መረጃዎች | 34ኛ የጨዋታ ቀን

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሳምንታት በኋላ ሲመለስ የዘጠነኛው ሳምንት መክፈቻ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ኢትዮጵያ መድን ከ ሲዳማ ቡና

ሊጉ ከሳምንታት ድል አልባ ጉዞ በኋላ በመጨረሻው ሳምንት ድል ያስመዘገቡት ሁለት ቡድኖች በማገናኘት ይጀምራል።

በመጀመርያው ሳምንት ባህር ዳር ከተማ ላይ ከተቀዳጁት ድል በኋላ ስድስት ድል አልባ ሳምንታት ያሳለፉት መድኖች ሀምበሪቾን ሁለት ለባዶ አሸንፈው ወደ ድል ተመልሰዋል። መድኖች ከድል ጋር በተራራቁባቸው ስድስት ጨዋታዎች ሦስት የአቻና ሦስት ሽንፈቶች አስመዝግበዋል። ቡድኑ በተጠቀሱት ጨዋታዎች ጥሩ የመከላከል አቅም ቢያሳይም ከፍተኛ የሆነ የግብ ማስቆጠር ችግር ታይቶበታል፤ በስድስት ጨዋታዎችም ሦስት ግቦች ብቻ ነበር ያስመዘገቡት። ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ሀምርሪቾ ላይ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር የቻለው የማጥቃት አጨዋወት ጥንካሬ ማስቀጠልም የአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ትልቁ የቤት ስራ ነው። በውድድር ዓመቱ በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ ከአንድ ግብ በላይ የተቆጠረበት የተከላካይ አደረጃጀትም የቡድኑ ጠንካራው ጎን ነው።

ዘላለም ሽፈራውን በዋና አሰልጣኝነት የቀጠሩት ሲዳማ ቡናዎች በስምንት ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። እንደ ተጋጣምያቸው በተመሳሳይ በውድድር ዓመቱ ሁለት ድሎች ብቻ ያስመዘገቡት ሲዳማ ቡናዎች በመጨረሻው ሳምንት ላይ ሳይጠበቁ ወላይታ ድቻ ላይ አራት ግቦች አስቆጥረው ካሸነፉ በኋላ ደረጃቸውን ለማሻሻል መድንን ይገጥማሉ። ባለፉት ዓመታት ባሰለጠኗቸው ክለቦች በተከተሉት የአጨዋወት ዘይቤ መሰረት መከላከል ላይ ያዘነበለ አጨዋወት ይከተላሉ ተብለው የሚጠበቁት አዲሱ አሰልጣኝ ከስምንቱ ጨዋታዎች በአምስቱ ግብ ሳያስቆጥር የወጣውን የቡድኑ ደካማ የማጥቃት አጨዋወት ላይ ለውጥ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። አሰልጣኙ ሊጉ በተቋረጠበት ወቅት በቂ የመዘጋጃ ጊዜ እንደ ማግኘነታቸው ቡድኑ ላይ በርካታ ለውጦች ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በስምንት ጨዋታዎች በአማካይ አንድ ግብ ያስተናገደው የተከላካይ መስመርም በአሰልጣኙ ስር ይበልጥ ይጎለብታል ተብሎ ይታመናል።

በኢትዮጵያ መድን በኩል ረዘም ላዘ ጊዜ በጉዳት ከራቀው ሀቢብ ከማል በስተቀር ሁሉም ተጫዋቾች ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። በሲዳማ ቡናዎች በኩልም ደስታ ዮሐንስ ብቻ በጉዳት ዝርዝር ውስጥ ተካቷል።

ባለፈው የውድድር ዓመት ባካሄዷቸው ሁለት ጨዋታዎች ላይ ሦስት ቀይ ካርዶች የተመዘዙበት ጨዋታ በኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ዋና ዳኝነት ይመራል። ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እና ሲራጅ ኑርበገን በረዳት ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሠ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ በመሆን በጋራ ጨዋታውን ይመሩታል።

