መረጃዎች | 39ኛ የጨዋታ ቀን

የአስረኛው ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን አሰናድተንላችኋል።

መቻል ከ ሀዋሳ ከተማ

ከመሪዎቹ ተርታ የሚገኙት መቻሎችና ተከታታይ ሽንፈት ያስተናገዱት ሀዋሳዎች ከኢትዮጵያ ዋንጫ ፍልሚያቸው በኋላ የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ይሆናል።

ከአምስት ተከታታይ ድሎች በኋላ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አቻ ተለያይተው ከመሪው በሦስት ነጥብ ዝቅ ብለው በሁለተኛ ደረጃነት የተቀመጡት መቻሎች ዳግም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ሀዋሳ ከተማን ይገጥማሉ። መቻሎች ካለፉት የውድድር ዓመታት የተሻለና ጥሩ ጊዜ እያሳለፉ ይገኛሉ፤ ከሁለት አቻና አንድ ሽንፈት ውጭ በተቀሩት ስድስት ጨዋታዎች ድል አድርገዋል። ማግኘት ከሚገባቸው ሀያ ሰባት ነጥቦችም ሀያውን አሳክተዋል። መቻሎች ከመሪው ንግድ ባንክና ሀድያ ሆሳዕና ቀጥሎ ጥቂት ግቦች ያስቆጠረ ጠንካራ የተከላላይ ክፍል ቢኖራቸውም በማጥቃቱ ረገድ ግን ከአማካይ ክፍሉ ጥራትና ከሚፈጠሩት የግብ ዕድሎች አንፃር ዕድሎች ወደ ግብነት የመቀየር ውስን ክፍተቶች አላቸው። የቡድኑ የማጥቃት ክፍል ወሳኝ አማካዮቹን ከጉዳት መልስ ካገኘ በኋላ የሚታይ ለውጥ ማሳየት ቢችልም አሁንም ውስን ለውጦችን ይሻል።

ከዘጠኙ ሳምንታት በአማካይ አንድ ነጥብ ሰብስበው በዘጠኝ ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀዋሳ ከተማዎች ከአስከፊው ጉዞ ለመላቀቅ መቻልን ይገጥማሉ። ሀዋሳዎች ተከታታይ አራት ጨዋታዎች ላይ ተሸንፈዋል። ቡድኑ በሊጉ ጅማሮ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ከነበራቸው ቡድኖች ውስጥ ቢካተትም በጊዜ ሂደት ግን ጥንካሬውን አጥቶ በመጨረሻዎቹ አራት የሊግ ጨዋታዎች አስር ግቦች አስተናግዷል። አሰልጣኝ ዘርዐይ ሙሉ በቀዳሚነት ይህንን የቡድኑ ዋነኛ ችግር በአፋጣኝ የመፍታት ስራ ይጠብቃቸዋል። ከዛ በተጨማሪም ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች ላይ አራት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው የፊት መስመርም ሌላው አንገብጋቢ ለውጥ የሚሻ ክፍል ነው።

በሀዋሳ ከተማ በኩል ከሙጂብ ቃሲም በተጨሜሪ እዮብ አለማየሁ እና መድሀኔ ብርሀኔ በቀይ ካርድ ቅጣት ከጨዋታው ውጪ ሲሆኑ በመቻል በኩል ሙሉ ቡድኑ ለጨዋታው ዝግጁ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ቅጣት ላይ የነበረው ግሩም ሐጎስ ቅጣቱን ጨርሶ ወደ ሜዳ ይመለሳል።

ሁለቱ ቡድኖች 32 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ ከተማ 14 በማሸነፍ ቅድሚያውን ሲይዝ መከላከያ 8 ጨዋታ አሸንፏል። ቀሪዎቹ 10 ጨዋታዎች አቻ የተለያዩባቸው ግንኙነቶች ናቸው። በርካታ በጎሎች የታጀበ ታሪክ ያለው ይህ ግንኙነት 72 ጎሎች የተቆጠሩበት ሲሆን ሀዋሳ 40 ፣ መከላከያ 32 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

በዋና ዳኝነት ጨዋታውን አባይነህ ሙላት ሲያጋፍረው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ እና ሙሉነህ በዳዳ በረዳትነት ኢንተርናሽናል ዳኛ (ዶ/ር) ሀይለየሱስ ባዘዘው በአራተኛ ዳኝነት በጣምራ ይመሩታል።

