ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥብ ቢጥልም ወደ መሪነቱ ተመልሷል

በምድብ ‘ሀ’ 10ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ተደርገው ሀላባ ከተማ ድል ሲቀናው ቀሪ ሶስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

ረፋድ 3:30 ላይ የተደረገው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ነቀምት ከተማ ከሀላባ ከተማን አገናኝቶ ሀላባ ከተማ ጨዋታውን በጠባብ ውጤት አሸንፏል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ አስመልክተውናል። ሀላባ ከተማ በተደጋጋሚ በአጭር ቅብብል ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ሲያረጉ በነቀምት ከተማ በኩል ደግሞ የሚቆራረጡ ኳሶች በብዛት የተመለከትንበት ነበር።ሀላባ ከተማዎች በአጋማሹ ጥሩ ጥሩ የግብ እድሎች መፍጠር ቢችሉም በአጥቂ መስመራቸው ደካማ አጨራረስ የተነሳ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ነቀምት ከተማ ራሱን በማጠናከር የሀላባ ከተማን ጫና ለመቆጣጠር ጥረት ያደረጉ ሲሆን በዚህም አጋማሹ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።

በሁለተኛ አጋማሽ ሀላባ ከተማዎች እንደ መጀመሪያ ሁሉ ጫና ፈጥረው ለመጫወት የሞከረ ሲሆን በአንፃሩ ነቀምቶች ወደ ራሳቸው የግብ አፈግፍገው በመልሶ ማጥቃት ወደ ተቃራኒ ግብ ለመድረስ ሲሞክሩ አስተውለናል። በ55ኛው ደቂቃ የሀላባ ከተማው ከማል አቶም ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ኦካይ ጁል አስቆጥሮ ወደ ቡድኑን መሪ አድርጓል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ነቀምት ከተማ በተደጋጋሚ የአቻነቷን ግብ ፍለጋ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን ነገርግን የሀላባ ከተማን ጠንካራ የመከላከል መስመር መስበር ተስኗቸዋል። በ71ኛው ደቂቃ የነቀምት ከተማ ተጫዋች የሆነው ሮበርት ሱላሉ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲሰናበት ጨዋታውም በሀላባ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ሀላባ ነጥቡን ከፍ በማድረግ ደረጃውን ወደ ስድስተኛ አሳድጓል።

ከዚህ ጨዋታ በመቀጠል 5:30 ላይ በተደረገው መርሀግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥብ ቢጋራም በግብ ክፍያ ብልጫ ወደ ምድቡ መሪነት ግን ተመልሷል።

ቤንች ማጂ ቡናን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ያገናኘው ይህ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር ቤንች ማጂ ቡና ተሽለው ታይተዋል። በአንፃሩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ኳስን በመንጠቅ በፈጣን ቅብብል ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት አድርገዋል።

በ10ኛው ደቂቃ የኢትዮ ኤሌክትሪክ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው ያሬድ ብርሀኑ በተቃራኒ የግብ ክልል አቅራቢያ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ቢመታውም ኳሱ ኢላማውን ሳይጠብቅ ለጥቂት የወጣበት ኳስ የአጋማሹ ብቸኛ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በኩል የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ራሳቸውን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት ያደረጉበት ነበር። ቤንች ማጂ ቡና ወደ ግብ በመድረስ እና በኳስ ቁጥጥር ተሽለው በተገኙበት በዚሁ አጋማሽ በ64ኛው ደቂቃ አብዱል አዚዝ አህመድ ለሀሰን ሁሴን ያቀበለውን ግልፅ የግብ እድል ወደ ውጭ በማውጣት ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በተመሳሳይ ቤንች ማጂ ቡናዎች በ75ኛው ደቂቃ ወደ ግብ የተሻማውን ኳስ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ግብ ጠባቂ ሲመልስበት ተቀይሮ የገባው ጃፋር ሙደሲር ዳግም ያገኘውን ግልፅ የሆነ የግብ ማግባት ሙከራ ሳይጠቀምበት መቅረቱን ተከትሎ ጨዋታው ያለ ምንም ግብ 0-0 ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥቡን ከአዲስ አበባ ከተማ እኩል በማድረግ በአንድ የግብ ብልጫ የምድቡ መሪ መሆን ችሏል።

ቀን 7:30 ላይ በተደረገው የዕለቱ ሶስተኛው መርሃ ግብር በምድቡ ግርጌ የሚገኙት ሞጆ ከተማን ከኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ አገናኝቶ ጨዋታው ነጥብ በመጋራት ተደምድሟል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማዎች የተሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን እና ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ያደረጉበት ነበር። በአንፃሩ በሞጆ ከተማዎች በኩልም ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት አድርገዋል።

በ27ኛው ደቂቃ የሞጆ ከተማ ተጫዋች የሆነው ኑሪ ሁሴን ከጥሩ የቅበብል ሂደት በኃላ ከመስመር ያገኘውን ኳስ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሯል።ከግቧ መቆጠር በኋላ ኮልፌዎች ግብ ለማግኘት ከፍተኛ ጫና መፍጠር ችለዋልል።

ይህንንም ተከትሎ በ32ኛው ደቂቃ ኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ በቅብብል ያሳደጉትን ኳስ የደረሰው እንዳለ ፀጋዬ በራሱ ጥረት ወደ ግብ ክልል በመግባት የአቻነቱን ግብ አስቆጥሯል።

በሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ራሳቸውን ለማጠናከር ጥሩ የሚባል የተጫዋች ቅያሪዎችን ቢያደርጉም አጋማሹ ግን ይበልጥ ጥንቃቄ የታከለበት ነበር። ሞጆ ከተማ በዮናታን ግርማ ጥሩ የሚባል እድል ሲያባክኑ በኮልፌዎች በኩል ደግሞ እንዳለ ፀጋዬ በተደጋጋሚ የሞጆ የግብ ክልል በመድረስ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ማስቆጠር ተስኖት ጨዋታው በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች ደረጃቸውን ሳያሻሽሉ እዛው የሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ሆነው የጨዋታ ሳምንቱን ፈፅመዋል።

የዕለቱ የማሳረጊያ በነበረው መርሃግብር 9:30 ላይ የተጀመረ ሲሆን ይርጋጨፌ ቡናን ከጅማ አባቡና አገናኝቶ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።

በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ይርጋ ጨፌ ቡናዎች የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም በቂ የግብ እድሎችን ግን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።በአጋማሹ ጅማዎች በተሻጋሪ ኳሶች ላይ ቀተንጠለጠለ መልኩ ለማጥቃት ሲሞክሩም እንዲሁ ተስተውሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ከመጀመሪያው አንፃር ተቀዛቅዘው የገቡ ሲሆን በአጋማሹም ብዙም ሙከራ ያልታየበት አጋማሽ ሆኗል። ጅማ አባቡና አልፎ አልፎ የግብ እድል ለመፍጠር ቢሞክርም ለግብ የቀረበ የግብ ሙከራ መፍጠር ተስኖት ጨዋታው ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።