ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማ ከናፈቀው ድል ጋር ታርቋል

ብርቱካናማዎቹ በቻርለስ ሙሴጌ እና ካርሎስ ዳምጠው ግቦች ኢትዮጵያ መድንን 2-1 በመርታት ወሳኝ ድል ተቀዳጅተዋል።

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ኢትዮጵያ መድን እና ድሬዳዋ ከተማ ሲገናኙ ከባለፈው ሳምንት ጨዋታ ኢትዮጵያ መድኖች በሲዳማ ቡና ከተረታው ስብስባቸው አሚር ሙደሲር እና ብሩክ ሙሉጌታን አሳርፈው በመሐመድ አበራ እና ኦሊሴማ ቺኔዱ ሲተኩ በፋሲል ሽንፈት አስተናግደው በነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በኩል ዳንኤል ተሾመ ፣ አቤል አሰበ ፣ ሔኖክ ሐሰን እና ዳዊት እስጢፋኖስ አርፈው አብዩ ካሳዬ ፣ ያሬድ ታደሠ ፣ ኤፍሬም አሻሞ እና ቻርለስ ሙሴጌ ተተክተዋል።

09፡00 ላይ በዋና ዳኛ ዳንኤል ይታገሡ ፊሽካ በተጀመረው ጨዋታ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታው የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ 2ኛው ደቂቃ ላይ በመድኖች አማካኝነት ሲደረግ ወገኔ ገዛኸኝ በግራ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው በርናንድ ኦቼንግ በግንባር ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ በኳሱ አቅጣጫ የነበረው በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ግብ ጠባቂው አብዩ ካሣዬ ይዞበታል።

ጨዋታው 6ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግብ ተቆጥሮበታል። አሰጋኸኝ ጴጥሮስ በግራ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ከአንድ ንክኪ በኋላ ያገኘው ቻርለስ ሙሴጌ በእግሩ በመግፋት ግብ አድርጎት ድሬዳዋ ከተማን መሪ አድርጓል።

ግብ ካስተናገዱ በኋላ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ያፈጠኑት ኢትዮጵያ መድኖች 12ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። መሐመድ አበራ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) የመታው ኳስ በግቡ አግዳሚ ሲመለስበት የተመለሰውን ኳስ ያገኘው ቹኩዌሜካ ጎድሰንም በግንባሩ ገጭቶት በድጋሚ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል።

25ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጣሪውን ቻርለስ ሙሴጌን በጉዳት አጥተው ካርሎስ ዳምጠውን የተኩት ብርቱካናማዎቹ ያደረጉት ለውጥ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ሲያጠናክርላቸው 40ኛው ደቂቃ ላይም ውጤታማ አድርጓቸዋል። ተቀይሮ የገባው ካርሎስ ዳምጠው ከሳጥን አጠገብ የተገኘውን የቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ በመምታት በግቡ የቀኝ ክፍል በኩል መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ከዕረፍት መልስ አስደናቂ አጀማመር ያደረጉት ኢትዮጵያ መድኖች 49ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸው ግብ አስቆጥረዋል። ግብ ጠባቂው አብዩ ካሣዬ ተጫዋች ለማለፍ ሲሞክር ተቀምቶ ኳሱን ያገኘው በአጋማሹ ተቀይሮ የገባው ያሬድ ዳርዛ ወደ ግብ የመታው ኳስ በተከላካይ ሲመለስ የተመለሰውን ኳስ ያገኘው ወገኔ ገዛኸኝ ግብ አድርጎታል።

ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር መድኖች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ይውሰዱ እንጂ በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው እየተቀዛቀዙ ሲሄዱ ድሬዎች በአንጻሩ ግብ ሲያስተናግዱ ከነበራቸው መረበሽ እየተላቀቁ በመሄድ በተሻለ የራስ መተማመን ጨዋታውን አስቀጥለውታል። ሆኖም 75ኛው ደቂቃ ላይ ወገኔ ገዛኸኝ በሳጥኑ የግራ ክፍል ይዞት በገባው ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አብዩ ካሣዬ መልሶበት የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።  በዚህ እንቅስቃሴም የድሬዳዋው የመስመር ተከላካይ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ከፍተኛ ጉዳት አስተናግዷል።

በቀሪ ደቂቃዎችም ጨዋታው እየተቀዛቀዘ ሄዶ በሁለቱም በኩል ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረግ ሲቀር 89ኛው ደቂቃ ላይ የመድኑ ተከላካይ በርናንድ ኦቼንግ ለራሱ ግብ ጠባቂ በግንባር ገጭቶ ያቀበለው ኳስ መረቡ ላይ ሊያርፍ ሲል ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ በግሩም ቅልጥፍና አስወጥቶታል። ይህም የመጨረሻው ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።