን ለማስጠበቅ በመከላከል የገቡት ጋሞ ጨንቻዎች በ69ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ተቀይሮ በገባው በተከላካያቸወ ጌታሁን ገዛኸኝ አማካኝነት ሁለተኛ ግብ በማስቆጠር መሪነታቸውን አጠናክረው 2 ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።

በሁለቱ ተጋጣሚ ቡድኖች መካከል ጥንቃቄ የሞላበት የቀኑ ማሳረጊያ የሆነው መርሐ-ግብር በደሴ ከተማ እና በወሎ ኮምቦልቻ መካከል ተደርጓል። የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች ጥሩ እንቅስቃሴ የታየ ሲሆን ግብ መሆኑ የሚችሉ ያለቁ ኳሶችን አግኝተው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።

ጨዋታ በጀመረ ገና በ5ኛው ደቂቃ የደሴ ከተማው አቡሽ ደርቤ በእርስ በርስ ቀብብሎሽ ጥሩ ኳስ አግንቶ የወሎ ኮምቦልቻው በረኛ አድኖበታል። ሌላኛው ግብ መሆን የሚችል ሙከራ በወሎ ኮምቦልቻ በኩል ሲደረግ ተጫዋች ተጎድቶባቸው በ30ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ማኑሄ ጌታቸው ከበረኛ ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀም ቀርቶ 0ለ0 በሆነ ውጤት ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጠንከር ብሎ የገቡት ደሴ ከተማዎች ሁለተኛ አጋማሽ እንደጀመረ በ49ኛው ደቂቃ አዲስ ግርማ እና ሙሉጌታ ካሳሁን በእርስ በርስ ቅብብሎሽ ኳስን ገፍተው በመሄድ ያገኙትን እድል ሙሉጌታ ካሳሁነ ወደግብነት ቀይሮ መሪ መሆን ችለዋል።

የአቻነት ግብ ፍለጋ በተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ የተስተዋሉት ወሎ ኮምቦልቻዎች መደበኛው የጨዋታ ክፍል ሊጠናቀቅ 2 ደቂቃ ሲቀረው ተቀይሮ የገባው ኦኒ ኡጁሉ የአቻነት ግብ አስቆጥሯል።

መደበኛው ደቂቃ ተጠናቆ ተጨማሪ በታየው ደቂቃ ሙሉጌታ ካሳሁን ግብ በማስቆጠር ደሴ ከተማ 2ለ1 አሸንፎ እንዲወጣ አስችሏል።