መረጃዎች | 40ኛ የጨዋታ ቀን

የአስረኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገም ቀጥለው ይካሄዳሉ ፤ ጨዋታዎቹን አስመልክተን ያሰናዳናቸው መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበናል።

ኢትዮጵያ መድን ከ ድሬዳዋ ከተማ

በአንድ ነጥብ የሚበላለጡ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ ፍልሚያ ነው።

በዘጠነኛው ሳምንት በሲዳማ ቡና የአንድ ለባዶ ሽንፈት የገጠማቸው ኢትዮጵያ መድኖች በዘጠኙ ሳምንታት በጨዋታ በአማካይ አንድ ነጥብ በማግኘት ዘጠኝ ነጥቦች ሰብስበው በ11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። መድኖች ከተከታታይ ስድስት ድል አልባ ሳምንታት በኋላ ሀምበርቾን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ የውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ድላቸው ማስመዝገብ ቢችሉም በመጨረሻው ጨዋታ በሲዳማ ቡና የአንድ ለባዶ ሽንፈት አስተናግደዋል።

በጨዋታውም ሁሌም በቡድኑ የሚስተዋለው የግብ ማስቆጠር ችግር ጎልቶ ታይቷል። ከባለፈው ዓመት ቡድናቸው አንፃር በተሻለ መንገድ የሚከላከል ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በማጥቃቱ ረገድ ያላቸው ጥምረት ግን ደረት የሚያስነፋ አይደለም። ቡድኑ ከሦስተኛው እስከ ስድስተኛው ሳምንት ድረስ በተካሄዱ አራት ጨዋታዎች ግብ አለማስቆጠሩና በውድድር ዓመቱ በጨዋታ በአማካይ 0.7 ግቦች ብቻ ማስቆጠሩም ማሳያዎች ናቸው። አሰልጣኙ በተከታታይነት የግብ ማስቆጠር ድርሻው የሚሸከም የሁነኛ አጥቂ እጥረታቸውን ለመሸፈን የግብ ምንጭ አማራጮቻቸው ማስፋት ይጠበቅባቸዋል።

ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች አስተናግደው ወደ ነገው ጨዋታ የሚቀርቡት ድሬዳዋ ከተማዎች በስምንት ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ብርቱካናማዎቹ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ማስተናገድ ችለዋል፤ ቡድኑ በተለይም በፋሲል ከነማ ሦስት ግቦች አስተናግዶ በተሸነፈበት ጨዋታ ላይ የተሻለ የመከላከል አደረጃጀት መገንባት ቢችልም የትኩረት ማነስ ችግሮች ተስተውሎበታል። በተለይም ከክፍት ጨዋታ የተቆጠሩባቸው ግቦች መነሻቸው የትኩረት ማጣት ችግር ነበር። አሰልጣኝ አስራት አባተ ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች ለማገገም የተጠቀሰው ችግር ከመቅረፍ በዘለለ በተጫዋቾች ጉዳት ምክንያት ሳስቶ የነበረው የማጥቃት ክፍላቸውም ላይ መጠነኛ ለውጦች ያደርጋሉ ተብሎ ይገመታል። የቡድኑ የአማካይ ክፍል ከመጨረሻው ጨዋታ ውጭ በነበሩ ጨዋታዎች ላይ የጎል ዕድሎች በመፍጠር ረገድ መሻሻሎች ቢያሳይም የአጥቂ ክፍሉ ውጤታማነት ግን አሁንም ለውጦችን ይሻል።

በጨዋታው መድኖች በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ያለው ሀቢብ ከማል አያሰልፉም። በድሬዳዋ ከተማዎች በኩልም ያሲን ጀማል ፣ ዓብዱልፈታህ ዓሊ እና ተመስገን ደረስ በጉዳት ምክንያት ቡድናቸውን አያገለግሉም። ባለፈው ጨዋታ ያልተሳተፈው ቻርለስ ሙሴጌ ግን ወደ ሜዳ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ መድን እና ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ 6 ጊዜ ተገናኝተው ሁለት ሁለት ጊዜ ሲሸናነፉ ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። መድን 6 ሲያስቆጥር ድሬዳዋ 5 አስቆጥሯል።

ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ዳንኤል ይታገሱ ሲመራው ለዓለም ዋሲሁን እና ወጋየሁ አየለ በረዳት ዳኝነት ባህሩ ተካ በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት ተመድቧል።

