ሙጂብ ቃሲም በክለቡ የዕግድ ውሳኔ ተላልፎበታል

“የሥነ ምግባር ግድፈት ነው የፈፀመው” አቶ ኡቴሳ ኡጋሞ የክለቡ ስራ አስኪያጅ

“ከሥራዬ በላይ የእናቴ ጤና ይቀድማል” ሙጂብ ቃሲም

በእግር ኳስ ሕይወቱ ሁለተኛ ክለቡ ወደነበረው ሀዋሳ ከተማ በድጋሚ በ2015 የውድድር ዘመን በመቀላቀል እየተጫወተ የሚገኘው አጥቂው ሙጂብ ቃሲም በውል መቋጫው ዓመት ከክለቡ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ይገኛል። ከአማካይ ስፍራ እግር ኳስን የጀመረው እና በመቀጠል በአብዛኞቹ የመጫወቻ ቦታዎች ላይ ተጫውቶ አሳልፎ በአሁኑ ሰዓት በአጥቂ ስፍራ ላይ ውጤታማ ሆኖ የዘለቀው ሀዋሳን በአምበልነትም ጭምር እያገለገለ ያለው ሙጂብ ቃሲም ከክለቡ ሀዋሳ ጋር ያለፉትን ከአንድ ወር በላይ ጊዜያት አይገኝም። የእናቱን ህመም ተከትሎ ለክለቡ አሰልጣኝ ፍቃድ ጠይቆ እንደሄደ ተጫዋቹ ቢናገርም ክለቡ የተሰጠውን ቀን አልፏል ሆን ብሎ ያደረገው ነው በሚል ሁለት ጊዜ ተጫዋቹ ላይ ማስታወቂያን ካወጣ በኋላ በመጨረሻም ክለቡ የዕግድ ውሳኔን በተጫዋቹ ላይ በማሳለፍ ለፌድሬሽኑ ውሳኔውን አሳውቋል። ደብዳቤ ቢፅፍም እስከ አሁን ተቀባይነት ሳያገኝ ከክለቡ ጋር እንደማይገኝ እና ዕግድ የተወሰነበትን ሙጂብ ቃሲም እና የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ኡቴሳ ኡጋሞን ሶከር ኢትዮጵያ ስለ ጉዳዩ በዝርዝር ጠይቃለች።

