የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 1-2 ኢትዮጵያ ቡና


“ተጫዋቾቻችን ትዕግስተኛ ነበሩ እና እስከ መጨረሻው ጠብቀን ውጤት አግኝተናል” አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ

“ሦስቱን ጨዋታ መሸነፋችን ለዛሬው ትልቅ ተፅዕኖ ፈጥሮብናል ብዬ አምናለሁ” አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ

በመስፍን ታፈሠ ሁለት ግቦች ኢትዮጵያ ቡና 2ለ1 በሆነ ውጤት ሀዋሳ ከተማን ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቃለ ምልልስን አድርገዋል።

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ጥሩ ፉክክር ተደርጎበት ሽንፈት ስላስተናገዱበት ጨዋታ…

“እንደ ቡድን ዛሬ ከዕረፍት በፊትም ከዕረፍት በኋላም የተደረገው ነገር ጥሩ ነው። ውጤት አለመኖሩ ያሳዝናል እንደዛም ሆኖ ብዙ ኳሶችን አንግሎች የሚመልሷቸው ነበሩ ቢያንስ ሁለት ለባዶ ሦስት ለባዶ መምራት የምንችልበት ነውና ከዛም ከዕረፍት በኋላም ጎሉ ከገባብን በኋላም አግኝተናል ባለ መረጋጋት ምክንያት አምክነናል። ዞሮ ዞሮ በእንቅስቃሴ እጅግ በጣም አሪፍ ነው በጣም ተሻሽለን ቀርበናል ፣ ጥሎ ማለፍ ጨዋታ የነበረውን ይዘት አስቀጥለናል ፣ ያው ቀይ ካርዶች ዋጋ አስከፍሎናል እውነት ለመናገር ምክንያቱም ሁለተኛ ጎል የገባብን ልጁ በቀይ ካርድ ከወጣ በኋላ ስለሆነ በዛውም ፓዚሽን ላይ ስለሆነ ቀይ ካርዶቹ ዋጋ አስከፍለውናል። እግር ኳስ ነው እንቀበለዋለን።”

መድሀኔ ብርሀኔ በቀይ ከወጣ በኋላ የተደረገው ቅያሪ ዘግይቷል ማለት ይቻላል ጎሉ በእርሱ መስመር በመቆጠሩ…

“አልዘገየንም ፣ ምክንያቱም አሁን በሦስት ተከላካይ ለመጫወት አስበን አንስተናል ግን ኳሱ እኛ የቆመ ኳስ ለመጠቀም በሄድበት ነው በመልሶ ማጥቃት ኳሱ የመጣው እና ቢሄድም የቆመ ኳስ ተመልሶ ስለመጣ በቅያሪው አይደለም ፣ ብንቀይርም ሦስት ተከላካይ ነው ያደረግነው ምክንያቱም ፉልባክ አስወጥተን ሦስት ተከላካይ ነው ከዛ በኋላም ተቆጣጥረነዋል። በቆሙ ኳሶች መልሶ ማጥቃትን ያለ መጠበቃችን እና የበረኛችን አወጣጥ ታይሚንጉን የጠበቀ ስላልሆነ ባይወጣ እንደውም ጎሉ ላይገባ ይችላል ምክንያቱም ተከላካዩ ሮጦ ደርሷል ፣ አንዳንዴ ትጠብቃለህ እንደዚህ አይነት ስህተቶች ይፈጠራሉ ፣ በረኛው ያቺን ታይሚንግ ቢጠብቅ እና ቢቆም ኖሮ ጎሉም ላይገባ ይችላል አንዳንዴ ይከሰታል ብዬ አስባለሁ።”

