የመጀመሪያውን የስፖርት ባዛርና ኤግዚቢሽን አስመልክቶ መግለጫ ተሰጥቷል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የሚሳተፉበትን የመጀመሪያው የስፖርት ባዛር እና ኤግዚቢሽን አስመልክቶ ዛሬ በሳፋየር አዲስ ሆቴል መግለጫ ተሰጥቷል።

የአዲስ አበባ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ከበርኖስ ማስታወቂያ እና ኢንተርቴይመንት ጋር በመተባበር 16ቱም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የሚሳተፉበት የመጀመሪያውን የስፖርት ባዛር እና ኤግዚቢሽን አስመልክቶ ዛሬ ታኅሣሥ 23/2016 ረፋድ 4 ሰዓት ላይ በሳፋየር አዲስ ሆቴል መግለጫ ተሰጥቷል።

ከአዲስ አበባ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ አቶ እንግዳወርቅ ዳንኤል ከበርኖስ ማስታወቂያ እና ኢንተርቴይመንት ድርጅት ደግሞ መስራች እና ባለቤቷ ወይዘሮ ብሩክታዊት ላቀው ተገኝተዋል።

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አቶ እንግዳወርቅ ዳንኤል ስለተዘጋጀው ፌስቲቫል ሲናገሩ በዓይነቱ እና በይዘቱ ለየት ያለ የተባለለት ፕሮግራም በሁሉም የስፖርት ዓይነት ውስጥ ያሉ ክለቦች የልምድ ተሞክሮ የሚካፈሉበት ፣ በአንድነት እና በወንድማማችነት ስሜትም አብሮነታቸውን የሚያጠናክሩበት መድረክ መሆኑ ሲገለጽ ለምሳሌ ያህልም በእግርኳስ ፣ በአትሌቲክስ ፣ ቦክስ ፣ ብስክሌት ፣ ማርሻል አርት እና የመሳሰሉት ወድድሮች ላይ የሚሳተፉ ክለቦች የየራሳቸው ቦታ ተዘጋጅቶላቸው ከአጀማመራቸው ጀምሮ አሁን እስከ ደረሱበት ደረጃ ያለውን ሂደት የሚገልጹበት አውደርዕይ እንደተመቻቸላቸው ታውቋል።

በመቀጠል ንግግር ያደረጉት ወ/ሮ ብሩክታዊት በበኩላቸው በርኖስ የማስታወቂያ እና ኢንተርቴይመንት ድርጅት ከተመሠረተ ስድስት (6) ዓመታት ማስቆጠሩትን ገልጸው በተለያዩ ከተሞች ባዛር እና ኮንሰርት በዋና ከተማዋም ብዙ የሚኒስትሮች መድረኮችን ማዘጋጀቱን በመጠቆም ሰላሳ ስድስት (36) የስፖርት ፌዴሬሽኖችን እና አሥራ ስድስት(16) የፕሪሚየር ሊግ ክለቦችን የሚያሳትፈው የስፖርት ፌስቲቫል ከየካቲት 8 እስከ የካቲት 10 ለሦስት ቀናት ያህል ሊደረግ መታሰቡን አሳውቀዋል። ኃላፊዋ አክለውም ሁሉም ክለቦች በተዘጋጀላቸው አውደርዕይ የምሥረታ ቀናቸውን ፣ ሙሉ ታሪካቸውን ፤ ከተለያዩ ብሔሮች እንደመምጣታቸው ደግሞ ባሕል እና እሴቶቻቸውን ማለትም ምግብ ፣ መጠጥ ፣ አልባሳት ለማስተዋወቅ የሚያስችላቸው ሦስቱንም ትውልድ የሚያገናኝ አጋጣሚ መሆኑን በመናገር ክለቦች የራሳቸውን ንብረት የሚሸጡበት ፣ የስፖርት ትጥቅ አምራቾች ምርታቸውን የሚያስተዋዉቁበት ዕድል መመቻቸቱን ገልጸው ለህጻናትም የተለየ ምቹ ቦታ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

በዕለቱ ከአውደርዕዩ በተጨማሪ ሁሉም ተሳታፊ ከተመልካችነት በላይ የሚሳተፍባቸው የስፖርት ክንውኖች ፣ የዳንስ ፊትነስ እና የመዝናኛ ፕሮግራም መዘጋጀቱ የታወቀ ሲሆን ሁሉም 16ቱም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ለመሳተፍ ማረጋገጫ መስጠታቸውን እና በቂ ቦታ እየተዘጋጀ መሆኑንም አዘጋጆቹ ተናግረዋል። ሆኖም ቀኑ ሲቃረብ ተጨማሪ አጠቃላይ መግለጫ እንደሚሰጥ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለት ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች መልሶችን ሲሰጡ በተለይም ኤግዚቢሽን ማዕከል ለሁሉም ተመራጭ ቦታ መሆኑን እና የየክለባቸው ምልክት የሆኑ የፕሪሚየር ሊጉ ተጫዋቾች በጨዋታዎች መካከል በሚኖራቸው ጥቂት ቀን እንዲመጡ የማመቻት ሥራ እንደሚሠሩ እና የፊርማው ሥነ ስርዓት ይዘግይ እንጂ በሁለቱም ተቋማት መካከል ሠፊ ሥራዎች ሲሠሩ እንደነበር ሀሳባቸውን ሰጥተው በፕሮግራሙ ላይ ከ 50 ሺህ ያላነሱ ታዳሚዎች እንደሚገኙ ግምታቸውን ማስቀመጣቸውን እና ለክለቦችም ክፍያ እንደማይጠይቁ አሳውቀው ለሚዲያዎችም ቦታ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በመጨረሻም በአዲስ አበባ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ እንዲሁም በበርኖስ ማስታወቂያ እና ኢንተርቴይመንት ድርጅት መካከል በየ ሦስት ዓመቱ የሚታደስ ይፋዊ የስምምነት ፊርማ ተደርጎ መርሐግብሩ ተጠናቋል።