በቅድሚያ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ኡቴሳ ሀሳባቸውን እንዲህ ሲሉ ያስረዳሉ “እስከ አሁን አልመጣም ባለፈው እንደዚህ ሆኜ ነው መጥቻለሁ አለ። የተሰጠው ፍቃድ እና እርሱ የመጣበት ጊዜ ሰማይ እና ምድር ነው ትልቅ ኃላፊነት የተሰጠው ሰው ነው ትልቅ ዋጋ እና ገንዘብ የተከፈለበትም ነው። ቢያንስ ይሄን ክለብ መቆጣጠር ያለበት እርሱ ነው በአጠቃላይ ተስፋም የምናደርገው ማለት ነው። የተፈቀደለትን አራት ቀን ተጠቅሞ መመለስ ሲገባው እርሱም አይቻልም አሰልጣኙ ፅሕፈት ቤቱ በማያውቀው መፍቀድም አይችልም ቢፈቅድም አንድ ሁለት ቀን ነው መፍቀድ ያለበት ከሁለት ቀን በላይ ሲሆን ለፅሕፈት ቤቱ ነው የሚያሳውቀው አደጋ ካልተፈጠረ ወይም በህመም ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ይሄ ከሆነ ደግሞ ሀኪሙ ነው የፍቃዱን ሁኔታ የሚገልፅልን ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ ሄደ ቆየ እናቴ ታማ ብሎ ደውሎ ነገረኝ እናቴ ታማ አለ የእናትህ መታመም እና ይሄ ጉዳይ ምን አገናኘው ጦር ሜዳ ከሄድክ እናቴ ታመመች አክስቴ ታመመች ይባላል እንዴ ኃላፊነት አትሰጥም ገንዘብን ወስደሀል ከክለቡ በወሰድከው ገንዘብ ደግሞ ዘመድ እንኳን ባይኖር ሰው ቀጥረህ ነው መምጣት ያለብህ እያስታመምኩ ነው የሚባል ቀልድ እንዴት ስፖርት ላይ ይሠራል? ስለዚህ አንተ ሥራውን አልፈለግክም ውጤታማም አይደለህም ውጤታማ ሳትሆን ተሸክመን እየሄድንም አንተ በተጨማሪ እናቴ ታመመች ብለህ በጭራሹ ከክለቡ መጥፋት ምን ማለት ነው? ክለቡ ልምምድ በሚያደርግ ሰዓት ላይ አልተገኘም ባለፈው ወደ ልምምድ ሲገቡም ከተፈቀደው ጊዜ ጀምሮ የለም ስለዚህ ክለቡን ማገልገል እና መጥቀም ሳይሆን የፈለገው እያላገጠ እንደፈለገ መሆን ነው። ቡድኑ ደግሞ ውጤት አልባ እየሆነ ሲመጣ እርሱ የባሰ ደግሞ የማበላሸት ሥራ የስነ ምግባር ግድፈት ነው የፈፀመው በዚህ ምክንያት እኛ የማፈላለጊያ ማስታወቂያ አወጣን በዛም አልተገኘም እንደገናም አወጣን አልተገኘም እንዲህ ሆኛለሁም አላለም ፤ የለም። መጨረሻ ላይ እኛ ይሄ ሰው የት እንዳለ ስለማናውቅ ማገድ አለብን ብለን አግደነዋል። ስልክ ደወለ ማመልከቻ ፅፎ ነበር ከእናቴ የሚበልጥ ነገር ስለሌለ እናቴን እያስታመምኩ ነው ነው የሚል ማመልከቻ ፅፏል ቤቱ ሆኖ።”

የክለቡን ሥራ አስኪያጅን ሀሳብ ተንተርሰን የዕግድ ውሳኔ ተላለፈበት የተባለውን የክለቡ አምበል እና አጥቂ ሙጂብ ቃሲም አናግረንም ተከታዩን ምላሽ እንዲህ ሰጥቶናል።