አዳማ ከተማ ከ ሀድያ ሆሳዕና

ባለፉት ሦስት ዓመታት ግንኙነታቸው ላይ በርካታ የአቻ ውጤቶች የተመዘገበበት ጨዋታ ነገ ምሽት ይከናወናል።

ከስድስት ሽንፈት አልባ ጨዋታዎች በኋላ በተከታታይ የሽንፈትና የአቻ ውጤቶች ያስመዘገቡት አዳማ ከተማዎች ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ሀድያን ይገጥማሉ። አዳማዎች በመቻል ከገጠማቸው ሽንፈት በፊት ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች በአማካይ ሁለት ግቦች በማስቆጠር ጥሩ ብቃት ላይ የነበረው የማጥቃት አጨዋወታቸው ጥንካሬ የመመለስ ስራ ይጠብቃቸዋል። ቡድኑ ምንም እንኳ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ላይም ሁለት ግቦች ብያስቆጥርም የቀደመው ዕድሎች ወደ ግብነት የመቀየር ስልነቱ ግን በውስን መልኩ ቀንሷል። በነገው ጨዋታም በሊጉ ጥቂት ግቦች ብቻ በማስተናገድ በሁለተኛ ደረጃነት ላይ የተቀመጠው ቡድን እንደመግጠማቸው ፈተናው ቀላል አይሆንላቸውም።

በሰባተኛ ሳምንት ከወራጅ ቀጠናው የወጡበት ድል ያስመዘገቡት ሀድያ ሆሳዕናዎች በስምንት ነጥቦች በ13ኛ ደረጃነት ተቀምጠዋል። ሀድያዎች በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ግብ ሳያስቆጥሩ ከወጡ በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ሦስት ግቦች በማስቆጠር መጠነኛ መሻሻል አሳይተዋል። በተለይም ፋሲል ከነማ ላይ ያስመዘገቡት የውድድር ዓመቱ ብቸኛ ድል የቡድኑ መሻሻል አንዱ ማሳያ ነው። ቡድኑ ከወልቂጤና ሀምበሪቾ ቀጥሎ ጥቂት ግቦች ያስቆጠረ ቡድን ቢሆንም በመከላከሉ ረገድ ግን ከሊጉ ምርጥ የመከላከል አደረጃጀት ካላቸው ቡድኖች አንዱ ነው። የአሰልጣኘት መንበሩ ከተረከቡ በኋላ በጎ ለውጦች ያመጡት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ላይ ውስን ለውጦች ማድረግ ቢችሉም አሁንም የቡድኑ ሚዛን ላይ ማስተካከያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በተለይም ፋሲል ከነማን ባሸነፉበት ጨዋታ ላይ የፊት መስመር ተጫዋቾቻቸው በጥልቀት ወደ ኋላ ተስበው በመከላከሉ ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ በመወሰናቸው የማጥቃት አጨዋወታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል፤ ይህንን የቡድን ሚዛን መፋለስ ማስተካከል ይኖርባቸዋል።

በአዳማ ከተማ በኩል ግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ እና አድናን ረሻድ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ አማካዩ ቻርልስ ሪባኑ ደግሞ በግል ምክንያት ከነገው ስብስብ ውጭ ይሆናል። በሀድያ ሆሳዕና በኩልም ዳዋ ሆቴሳ በቤተሰብ ችግር ምክንያት፤ ሔኖክ አርፊጮ እና ካሌብ በየነ በጉዳት አይኖሩም ተመስገን ብርሀኑ እና ብሩክ ማርቆስም መሰለፋቸው አጠራጣሪ ነው።

በዋና ዳኝነት አባይነህ ሙላት በረዳትነት ዳኝነት ለዓለም ዋሲሁን እና ኤልያስ መኮንን ዳንኤል ግርማይ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ጨዋታውን ይመሩታል።