ከፍተኛ ሊግ | ተጠባቂው ጨዋታ በአርባምንጭ አሸናፊነት ተጠናቋል

በከፍተኛ ሊጉ የ11ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ በምድብ ‘ሀ’ ንብ ፣ ሀላባ ከተማ እና ኦሮሚያ ፖሊስ ሲያሸንፉ የምድብ ‘ለ’ ወሳኝ ጨዋታ በአርባምንጭ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሀዋሳ ላይ ከበርካታ ግብ ሙከራዎች ጋር የታጀበው የ4 ሰዓቱ ጨዋታ ባቱ ከተማ ከቢሾፍቱ ከተማ መካከል ተደርጓል። በሁለቱም ቡድኖች መካከል በቁጥር በርከት ያለ የግብ ሙከራ መደረጉን ተመልክተናል።

ቢሾፍቱ ከተማዎች ባንደኛው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር እና በግብ ሙከራ ብልጫ መውሰድ ችለው ነበር። በ22ኛው ደቂቃ የቢሾፍቱ ከተማው 9 ቁጥር ለባሽ የሆነው አብዱልአዚዝ ኡመር ግብ ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ ተብሎበታል። ባቱ ከተማ በአንፃሩ የግብ ሙከራ በማድረግ ተመጣጣኝ ጨዋታ አድርገዋል። በ32ኛው ደቂቃ የባቱ ከተማው ጆንቴ ገመቹ ከመስመር ወደ ግብ የመታት ኳስ የግብ አግዳም መልሶበታል። እንዲሁም በ40ኛው ደቂቃ የባቱው ወንደሰን በለጠ በመሬት ከሳጥን ውጪ ሆኖ የመታት ኳስ በድጋሚ የግብ አግዳሚ መልሶበታል።

ሁለቱም ቡድኖች በተደጋጋሚ የተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል እየገቡ አደገኛ እና ለግብ የተቃረበ ሙከራ ሲያድርጉ የተስተዋሉ ሲሆን በመጀመሪያ አጋማሽ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው 0ለ0 በሆነ አቻ ውጤት እረፍት አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ አይነት ሳይሆን በጥንቃቄ የተሞላ አጨዋወት ይዘው ገብተዋል። በ50ኛው ደቂቃ የቢሾፍቱ ከተማው ተጫዋች ዘካሪያስ ከበደ ነገሽ ዳዊት ያቃበለለትን ኳስ ተከላካዮችን አታሎ ድንቅ ግብ በማስቆጠር ቢሾፍቱ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ በተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ያደረጉት ባቱ ከተማዎች የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ወደጨዋታ ለመመልስ ጥረት አድርገዋል። በ61ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ዮናታን አምባዬ በራሱ ጥረት የቢሾፍቱ ከተማ ተከላካዮችን እያታለለ በመስመር በኩል ሰብሮ በመግባት ኳስና መረብ አጋናኝቶ አቻ እንዲሆኑ አስችሏል። ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ሁለቱም ቡድኖች የግብ ሙከራ ቢያድርጉም ሌላ ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

በምድብ ‘ሀ’ 03:30 ላይ በተደረገው ጨዋታ ነቀምቴ ከተማ በዚህም ሳምንት ሽንፈት አስተናግዶ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ያለው ተሳትፎ እንዲደበዝዝ ሆኗል። ነቀምቴን የገጠመው ንብ ጨዋታውን 4-1 በሆነ ውጤት ማገባደድ ችሏል። ተከታታይ ድሎችን ያሳካው ንብ ነጥቡን 20 በማድረስ ነገ ጨዋታዎቻቸውን ከሚያከናውኑት ሁለቱ መሪዎች በሁለት ነጥብ ርቀት ላይ ተቀምጧል።

በምድብ ለ በመጀመሪያዎቹ በ5 ደቂቃዎች ብቻ ሁለት ግቦች የተቆጠሩበት የቀን ስምንት ሰዓቱ ጨዋታ ጋሞ ጨንቻን ከደሴ ከተማ አገናኝቶ በጋሞ ጨንቻ በላይነት ሲጠናቀቅ ደሴ ከተማ ተከታታይ ሽንፈት አስተናግዷል።

ጨዋታው ገና ከጀመረ በሁለተኛው ደቂቃ ተቀይሮ በመግባት ተቃራኒ ቡድንን በማስጨነቅ ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማመቻቸት የሚታወቀው ጉልላት ተሾመ ዛሬ ቋሚ ሆኖ በመግባት ከሳጥን ውጭ ሆኖ አክርሮ መትቶ ለደሴ ከተማ ግብ በማስቆጠር መሪ እንዲሆኑ አድርጓል።

ደሴ ከተማዎች ለሦስት ያህል ደቂቃ ብቻ ነበር በመሪነት መቆየት የቻሉት። ግብ አስቆጥረው መረጋጋት ተስኗቸው የኳስ ብልጫ በተቃራኒ ቡድን የተወሰደባቸው ሲሆን በ5ኛው ደቂቃ ታደለ ታንቶ ከመስመር በመሬት ያቃበለለትን ኳስ ጌታሁን ገዛኽኝ አክርሮ መቶ ለጋሞ ጨንቻ ኳስና መረብ አገናኝቶ  አቻ እንዲሆኑ አስችሏል።