ባህር ዳር ከተማ ከ ሀምበርቾ

ባህርዳር ከተማ እና ሀምበርቾ የሚያካሂዱት ጨዋታ ምሽት 12:00 ላይ ይደረጋል።

ከሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ ከሻሸመኔ ከተማ ጋር አቻ በመለያየት በአስራ ስምንት ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህር ዳር ከተማዎች ዳግም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ በሊጉ ግርጌ ላይ ከሚገኘው ሀምበርቾ ይገናኛሉ። በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ግብ ሳያስቆጥሩ በወጡበት ጨዋታ ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ጥቂት የማይባሉ የግብ ዕድሎች መፍጠር ቢችሉም በአማዛኙ ግን ወደ ራሱ የግብ ክልል ቀርቦ ለመከላከል የመረጠውን ተጋጣሚ ለማስከፈት ሲቸገሩ ተስተውለዋል። የነገው ተጋጣሚያቸውም በተመሳሳይ ወደ ራሱ የግብ ክልል ተጠግቶ ይከላከላል ተብሎ ስለሚጠበቅ ከወዲሁ መፍትሄ ማበጀት ይኖርባቸዋል። በተለይም ከዚህ ቀደም ቡድኑ የሚጠቀምበት የፈጣን ሽግግር አጨዋወት ላይ ውስን ለውጦች ማድረግ ይጠበቅበታል። በ ‘Low Block’ ለመከላከል አልሞ የሚገባን ቡድን ማስከፈት የሚችል ትእግስት ቡድኑ ላይ ማስረፅም የአሰልጣኙ ሌላው ስራ ነው።

የአሰልጣኝ ለውጥ አድርገው ባካሄዱት የመጀመርያ ጨዋታ ላይ ሽንፈት የገጠማቸው ሀምበርቾዎች በሁለት ነጥቦች በሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጠዋል። ሀምበርቾዎች ንግድ ባንክን በገጠሙበት ጨዋታ ላይ መከላከል ላይ ያመዘነ አጨዋወት ቢከተሉም ሁለት ግቦች ከማስተናገድ አልተረፉም። ሆኖም ጨዋታው ከሊጉ መሪና ጠንካራ የማጥቃት ክፍል ጋር ካለው ቡድን ጋር የተካሄደ እንደመሆኑ ቡድኑ በመከላከሉ ረገድ ያሳየው እንቅስቃሴ መጥፎ ነበር ብሎ ለመደምደም አይቻልም። ቡድኑ በቀጣዮቹ ጨዋታዎች በትኩረት የመከላከል ክህሎት ጨምሮ ውስን ማሻሻያዎች ካደረገ በተሻለ መንገድ ሊከላከል እንደሚችል ፍንጭ ያሳየበት ጨዋታም ጭምር ነበር። አዲሱ የአሰልጣኞች ቡድን በነገው ጨዋታም በተመሳሳይ ወደ ራሱ ግብ ክልል በቁጥር በዝቶ የሚከላከል አጨዋወት ይከተላል ተብሎ ይገመታል፤ ተጋጣሚው በሊጉ በርካታ ግቦች ካስቆጠሩ ሦስት ክለቦች አንዱ የሆነውን እንደመግጠሙ መከላከሉ ላይ ቅድምያ ሰጥቶ የሚገባበት ዕድል ሰፊ ነው። ለተከታታይ ስድስት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት የተሳነው የማጥቃት ጥምረት የማስተከል ስራም አሰልጣኝ ብሩክ ሲሣይ ትልቁ የቤት ስራ ነው።

በባህር ዳር ከተማ በኩል በመጨረሻው ጨዋታ በሁለት ቢጫ ከሜዳ የወጣው ፍሬዘር ካሳ በቅጣት አይሰለፍም፤ በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ያለው አደም አባስም በተመሳሳይ ቡድኑን አያገለግልም። ሌላው ከተፈቀደለት የዕረፍት ጊዜ የዘገየው ሱሌይማን ትራኦሬ ቡድኑን ተቀላቅሏል። በሀምበርቾ በኩል የበረከት ወንድሙ መሰለፍ አጠራጣሪ ነው። ቅጣቱን የጨረሰው ቴድሮስ በቀለ ግን ወደ ሜዳ ይመለሳል።

አዲሱ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ በመሐል ዳኝነት ሙሉነህ በዳዳ እና ኤፍሬም ሀይለማርያም ረዳቶች ሚካኤል ጣዕመ በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት ተሰይሟል።