ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ኢትዮ ኤሌክትሪክ መሪነቱን አጠናክሯል

በምድብ “ሀ” 9ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ተደርገው ጅማ አባጅፋር ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኦሮሚያ ፖሊስ ድል ሲቀናቸው ሞጆ ከተማ እና ወልዲያ ነጥብ ተጋርተዋል።

ረፋድ 3:30 ላይ የተደረገው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ስልጤ ወራቤን ከጅማ አባጅፋር አገናኝቶ ድንቅ ወቅታዊ አቋም ላይ የሚገኘው አባ ጅፋር ባለ ድል ሆኗል።

የመጀመሪያው አጋማሽ በጥሩ ሙከራዎች የታጀበ እና በሁለቱም ቡድኖች ጥሩ የሚባል ፉክክር አስመልክተውናል። በተለይም ከአሰልጣኝ ለውጥ በኋላ የተነቃቃው ስልጤ ወራቤ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን በ28ኛው ደቂቃ ከርቀት ያገኙትን የቅጣት ምት አስቻለው ኡታ አክርሮ በመምታት ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታውም በዚው ሁኔታ ቀጥሎ ጅማ አባጅፋር የአቻነቱን ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። መደበኛው አጋማሽ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ጅማ አባጅፋር ከመስመር ገለታ ኃይሉ ያሻገረውን ኳስ ልማደኛው ፊልሞን ገ/ፃድቅ በግንባር አስቆጥሮ በአቻ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ይበልጥ ተሻሽለው በመቅረብ ብርቱ ፉክክር አድርገዋል። በ54ኛው ደቂቃ የጨዋታው ኮከብ ሄኖክ ገ/ህይወት ከርቀት አክርሮ በመምታት በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ቀይሮ ጅማ አባ ጅፋርን መሪ ሲያደርግ ብዙም ሳይቆይ ስልጤ ወራቤ ግብ ለማስቆጠር በ58ኛው ደቂቃ ማቲያስ ኤልያስ ወደ የግብ ክልል ይዞ በመግባት ላይ የጅማ አባጅፋር ተከላካይ ልመንህ ጥፋት በመስራቱ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ማቲያስ ኤልያስ አስቆጥሯል። በ69ኛው ደቂቃ ደግሞ ጅማ አባጅፋር በጥሩ ቅብብል ፊልሞን ገ/ፃድቅ ወደ ግብ ሰብሮ ለመግባት ሲጥር በተሰራበት ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ፊልሞን ገ/ፃድቅ ያሸናፊነት ግብ አስቆጥሯል። ከግቡ መቆጠር በኋላ በሁለቱም ቡድኖች ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ምንም ግብ ሳይቆጠር በጅማ አባጅፋር 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከዚህ ጨዋታ በመቀጠል 5:30 ላይ በተደረገው መርሀግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ በጊዜያዊነት ወደለቀቀው መሪነት የተመለሰበትን የ1-0 ድል ይርጋ ጨፌ ቡና ላይ አስመዝግቧል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች መፈራራት በሚመስል መልኩ ቀዝቀዝ ያለ አጨዋወት እና ብዙ የግብ እድል ያልተመለከትንበት አጋማሽ ሆኗል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጥቂት ኳሶችን ወደ ግብ ለመውሰድ ጥረት ማድረጋቸው ተስተውሏል። በይርጋጨፌ ቡና በኩል የተቆራረጠ ኳስ እና ወደኋላ በማፈግፈግ ትኩረቱን መከላከል ላይ አድርገዋል። አጋማሹም በዚው ውጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጥሩ በመነቃቃት ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። በዚህም በ55ኛው ደቂቃ በፈጣን ቅብብል ወደ ይርጋጨፌ የግብ ክልል በመግባት በተሰራበት ጥፋት ያገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ቢንያም ካሳሁን ወደ ግብ ቀይሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ይርጋጨፌ ቡና ግብ ለማስቆጠር ጥረት ያደረገ ቢሆንም የኢትዮ ኤሌክትሪክን የተከላካይ ክፍል ማለፍ ተስኖት ጨዋታውን በሽንፈት አጠናቋል።

ቀን 7:30 ላይ የተደረገው ሶስተኛ ጨዋታ ሞጆ ከተማን ከወልዲያ አገናኝቶ ያለግብ ተጠናቋል። የመጀመሪያ አጋማሽ ወልዲያዎች በኳስ ቁጥጥር እና ተጋጣሚ ቡድን ላይ ጫና በመፍጠር ተሽለው ተገኝተዋል። በአንፃሩ ሞጆ ከተማ የሚያገኘውን ኳስ በመልሶ ማጥቃት የግብ እድል ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። ሆኖም ያን ያህል ግልፅ የግብ እድል ሳይፈጠር አጋማሹ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ለመሸናነፍ ከፍተኛ ፉክክር አድርገዋል። ወልድያ ከተማ ጨዋታውን ድል ለማድረግ ከፍተኛ የሆነ ጫና ያሳደሩ ቢሆንም ሞጆ ከተማ የተከላካይ ስፍራቸውን በማደራጀት ምንም ግብ ሳያስተናግዱ ጨዋታው ተጠናቋል።

በዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ 9:30 ላይ ጅማ አባቡናን ከኦሮሚያ ፖሊስ አገናኝቶ ኦሮሚያ ፖሊስ 3-2 አሸንፏል። ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ በፈጣን አጨዋወት ጥሩ ጥሩ የግብ እድል ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ የተስተዋለ ሲሆን በ10ኛው ደቂቃ የኦሮሚያ ፖሊስ ተጫዋች ዳንኤል ዳርጌ ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ዳንኤል ዳርጌ ወደ ግብ ቀይሮታል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ጅማ አባጅፋር ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ይህንን ተከትሎ በ32ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ዮሐንስ ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት እስጢፋኖስ ተማም ማስቆጠር ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ጅማ አባቡና ጥሩ የግብ እድል አግኝቶ ጴጥሮስ ገዛኸኝ ወደ ግብ ሲመታው የግቡን ቋሚ መቶ የተመለሰውን ኳስ እስጢፋኖስ ተማም መልሶ የመታው ኳስ ከጨዋታ ውጪ በሚመስል መልኩ በተዘናጉበት ሰአት በ37ኛው ደቂቃ ኦሮሚያ ፖሊስ በመልሶ ማጥቃት ይዞ ሄዶ ኤፍሬም ቤኃም አስቆጥሮ ዳግም ቡድኑን መሪ አድርጓል። መደበኛው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ የጅማ አባቡና ተጫዋች የሆነው ግሩም ብሩጌታ በራሱ ጥረት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ተከላካይ እና ግብ ጠባቂ በማለፍ አስቆጥሮ ቡድኑን በአቻ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል እንዲሄድ አርጓል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማ አባቡና ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው ተጫውተዋል። ሆኖም የተከላካይ ስፍራውን አጠናክሮ የገባው ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ የሚያገኘውን ኳስ በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ጨዋታውም በዚው አጨዋወት ቀጥሎ በ80ኛው ደቂቃ የኦሮሚያ ፖሊስ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ሄኖክ ፍቃዱ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂ ሲመልሰው ዳንኤል ዳርጌ የማሸነፊያውን ግብ አስቆጥሯል።