አራት ተከታታይ ሽንፈትን ክለቡ ማስተናገዱ እና ቡድኑ ስላጣው ነገር…

“ሦስት መደዳውን ከተሸነፍን በኋላ ጥሎ ማለፍ ተጫውተን አሸንፈን ወደ አሸናፊነት ተመልሰናል። አንደኛ የምናገኛቸው ተጋጣሚ ቡድኖች እጅግ በጣም ነጥብ የሚፈልጉ እንደኛ እጅግ ጠንካራ ሊጉ ላይ ትልቅ ልምድ ያላቸው ጠንካራ ቡድኖች ናቸው። በዛው ልክ ነው ጫናውም አንድ ስትሸነፍ ሁለተኛውም ላይ ሙሉ ኮንፊደንስ አይኖርህም እነዚህ ሽንፈቶች ሲደጋገሙ በስነ ልቦናው ትንሽ ትወርዳለህ። ስነ ልቦናው ትንሽ ጎድቶናል ብዬ አስባለሁ ፣ ሦስቱን ጨዋታ መሸነፋችን ለዛሬው ትልቅ ተፅዕኖ ፈጥሮብናል ብዬ አምናለሁ ግን እግር ኳስ ነው ገና ነው። ስለዚህ ብዙ ነገር መቀየር ይቻላል ትልቁ ነገር ቡድን እንደ ቡድን ሲጫወት ነው ፣ እንደ ቡድን በጣም ያማረ እግር ኳስ ተጫውቷል ፣ ብዙ ጎሎችን አመከንን እንጂ ወደ ጎል ደርሰናል ያለ መጠቀም ችግር እንጂ የተሻልን ነበርን ፣ ከእነርሱ ጥርት ያለ ኳስ በመድረስ ማለት ነው ስለዚህ ቀጣይ ያሉትን ጨዋታዎች አስተካክለን ቡድናችንን ወደ ነበረበት እንመልሳለን።”

አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለ ሁለቱ አርባ አምስት ደቂቃዎች…

“በጣም ጥሩ ነበር። መጀመሪያ ተጋጣሚያችን ሜዳው ላይ በቁጥር በዝቶ ለመከላከል ዘግቶብን ነበር ነገር ግን በዛው ልክ ተጫዋቾቻችን ትዕግስተኛ ነበሩ እና እስከ መጨረሻው ጠብቀን ውጤት አግኝተናል ፣ መምራትም ጀምረናል ከዛ በኋላ ግን ጨዋታውን ለመቆጣጠር ነበር የሞከርነው ወዲያው ከዕረፍት እንደተመለስን ተመልሰዋል ፣ ዕርግጠኛ ነበርኩኝ የነበረው ሂደት ተጫዋቾቼ ጋር የነበረው እንቅስቃሴ በጣም ጥሩ ስለነበረ መመለስ እንደምንችል ዕርግጠኛም ነበርኩ እና ከዛ አንፃር በጣም ጥሩ ነበር። ዛሬ ተጫዋቾቻችን ቢያንስ የሚችሉትን ነገር ከፍለዋል ሜዳ ላይ።”

በሸገር ደርቢም በዛሬው ጨዋታ ቡድኑ ላይ ስላለው ከፍተኛ መነቃቃት…

“አንደኛ ተጫዋቾቹ በራስ መተማመናቸው እንዲያሳድጉ ትልቁ እኔ የሰራሁት ነገር ፣ ሁለተኛ የቡድን ስፕሪታችን ከፍ ማድረግ ፣ ሦስተኛ ደግሞ ጨዋታዎችን ተጫዋቾች ባላቸው አቅም መሄድ አለብኝ ብዬ ስላሰብኩኝ በይበልጥ በልጆቹ አቅም ተመርኩዘን ነው እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ የሞከርነው ፐርፌክት አይደለም ፣ ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ ነው ያንን እያሳደግን መሄድ ነው የምንፈልገው።”

ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የነበሩ የጎል ዕድሎች ወደ ግብነት ያለ መቀየር ውስንነት መታየቱ…

“አሁንም ከጉጉት ነው። አሁንም አንዳንድ የተወሰኑ ተጫዋቾችን ከጨዋታው በኋላ ሳይ በመሳታቸው ቁጭት ውስጥ ናቸው ነገር ግን ይመጣል ፣ ዋናው እያሸነፍን የራስ መተማመናችንን ከፍ እያደረግን ወጣቶች ናቸው ብዙ የልምድ ማነስ አለ ጨዋታዎችን እያሸነፍን ስንሄድ በዛ ልክ ይስተካከላል ብዬ አስባለሁ።”

የብሩክ በየነ የፍፁም ቅጣት ምት መቺነት ወደ መስፍን ታፈሠ መዞሩ…

“ምንም ሌላ ነገር ሳይሆን ብሩክን ከጫና ነፃ ለማድረግ ታስቦ እንጂ ብሩክ ጥሩ መቺ እንደሆነ ይታወቃል ነገር ግን ከጫና እርሱን ነፃ ለማድረግ ስለፈለኩኝ ከእርሱ ጋር ተነጋግረን ተወያይተን ያደረግነው ነው። ጫና ውስጥ ስለሆነ ተደጋጋሚ ስላሳተ ያንን ጫና ከእርሱ ላይ ለመቀነስ የታሰበ ነው።”