የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ | የ9ኛ ሣምንት ምርጥ 11

ከትናት በስቲያ በተጠናቀቀው ዘጠነኛ ሣምንት ጎልተው በወጡ ተጫዋቾች ይህንን ምርጥ ቡድን ሠርተናል።

አሰላለፍ- 3-4-1-2

ግብ ጠባቂ

ታፔ አልዛየር – ሀዲያ ሆሳዕና

ነብሮቹ አዳማን በሠመረ ሀፍተይ ብቸኛ ግብ በመርታት ተከታታይ ድል ሲያስመዘግቡ የግብ ዘቡ ታፔ ብቃት ግሩም ነበር። አዳማዎች ያደረጓቸውን ሦስት ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን ያዳነው አይቮሪያዊው ግብ ጠባቂ ከበረከት አማረ ጋር ተፎካክሮ ከውጤታማነቱ አንጻር ሲመዘን እርሱ ተመራጭ በመሆኑ ምርጥ አስራ አንድ ውስጥ ምርጫችን ውስጥ ሊካተት ችሏል።

ተከላካዮች

ዋሳዋ ጄኦፍሪ – ኢትዮጵያ ቡና

ቡናማዎቹ ኃይቆቹን 2ለ1 በመርታት ከነበሩበት ጫና በመውጣት ተከታታይ ድል ሲያስመዘግቡ የመሃል ተከላካዩ ዋሳዋ አስተዋጽኦ የጎላ ነበር። የኋላ መስመሩን በተሻለ የራስ መተማመን ከመምራቱም በላይ ከቆሙ ኳሶች ሲፈጥራቸው የነበሩት የግብ ዕድሎች በምርጥ ቡድናችን ውስጥ እንዲካተት አስችለውታል።

ከድር ኩሊባሊ – ሀዲያ ሆሳዕና

ሀዲያዎች ተከታታይ ድል ሲያስመዘግቡ እንደ ቡድን አጋሩ ታፔ ሁሉ እጅግ ስኬታማ ቀን ያሳለፈው የመሃል ተከላካዩ ኩሊባሊ የአዳማን ተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያመክን የነበረበት መንገድ እና የኋላ መስመሩን ሲያደራጅ የነበረበት መንገድ በቦታው ያለ ተቀናቃኝ ተመራጭ አድርጎታል።

ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ፈረሠኞቹ ከመቻል ጋር 1ለ1 በተለያዩበት ጨዋታ የመሃል ተከላካዩ ፍሪምፖንግ ሜንሱ በግንባር ገጭቶ ባስቆጠረው ግብ ቡድኑን ነጥብ እንዲጋራ ሲያስችል ከግቡ ባሻገርም ባደረገው እንቅስቃሴ በምርጥ ቡድናችን ውስጥ ተካቷል።

አማካዮች

በፍቃዱ ዓለማየሁ – ኢትዮጵያ ቡና

ኢትዮጵያ ቡናዎች ሀዋሳን 2ለ1 በመርታት ወሳኝ ድል ሲያሳኩ የግራ መስመር ተከላካዩ በፍቃዱ ብቃት የሚደነቅ ነበር። ከተስፋ ቡድን ዘንድሮ ወደ ዋናው ቡድን በማደግ ለክለቡ ድንቅ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው በፍቃዱ ዕረፍት የለሽ በሆነ እንቅስቃሴ ከሳጥን ሳጥን በሚያደርጋቸው ሩጫዎቹ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ሲሆን ባሳለፍነው ሣምንትም ስኬታማ ጊዜ ማሳለፍ ችሏል።

አብነት ደምሴ – ወላይታ ድቻ

የጦና ንቦቹ ሠራተኞቹን በረቱበት ጨዋታ ከብርቱ ጥረት በኋላ የማሸነፊያውን ግብ በግሩም ሁኔታ በግንባር በመግጨት ያስቆጠረው አብነት ከግቡ ባሻገር በተለይም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ በተሻለ የራስ መተማመን ውጤቱን ይዘው እንዲወጡ አስችሏል።