“ከባህር ዳር ጨዋታ በኋላ ፍቃድ ጠይቄ ነው የወጣውት ተደውሎልኝ ነበር ከጨዋታው በፊትም እናቴ እንደታመመች ያውቃል አሰልጣኝ ዘርዓይ ደውለውልኝ ከጨዋታው በፊትም እናቴ ህክምናም ላይ ስለነበረች አሟታል ና አሉኝ የግድ ደግሞ ጨዋታውን መጫወት ስለነበረብኝ የባህርዳርን ተጫውቼ በጠዋቱ ተነስቼ ዘርዓይ ጋር ስደውል ስልኩ አይሠራም። ብርሀኑ ፈየራ ነበር (ምክትል አሰልጣኝ) ልወጣ ስል ቡድን መሪውን አገኘሁት ፣ ዘርዓይ ስልኩ አይሠራም ትናንት ነው ስልክ የተደወለልኝ እናቴ ታማለች ዘርዓይ ደግሞ ያውቃል ከዚህም በፊት እንደታመመች ስለዚህ ልሄድ ነው ስለው ኧረ ችግር የለውም ሂድ ሂድ አለኝ ከቡድን መሪው ቀጥዬ ለፈየራ ስደውል ኧረ ችግር የለውም ነገርከው ለዘርዓይ ሲለኝ ዘርዓይ ስልኩ እንቢ ብሎኛል አልኩት ነገረው። ልክ ቤት እንደደረስኩኝ ደወልኩለት ለዘርዓይ እናቴ እንደሚያማት ታውቃለህ ድንገት አመማት ተብሎ ወደ ወንዶ ሄጄ ድጋሚ ወደ አዲስ አበባ ይዣት መሄድ አለብኝ ስለዚህ እርሷን ማሳከም አለብኝ ፤ ኧረ ችግር የለውም አለ። ተነስቼ ከሥራዬ በላይ የእናቴ ጤና ይቀድማል በሚል እርሷን ወስጄ ህክምና ድንገት ደግሞ እኔ ነኝ እርሷን ሳመላልሳት የነበረው እና ሰውም ስለሌለ ሚስቴም ደግሞ ልጆች ስላሉ በዛ መሠረት ግድ እኔ መገኘት አለብኝ በሚል ብዙ ምርመራም ስለምታደርግ አመላለስኳት። አጋጣሚ ቀኑ ሄደ አስራ አምስት ቀን ሆነ ገና በአስር ቀን በአስራ አምስት ቀን ውስጥ ነው አትገባም ብለው ደወሉልኝ ሲደውሉልኝ እነርሱ በጊዮርጊስ ተሸንፈው ወደ ሀዋሳ ሄዱ ከዛ ወዲያው ስብሰባ አደረጉ ዘርዓይንም ገመገሙት መሰለኝ እንደ ወጣ ተገምግሚያለሁ ምናምን አለ አይዞህ ያጋጥማል ውጤት ሲጠፋ እንደዚህ ነው አልኩት እና ና ድረስ በቃ አለኝ እንዴት ጥዬ ልምጣ ለማን ጥዬ ልምጣ ቢያንስ ምርመራ አላት እንደገና ቁስል ላይ ነው ያለችው ለማን ጥያት ልምጣ አልኩ ፤ መድረስ አለብህ ግዴታ ነው እንዲህ ብለውኛል ምናምን አለ። እኔ ደግሞ ምንም ማድረግ አልችልም የእናቴ ነገር ከእኔ ከሥራዬ በላይ ስለሆነ አልችልም አልኩት ለማንኛውም ነገ ድረስ አለኝ ልጆች ወደ ዝግጅት ገቡ ቡድን መሪው ደወለልኝ ያለውን ነገር አስረዳኋቸው ያለሁበት ሁኔታ ይሄ ነው አልኩ። ሰዎቹ ጫና ፈጥረውብኛል እኔንም አባርርሃለው አሉኝ እኔ ምንም ማድረግ አልቻልኩም ከፈለጋችሁ ኑና አሳክሙልኝ እኔ መጥቼ ልጫወት አልኩ በጣም አጨናነቁኝ ፣ መጨረሻ ላይ መቼም ኃላፊነት የሚወስደው አሰልጣኙ ነው ፈቅጄለት ነው የሄደው እናቱ ታማ ነው ኃላፊነት የምወስደው እኔ ነኝ ቢል ደብዳቤ የሚባለውን ነገር አይመጣም። ከዛ ሄዶ ለእነርሱ ከአቅሜ በላይ ሆኗል ሆን ብሎ ነው የሄደው ከሀገር ለቆ ጠፍቶ ምናምን ተባለ ተብሎ ልጆች ነው የሚነግሩኝ ሜዳ ላይ ተለጥፏል ደብዳቤ ብለው ከፈለጉ ጀርባቸው ላይ ለጥፈው ያዙት ሲሻላት እኔ መጣለሁ ዋናው እናቴ ይሻላት እንጂ ከዛ ሄድኩኝ ጨርሼ አዳማ ከመሄዳቸው በፊት ሄድኩኝ ፣ ስሄድ ኡቴሳ ጋር ደወልኩ አላነሳ አለኝ በሌላ ስልክ አገናኙኝ አውርቼው ወደ ክለቡ ልቀላቀል ማለት ነው። ዘርዓይን አውራው ውሳኔ ገና አልወሰንም እናሳውቅሃለን የምን ውሳኔ ነው ስል መወሰን አለበት ቦርዱ ተሰብስቦ እንደዛ ከሆነ ቶሎ ወስኑና ንገሩኝ ብዬ ትቼ ወደ ቤት መጣሁ አትቀላቀል ስላሉኝ።” ሲል ተጫዋቹ ለሶከር ኢትዮጵያ ምላሹን አሳውቋል።