ሀድያ ሆሳዕና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከመጥፎው አጀማመር ተላቀው በጥሩ የአሸናፊነት መንፈስ የሚገኙት ሀድያ ሆሳዕናዎች አምና ቻምፒዮንነታቸውን ባረጋገጡቡት በዚህ መርሀግብር ጥሩ ትዝታ ወደ ሜዳ የሚገቡት ፈረሰኞቹ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ምሽት 12:00 ላይ ይከናወናል።

ከተከታታይ አምስት አቻዎች በኋላ ሁለት ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው ነጥባቸው ወደ አስራ አንድ አድርሰው በ10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀድያ ሆሳዕናዎች የሽቅብ ጉዟቸው ለማስቀጠል ፈረሰኞቹን ይገጥማሉ። ድል ባደረጉባቸው ሁለት ጨዋታዎች ላይ በአመዛኙ ወደ ራሱ ግብ የተጠጋና ወደ መከላከሉ ያደላ አጨዋወት የነበራቸው ሀድያዎች በመከላከሉ ረገድ ጠጣር የሆነ አደረጃጀት አላቸው፤ በሊጉም በጨዋታ በአማካይ 0.6 ግቦች ብቻ በማስተናገድ ከንግድ ባንክ ቀጥለው ተቀምጠዋል። አሰልጣኝ ግርማ በነገው ዕለትም በተመሳሳይ መከላከል ላይ የተመሰረተ አጨዋወት የሚከተሉበት ዕድል የሰፋ ነው። የነገው ተጋጣሚያቸው በሊጉ ከፍተኛው የግብ መጠን ያስቆጠረ ክለብ እንደመሆኑና ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ላይ የተከተሉት አጨዋወት እንደ ምክንያት የሚነሱ ነጥቦች ናቸው። ሀድያዎች ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ማስቆጠር ቢችሉም የመልሶ ማጥቃት አጨዋወቱ ውጤታማነት ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ የአቻና ሽንፈት ውጤቶች ያስመዘገቡት ፈረሰኞቹ ከሁለተ ሳምንታት በኋላ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ሀድያን ይገጥማሉ። በሊጉ ጠንካራ የማጥቃት ክፍል ካላቸው ክለቦች ውስጥ የሚገኙት ፈረሰኞቹ የአምስት ሳምንታት ያለመሸነፍ ጉዟቸው በባህርዳር ከተማ ከተገታ በኋላ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻሉት አንዱን ብቻ ነው፤ ይህንን ተከትሎም ከመሪው ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዮነት ወደ ስድስት ከፍ ብሏል። በነገው ጨዋታም ወደ አሸናፊነት ከመመለስ ባለፈ ከመሪው ጋር ያላቸው የነጥብ ልዮነት ብያንስ አስጠብቆ ለመሄድ ማሸነፍ ግድ ይላቸዋል። የፈረሰኞቹ ወቅታዊ ውጤት ጥሩ የሚባል ባይሆንም የቡድኑ እንቅስቃሴ ግን በመጥፎ ጎን የሚጠቀስ አይደለም፤ ቡድኑ ከመቻል ጋር አቻ በተለያየበትና ከተጋጣሚው በአንፃራዊነት የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳየበት ጨዋታም የዚ ማሳያ ነው። አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ካለፉት ሁለት ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ለማሸነፍ ለውጦች ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፤ በተለይም ለውትሮ ጠንካራ የነበረውና በሁለቱም ጨዋታዎች ውስን መቀዛቀዞች የታየበት የማጥቃት አጨዋወታቸው ውስን ለውጥ ይደረግባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁት የቡድኑ ክፍሎች ናቸው።

ሀድያ ሆሳዕናዎች በአባቱ ሞት ምክንያት ከቡድኑ ጋር ከሌለው ዳዋ ሆቴሳ በተጨማሪ ሔኖክ አርፊጮ እና ካሌብ በየነ በጉዳት ምክንያት አይኖሩም። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ቅጣቱን ያልጨረሰው ሞሰስ አዶ በዚ ጨዋታ ተሳትፎ አይኖረውም።

ቡድኖቹ እስካሁን ስምንት ጊዜ ሲገናኙ ቅዱስ ጊዮርጊስ አራት ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ ሁለት ድሎችን አሳክተው ሁለት ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘጠኝ ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ ሦስት ግቦች አስቆጥረዋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በመሐል ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና ሠለሞን ተስፋዬ በረዳት ዳኝነት ሔኖክ አበበ በአንፃሩ በአራተኛ ዳኝነት ተሰይሟል።