የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ መድን 1-2 ድሬዳዋ ከተማ

“ከፍተኛ ትግል አድርገን ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ችለናል” አሰልጣኝ አስራት አባተ

“ሽንፈት ላይ ስትሆን ሁልጊዜ በጣም ስህተቶች ይጎላሉ” አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ

ድሬዳዋ ከተማ የዓመቱ ሦስተኛ ድሉን ኢትዮጵያ መድን ደግሞ ስድስተኛ ሽንፈቱን ካስተናገደበት ጨዋታ መቋጫ በኋላ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ አስራት አባተ – ድሬዳዋ ከተማ

የዓመቱን ሦስተኛ ድል ስላሳኩበት ጨዋታ…

“ጠንካራ እና ከባድ ጨዋታ ነው ሁለታችንም በአንድ ነጥብ ልዩነት ነበር የነበርነው። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ጨዋታን ማሸነፍ አልቻልንም ተሸንፈናል እና ይሄን ጨዋታ ማሸነፍ በተቻለ መጠን ከቡድኖች ጋር ያቀራርበናል አሁን ካለንበትም ስለሚያስወጣን ከፍተኛ ትግል አድርገን ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ችለናል።”

ከመጀመሪያው አጋማሽ ሁለተኛውን አጋማሽ ሲጀምሩ መቀዛቀዛቸው ከምን አንፃር…

“የተቀዛቀዝንበት ምክንያት የሚመስለው በዛ ደረጃ አይደለም። አንደኛ ታክቲካሊ ነው ፣ ሁለተኛ ከጥንቃቄ ማነስ ግብ ጠባቂያችን ኳስን እግሩ ላይ አዘግይቶ ጎል ተቆጠረብን ፣ ከዕረፍት በኋላ ሦስተኛው ደቂቃ ላይ ያ ደግሞ እነርሱ እንዲነሳሱ አድርጓል የእኛን ልጆች ደግሞ እንደገና ፍርሃት ውስጥ ከትቷል እና ያ በተወሰነ መልኩ ጭንቀት የሚመስል አይነት አጨዋወቶች ነበሩ ሆኖም ግን በትግል ጨዋታውን ማሸነፍ ችለዋል።”

በጨዋታው ቻርለስ ሙሴጌ እና አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ስለ ገጠማቸው የጉዳት መጠን…

“አሁን በዋነኝነት ቡድናችንን እኛ እናጉላው እንጂ እየፈተነን ያለው ጉዳት ነው። ተመስገንም ከፍተኛ ጉዳት ላይ ነው ኤፍሬምም እንግዲህ የመጫወት ፊትነሱ እንደምናየው ነው ከረጅም ጉዜ ጉዳት ነው የመጣው ዛሬም ፣ ካርሎስ የገባው ከነ ጉዳቱ ነው ቻርለስ ሙሴጌም ባለፈው ጨዋታ ላይ አልነበረም ከነ ጉዳቱ ነበር ፣ ጎሉ ከገባም በኋላ በጊዜ ነው ተቀይሮ የወጣው እነዚህ እና መሰል ነገሮች እያጋጠሙን ነው ያለው ፣ እንደገና ሱራፌልም አገግሞ ነው የመጣው ምናልባት የአሰጋኸኝ ጠንከር ያለ ይመስለኛል በኋላ እንግዲህ የህክምና ክፍሉ የሚለውን ሰምተን ለቀጣይ ጨዋታ የምንዘጋጅ ይሆናል። አሁን ላይ ይሄ ነው ማለት ትንሽ የሚከብድ ይመስለኛል።”

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ – ኢትዮጵያ መድን

ስለ ጨዋታው…

“ዛሬ ጥሩ ነው በእርግጥ በእንቅስቃሴ ደረጃ ፣ በጥረት ደረጃ ተነሳሽነት ነበር  ብዙዎቹ በጣም ጥሩ ነው። አንዳንድ ጊዜ በዚህ ሽንፈት ላይ ስትሆን ሁልጊዜ በጣም ስህተቶች ይጎላሉ እና በጣም ወሳኝ የሆኑ እንደዚህ እንደ ዕድል ሆኖ በተጋጣሚ ዘንድ አጋጣሚን የማግኘት ዕድል ይኖረዋል ፣ የምንፈፅማቸው ስህተቶች ከጉጉትም የተነሳ ዝም ብሎ የምትሳሳታቸው ስህተቶች አሉ። አሁን ለምሳሌ ቅጣት ምት የተመታብን ርስ በርስ በነበረው ግጭት ዝንጉ በመሆን ነው የማዕዘን ምት የተመታብን ራሳችን ያወጣነው ኳስ እንደዚሁ ነው ፣ ችግሮች የመጡት ከሽንፈቶች ተያይዞ የመጣ ነገር ነው። በተረፈ ግን ዛሬ እንቅሰቃሴያችን መጥፎ አይደለም ጥሩ ነው።”

በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ አጀማመር እና ፍጥነት ኖሯቸው ግን እንቅስቃሴው ስላልቀጠለበት ምክንያት…

“ተጋጣሚ የያዘውን ይዞ ለመውጣት የሚያደርገው ጥረት አለ ፣ ሙሉ አቅሙን በመከላከል ላይ ነው የሚሆነው እና የመጨረሻው የማጥቂያ ዞኑ ላይ በሙሉ ተሰብስበዋል ወይም ሹት አድርገህ ነው ወይም ደግሞ አንድ ለአንድ ማሸነፍ አለብህ ወይሞ ደግሞ በመሐል ለመሐል ነው እና በዚህ ማሸነፍ አልቻልንም። ረጃጅም ኳሷች ላይ እነርሱ ያሸንፋሉ ፣ በሌላ በኩል ካለህ የግል አቅም በጣም ወሳኝነት አለው ፣ ስለዚህ አውት ስታንዲንግ የሆነ ተጫዋች ያስፈልግሃል ፣ በዚህ ካልሆነ በስተቀር መጥፎ አይደለም።”

ከሜዳ ስለራቀው ሀቢብ ከማል የጉዳት ሁኔታ…

“አናውቀውም ፣ የህክምና ጉዳይ ነው የሚሆነው እስከ አሁን ያገኘነው ኢንፎርሜሽን ወደ ጂም እንደሚሄድ ነው  የተገነዘብኩት ፣ ከዛ ውጪ ሀኪሞች የሚሉትን መረዳት መቻል አለብን ፣ ጂም ላይ ሲደርስ ምን አይነት እንቅስቃሴ እያደረገ ነው የሚለውን የምናይ ይሆናል እርሱን ካየን በኋላ ነው የምናውቀው።”