አቻ ከሆኑ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች መሪ ለመሆን ተጨማሪ ግብ ፍለጋ የግብ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር 1-1 በሆነ ውጤት ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱት ጋሞ ጨንቻዎች በ75ኛው ደቂቃ ብሩክ ሰካሌ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ከሳጥን ውጭ ሆኖ መጥቶ በማስቆጠር ጋሞ ጨንቻን መሪ አድርጓል።

ደሴ ከተማ በአንፃሩ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ በቀረችው ደቂቃ ግብ ለማስቆጠር በተደጋጋሚ ለግብ የተቃረቡ ኳሶችን ሲሞክሩ ተስተውለዋል። ሆኖም ግን ጋሞ ጨንቻ መሪነታቸውን ለማስጠበቅ ወደ ኋላ አፈግፍገው በመከለከላቸው ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው 2-1 በሆነ ውጤት በጋሞ ጨንቻ አሸናፊነት ተቋጭቷል።

በምድብ ሀ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ በተደረገ የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ሀላባ ከተማ ጅማ አባ ጅፋርን 4-1 ረቷል። ውጤቱ በተከታታይ ድሎች ተነቃቅቶ ለነበረው ጅማ አባ ጅፋር ሁለተኛ ተከታታይ ሽንፈት ሆኖ ሲመዘገብ ሀላባዎች ደግሞ ተከታታይ ድል አሳክተው ደረጃቸውን ወደ አምስተኛ ከፍ ያደረጉበት ሆኗል።

በምድብ ለ የዕለቱ የመጨረሻ የነበረው እና መሪዎቹን ያገናኘው ደመቅ ካለ ከደጋፊ ድባብ እና ከማራኪ እግር ኳስ ጋር የታጀበው ተጠባቂው ጨዋታ ከመጀመሪያው ጀምሮ ሁለቱም ቡድኖች ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ ታይተዋል።

ገና ጨዋታ እንደጀመረ ነጌሌ አርሲዎች በተደጋጋሚ ወደተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ኳስ ይዘው እየገቡ ሙከራ አድርገዋል። በአራተኛው ደቂቃ ሁለት ቁጡሩ ምንተስኖት ከመስመር ያሻማት ኳስ ታምራት ኢያሱ በግንባሩ ገጭቶ አስገራሚ ሙከራ አድርጓል።

አርባምንጭ ከተማ በአንፃሩ በፊት አጥቂያቸው በአህመድ ሁሴን አማካኝነት የግብ ሙከራዎችን ሲያድርጉ በ19ኛው ደቂቃ የቆመ ኳስ አግንተው እንዳልካቸው መስፍን ቀጥታ ወደግብ የመታትን ኳስ ግብ ጠባቂው እንዴትም ሆኖ አድኗታል።

ሁለቱም ቁድኖች ግብ ለማስቆጠር በተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን በ36ኛው ደቂቃ መርሁን መስቀለ በተከላካዮች መሃል ሰንጥቆ ያቃበለለትን ኳስ አህመድ ሁሴን ወደቦክስ ውስጥ ይዞ በመግባት አርባምንጭ ከተማን መሪ እንዲሆኑ አስችሏል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ነጌሌ አርሲዎችም የአቻነት ግብ ፍለጋ ኳስን ወደፊት ሲያንሸራሽሩ ተስተውለዋል። ሆኖሞ ግን ግብ ማስቆጠረ ሳይችሉ ቀርተው 1ለ 0 እየተመሩ ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ጠንከር ብሎ የገቡት ነጌሌ አርሲዎች በ49ኛው ደቂቃ በቦክስ ውስጥ ሰለሞን ገመቹ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀም ቀርቷል።ነጌሌ አርሲዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ወደፊት በሚሄዱበት ወቅት አርባምንጭ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት በ59ኛው ኳስ አግኝተው አህመድ ሁሴን ኳስና መረብ አገናኝቶ  መሪነታቸውን አጠናክሯል።

የምድብ መሪነታቸውን ለመረከብ በጫና ሲጫዎቱ የነበሩት ነጌሌዎቹ  በ66ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ታምራት ኢያሱ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር 2ለ1 በመሆን ወደጨዋታ እንዲመልሱ አድርጓል።

መደበኛው የጨዋታ ተጠናቆ ተጨማሪ በታየ ደቂቃ ላይ ነጌሌ አርሲዎች በምንተስኖት አዲስ አማካኝነት ለግብ የተቃረበ ሙከራ ቢያደርጉም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው በአረባምንጭ ከተማ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ወሳኝ ድል ማሳካት የቻለው አርባምንጭ ከተማ ነጥቡን 27 በማድረስ ተከታዩ ነጌሌ አርሲን በሦስት ነጥብ ርቆ መቀመጥ ችሏል።

የምድብ ሀ የመጨረሻ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ተከናውኖ ኦሮሚያ ፖሊስ በያለው አታረጋ ብቸኛ ጎል ይርጋጨፌ ቡናን 1-0 አሸንፏል። ውጤቱም ኦሮሚያ ፖሊስ በሰንጠረዡ አጋማሽ እንዲቀመጥ አስችሎታል።