ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | አርባምንጭ በግብ ልዩነት መሪነቱን ሲያስቀጥል ደሴ ከተማ አሸንፏል

ግቦች በበረከቱበት ዘጠነኛ ሳምንት የምድብ ለ ሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ተደርገው ደሴ ከተማ እና ወሎ ኮምቦልቻ ከመመራት ተነስተው ሲያንፉ ካፋ ቡና እና አርባምንጭ ከተማ ወሳኝ ድል አሳክተዋል።

5 ግቦች በተቆጠረቡት በረፋድ ሶስት ሰዓት ጨዋታ ደሴ ከተማ ባለቀ ደቂቃ ግብ አስቆጥሮ አሸንፏል። አምስቱም ግቦች በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠሩበት በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ወደሜዳ በመግባታቸው ኳስን ወደፊት ገፍተው ከመጫወት ይልቅ ወደኋላ አፈግፍገው በመከላከል ሲጫወቱ ተስተውለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ተሽሎ ለመገኘት ጥረት አድርገዋል። ቀድመው ቅያሪ ያደረጉት ደሴ ከተማዎች ከደብረብርሃን ከተማ የጨዋታ ብልጫ ቢወስዱም በ54ኛው ደቂቃ የደሴ ተጫዋቾች ኳስን እየገፉ ወደፊት ሄደው ሳይመልሱ ሲቀሩ ደብረብርሃኖች ያገኙትን እድል በሄኖክ አየለ አማካኝነት ወደግብነት ቀይረው መሪ መሆን ችለዋል። ነገር ግን በመሪነት የቆዩት ለአራት ደቂቃ ብቻ ነበር። በኳስ ቁጥጥር ተሽለው የተገኙት ደሴ ከተማዎች በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ በታየው በበሱፍቃድ ነጋሽ አማካኝነት የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል።

የአቻነት ግብ ከተቆጠረ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች በጥንቃቄ ሲጫወቱ የተስተዋሉ ሲሆን ለ20 ደቂቃዎች ያህል አስቆጪ የሚባል የግብ ሙከራ አላስመለከቱም። ተቀይሮ የገቡት አቡሸ ደርቤ እና  ሚካኤል ለማ በእርስ በእርስ ቅብብሎሽ ወደተቃራኒ ቡድን በሚሄዱበት ግዜ በአቡሽ ደርቤ ላይ የደብረብርሃን ተከላካዮች ጥፋት ሰርተውበት ቅጣት ምት ተሰቷቸዋል። በ82ኛው ደቂቃ የቆመ ኳስ ተፈሠ ሠርካ ወድግብ ክልል አሻምቶ ዘሪሁን ዐቢይ ኳስና መረብ አገናኝቶ ደሴ ከተማ መሪ መሆን ችለዋል።

ደሴ ከተማ 2ለ1 እየመራ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ግዜ አልቆ ተጨማሪ በታየው 6 ደቂቃ ውስጥ ሁለት ግቦች የተቆጠሩ ሲሆን በ90+3 ደቂቃ ላይ ኢዮብ አስራት የደሴ ከተማ ተከላካዮች የሰሩትን ሰህተት በመጠቀም ደብረብርሃን ከተማን አቻ አድርጓል።

ተጨማሪ ደቂቃ ሊያልቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ቀርተው እያለ በድጋሚ ደብረብርሃን ከተማዎች ጥፋት ሰርተው የቆመ ኳስ ለደሴ ከተማ ተስጥቷቸዋል።ያገኙትን ቅጣት  ምት ኳስ ከመስመር አከባቢ ታፈሰ ሰርካ አሻምቶ ዘሪሁን ዐቢይ ጭፎ ወዴግብነት ቀይሮ ጨዋታው 3ለ2 በሆነ ውጤት በደሴ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።

በማስከተል አምስት ሰዓት ላይ በተደረገው መርሃግብር 6 ግቦች ሲቆጠሩ ወሎ ኮምቦልቻ ከመመራት ተነስተው ቢሾፍቱ ከተማ ላይ የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ 4-2 አሸንፈዋል።

በመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በግብ ሙከራዎች ተሽለው የተገኙት ቢሾፍቱ ከተማዎች ግቦችን ለማስቆጠር በተደጋጋሚ ሙከራ አድርገዋል። በ27ኛው ደቂቃም እስጢፋኖስ ብርሃኑ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭተው በማስቆጠር ቢሾፍቱ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል።

ግብ ከቆጠረባቸው በኋላ ወደጨዋታ ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ወሎ ኮምቦልቻዎች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ ተስተውለዋል። በዚህም 43ኛው ደቂቃ ላዬ ዮሐንስ ኪሮስ በራሱ ጥረት ኳስና መረብ አገናኝቶ የመጀመሪያ አጋማሽ 1ለ1 በሆነ ውጤት እረፍት ወተዋል።

ወሎ ኮምቦልቻ ከመልበሻ ክፍል መልስ ፍፁም የጨዋታ በላይነት በመውሰድ ኳስን ተቆጣጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን በ58ኛው እና በ59ኛው ደቂቃ አከታትለው ግቦችን በማስቆጠር ተቃራኒ ቡድን ላይ ብልጫ ወስደዋል። በ58ኛው የጨዋታው ኮከብ የተባለው ቢላል ገመዳ ከፊት መስመር ተጫዋቻቸው ከማኑሄ ተስፋዬ ጋር በቅብብሎሽ ሄዶ 2ለ1 እንዲመሩ አስችሏል።

