የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀድያ ሆሳዕና 0-0 ቅዱስ ጊዮርጊስ

“በሠራነው ስራ በቂ ነገር አግኝተናል” አሰልጣኝ ግርማ ታደሠ

“የተሻለ ነገር ለማድረግ ነበር ምንም አልተሳካም” አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ

ነብሮቹ እና ፈረሰኞቹ ያለ ጎል ጨዋታቸውን ከፈፀሙ በኋላ የድህረ ጨዋታ አስተያየት ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኞቹ ጋር አድርጋለች።

አሰልጣኝ ግርማ ታደሠ – ሀድያ ሆሳዕና

ስለ ጨዋታው…?

“ዛሬ ጨዋታው አቀራረባችን በጣም ጥሩ ነው። ጥሩ አቀራረብ ቀርበናል ብዬ ነው የማስበው ፣ ለምን ጠንካራ ቡድን ነው ጊዮርጊስ በዛ ላይ ደግሞ አጨዋወታቸው በጣም ከባድ ነው ቀጥተኛ ኳስ ነው ከየትኛውም አቅጣጫ ከተከላካይ ጀርባ ላይ የሚጥሉት ኳስ በጣም ከባድ ነው ፣ ለእነዛ በጣም ዝግጅት አድርገን ነው የቀረብነው ምናልባት በጣም ማኔጅ ማድረግ ችለናል ብዬ ነው የማስበው ፣ እንደውም የጎል አጋጣሚዎችን ከዕረፍት በፊትም በኋላም መፍጠር ችለናል በመልሶ ማጥቃት እንደ አጠቃላይ ግን በሠራነው ሥራ በቂ ነገር አግኝተናል ብዬ አስባለሁ። እንደዚሁም ደግሞ ተጫዋቾቹ ለከፈሉት ዋጋ በዚሁ አጋጣሚ ላመሰግን እፈልጋለሁ።”

ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ከራሳቸው የግብ ክልል በተሻለ እየወጡ ለማጥቃት ስለ መጫወታቸው…?

“እነርሱን ለመሳብ ፈልገናል በዕርግጥ ኳሳቸው ረጃጅም ኳሶች ስለሆነ እኛ በጣም እየወረድን የምናገኛቸውን ኳሶች በመልሶ ማጥቃት አግኝተናል። ሁለት ሦስት ኳሶችን በሚገባ አግኝተናል ግን ሦስተኛ ሜዳ ላይ የጥራት ችግር አለብን በጣም መስራት ይጠበቅብናል ካለን አቅም ፣ ካሉም ልጆች አኳያ በተወሰነ መልኩ ጥራት ችግር አለ ያንን እናስተካክላለን ብዬ አስባለሁ።”

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

አቻ ስለ ወጡበት ጨዋታ…

“ሀድያ ሁሌም ከእኛ ጋር ሲጫወት እንደዚህ አይነት ጨዋታ ነው የሚጫወተው ፣ ማድረግ ያለባቸውን እና ሠርተው የመጡበት ማድረግ ችለዋል። እኛ በይበልጥ መቶ ፐርሰንት ኮንሰንትሬሽናችን ትንሽ ላላ ያለ ነበር ግን ማድረግ ያለብንን ሁሉ ሞክረን የተሻለ ነገር ለማድረግ ነበር ምንም አልተሳካም።”

የጠሩ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የቡድናቹ የአቅም ማነስ ወይስ የተጋጣሚ ቡድን የመከላከል ጥንካሬ…

“ሎው ብሎክ ነው የተጫወቱት እኛም ደግሞ ቅድም መጀመሪያ እንደተናገርኩት በይበልጥ ኮንሰንትሬሽናችን ልክ አልነበረም። አንዳንድ ኳሶቻችን ይበላሹብን ነበር ማድረግ ያለብንን ኳሶች በቀላሉ ይባክናሉ። እንደዚህም ሆኖ ሞክረናል ጥንካሬ የላቸውም እንጂ ያለብንን አድርገናል። እነርሱም ጠንካራ ነበሩ ጥሩ ጨዋታ ነው የተጫወቱት በትራንዚሽን ነበር እኛ ላይ ለመምጣት የሚፈልጉት ግን ዜሮ ለዜሮ ወጥተናል ተከስቷል ምንም ማድረግ አልችልም ፣ ማለት እንደዚህ አይነት ነገር ነገም ሊገጥመን ስለሚችል የተሻለ ነገር ለማድረግ እንሄዳለን ፣ ከዚህም በላይ የተሻለ ነገር ለማድረግ መሄድም እንችል ነበር አንዳንድ ቀላል ኳሶች በቀላሉ ይበላሹብናል በሎው ብሎክ ነው የሚጫወቱት ከዛ ኳሶቻችን ሲበላሹ በትራንዚሽን ሩጫ ነው የሚሆነው ስለዚህ ይሄ ይሄ ነው እንጂ መጥፎ ነገር አልነበረውም ጨዋታው።”