አማኑኤል ዮሐንስ – ኢትዮጵያ ቡና

ቡናማዎቹ በማራኪ እንቅስቃሴ ሀዋሳ ላይ ድል ሲቀዳጁ የአማካዩ ብቃት አስደናቂ ነበር። በመጀመርያዎቹ ሳምንታት ከተጠባባቂ ወንበር እየተነሳ ይጫወት የነበረው አማኑኤል ወደ ቋሚ አስራ አንድ ከተመለሰበት ጊዜ አንስቶ ወደ ሚታወቅበት የቀድሞ አቋሙ እየተመለሰ ይገኛል። በተለይም ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ለማሸነፊያው ግባቸው ቁልፍ መነሻ የነበር ሲሆን ከውጤታማነቱ ባሻገር ቡድኑ በኳስ ቁጥጥሩ ለወሰደው ብልጫ ጉልህ አስተዋጽኦ ነበረው።

ሽመክት ጉግሣ – ፋሲል ከነማ

ዐፄዎቹ ብርቱካናማዎቹን 3-0 በመርታት ወደ ድል ሲመለሱ የመስመር አጥቂው ሽመክት ሁለት ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ሲችል ከዕረፍት መልስ ወደኋላ ተስቦ ግሩም የሆኑ የተሰነጠቁ ኳሶችን አመቻችቶ ባቀበለበት ቦታ ላይ በምርጥ ቡድናቸን ውስጥ አካተነዋል።

ባሲሩ ኦማር – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ንግድ ባንኮች ባደጉበት ዓመት በሊጉ አስገራሚ ግስጋሴ እንዲያደርጉ የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ ተከታታይ ጎሎች በየጨዋታው እያስቆጠረ ሚናው ከፍ እያለ የሚገኘው ባሲሩ ንግድ ባንኮች ስድስተኛ ተከታታይ ድል ባስመዘገቡበት የሀምበሪቾው ጨዋታም ያሳየው ብቃት እጅግ ግሩም ነበር። ባሲሩ የቡድኑን የመጀመሪያ ግብ በስሙ ማስመዝገብ ሲችል ሲያደርጋቸው የነበሩት በርካታ ስኬታማ ቅብብሎቹ እና የፈጠራቸው የግብ ዕድሎች ያለ ተቀናቃኝ ተመራጭ አድርገውታል።

አጥቂዎች

ጌታነህ ከበደ – ፋሲል ከነማ

ፋሲሎች ድሬዳዋን በመርታት ወደ ድል በተመለሱበት ጨዋታ ልዩነት ፈጣሪ የነበረው ጌታነህ ከበደ በውድድር ዓመቱ ምርጡ የሆነውን እንቅስቃሴ ባደረገበት ጨዋታ ከተደጋጋሚ ጥረቶች በኋላ በቅጣት ምት እና በጨዋታ ያስቆጠራቸው ግሩም ግቦች ለቡድኑ ማሸነፍ የነበራቸው ሚና በጉልህ የሚታይ ነበር።

መስፍን ታፈሰ – ኢትዮጵያ ቡና

ከጎል በመራቁ ምክንያት በራስ መተማመኑን አጥቶ ይገኝ የነበረው መስፍን በዚህኛው ሣምንት ቡናማዎቹ ኃይቆቹን ሲረቱ ከቀድሞ ክለቡ ላይ በፍጹም ቅጣት ምት እና በጨዋታ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ካደረገው እንቅስቃሴ ባሻገር ውጤታማነቱ በቦታው ተመራጭ አድርጎታል።


ተጠባባቂዎች

በረከት አማረ – ኢትዮጵያ ቡና
ፈቱዲን ጀማል – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ብርሃኑ በቀለ – ሲዳማ ቡና
ይታገሡ ታሪኩ – ኢትዮጵያ ቡና
አብዱልከሪም ወርቁ – ኢትዮጵያ ቡና
በረከት ግዛው – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
በዛብህ መለዮ – ሲዳማ ቡና
ሠመረ ሀፍተይ – ሀዲያ ሆሳዕና
ቢኒያም ፍቅሩ – ወላይታ ድቻ

አሰልጣኝ – ነጻነት ክብሬ

ኢትዮጵያ ቡናን ላለፉት ሁለት የፕሪሚየር ሊግ እና አንድ የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች የመራው ነጻነት ተጫዋቾቹ ላይ የፈጠረው እጅግ የጋለ የመጫወት ፍላጎት ቡድኑ ላሳካቸው ተከታታይ ድሎች ወሳኝ ነበር። ባሳለፍነው ሣምንትም ቡናማዎቹ ኃይቆቹን ሲረቱ የነበራቸው የጨዋታ ብልጫ አሰልጣኙ ምርጥ ቡድናችንን እንዲመራ አስችሎታል።