ቢሾፍቱ ከተማ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ መረጋጋት ተስኗቸው ተከላካዮቻቸው የሰሩትን ሰህተት በመጠቀም ዮሐንስ ኪሮስ በማስቆጠር ወሎ ኮምቦልቻ 3ለ1 እንዲመሩ አድርጓል። ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር ኳስን ወደፊት ገፍተው ሲጫወቱ የተስተዋሉት ወሎ ከምቦልቻዎች በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ግዜ ሊጠናቀቅ ሶስት ያህል ጨዋታዎች ቀርተው እያለ ተቀይሮ የገባው መልካሙ ፍንዱሬ አስቆጠሮ የወሎ ኮምቦልቻ መሪነቱን አጠናክሯል። ባለቀ ደቂቃ የቢሾፍቱ ከቸማው ጃፋር ከበደ በራሱ ጥረት ከቦክስ ውጪ ሆኖ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው 4ለ2 በወሎ ኮምቦልቻ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከሰዓት 8:00 ላይ በተደረገው መርሐ-ግብር ካፋ ቡና የካ ክ/ከተማን በጠባብ ውጤት አሸንፏል። ብዙም የግብ ሙከራዎች ባላስመለከተው በዚህ ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ መገባደጃ ላይ ግብ እስኪቆጠር ድረስ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ ሲያድርጉ ተመልክተናል።

በመጀመሪያ አጋማሽ መጠነኛ የጨዋታ ብልጫ የወሰደው ካፋ ቡና ከተቃራኒ ቡድነ አንፃር የተሻለ እንቅስቃሴ አድርጓል። የመጀመሪያ አርባ አምስት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል ሊመሩ ሲሉ የከፋ ቡና የፊት መስመር ተጫዋች እሸቱ መና ያሻገረለትን ኳስ ይዞ በመግባት ተከላካዮችን አታሎ በማለፍ ከበረኛ ጋር ተገናኝቶ እሱንም ሸውዶ በማለፍ ባስቆጠራት ድንቅ ግብ እረፍት እየመሩ እንዲወጡ አስችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ የካዎች የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ቢያደርጉም ውጤቱን ለማስጠበቅ ጠንካራ ሆኖ የዋለውን የካፋ ቡናን ተከላካይ ክፍል አልፎ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸዋል። ካፋ ቡና በበኩሉ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል እንዳለው ያስለመለከተ ጨዋታ የተየ ሲሆን በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠረ ብቸኛ ግብ ካፋ ቡና አሸናፊ በመሆን ደረጃውን አሻሽሏል።

የሳምንቱ ማሳጊረያ የአስር ሰዓቱ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ የምድብ መሪነቱን ለማስጠበቅ ኦሜድላ ላይ ብልጫ በመውሰድ ጫና ፈጥሮ የተጫወተ ሲሆን በሁለቱም አጋማሾች በተቆጠሩ ሁለት ግቦች ተጋጣሚውን 2-0 አሸንፏል።

በሁለቱም አጋማሽ የጨዋታ በላይነት የወሰዱት አዞዎቹ በግብ ክፍያ በልጦ የምድብ መሪነታቸውን ለማስጠበቅ በተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውለዋል። ተጋጣሚው ኦሜድላ በአንፃሩ ዛሬ ደካማ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን እምብዛም አስቆጪ የሚባል የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ አልተመለከትንም። ከተደጋጋሚ የግብ ሙከራ በኋላ በ28ኛው ደቂቃ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ ፍጥነት በመጠቀም የኦሜድላ ተከላካዮችን በማለፍ ወደቦክስ ውስጥ በመግባት ከበረኛው ጋር ተገናኝቶ ጠንከር ያለ ኳስ በመምታት ኳስና መረብ አገናኝቶ አርባምንጭ ከተማን መሪ አድርጎ እረፍት 1ለ0 እየመሩ ወተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽም ከተቃራኒው ቡድን ተሽለው የተመለሱት አርባምንጮች ከኳስ ቁጥጥርም ሆነ በግብ ሙከራዎች ከተቃራኒው ቡድን በልጠው ተገኝተዋል። በተለይም የመጀመሪያ ግብ ያስቆጠረው አህመድ ሁሴን በተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ሲያድርግ ተስተውሏል።

በ73ኛው ደቂቃ አህመድ ሁሴን በራሱ ጥረት ኳስን እየገፋ ወደ ሳጥን ውስጥ በመግባት የበረኛውን አቅጣጫ በማየት በቀላሉ አርባምንጭ ከተማ በግብ ክፍያ ልዩነት የምድብ መሪነቱ ያረጋገጠበትን ግብ አስቆጥሯል። ሁለተኛ ግብ ካስቆጠሩም በኋላ ተጨማሪ ግቦችን ፍለጋ ወደተቃራኒ ቡድን ሲሄዱ የተመለከትን ቢሆንም ግብ ሳያስቆጥሩ ቀርተው ጨዋታው 2-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።