የሀምበሪቾ ዋና አሰልጣኝ ከቡድኑ ጋር አይገኙም

ሀምበሪቾን ባሳለፍነው ዓመት ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያሳደጉት አሰልጣኝ ከቡድኑ ጋር አብረው እንደማይገኙ ታውቋል።

በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሀምበሪቾ እንዲሳተፍ ያስቻሉት ዋና አሰልጣኙ ደጉ ዱባሞ ያለፉትን ስምንት ሳምንታት ቡድኑን ሲመሩ መቆየታቸው ይታወሳል። ይህን መረጃ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ በሁለቱም ወገኖች በኩል ያለውን እውነታ ለማወቅ ያደረግነው ጥረት ባይሳካልንም ከሰሞኑ የክለቡ አመራሮች እና አሰልጣኙ በስምምነት በሚለያዮበት ጉዳይ ዙርያ ውይይት ማድረጋቸውን ሰምተናል።

ይህን ተከትሎም ቡድኑ ለአንድ ሳምንት ከደሞዝ ጋር በተገናኘ ልምምድ አቋርጦ ቆይቶ ዛሬ የመጀመርያ ልምምዱን ረፋድ ላይ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ሲሰራ አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ አለመገኘታቸውን እና ከዚህም በኋላ ቡድኑን የመቀላቀላቸው ነገር ያከተመ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በዚህ መረጃ ዙርያ የሚኖሩ አዳዲስ ጉዳዮች ካሉ ተከታትለን የምናቀርብ ይሆናል።