የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 0-0 አዳማ ከተማ


“የተጫዋቾች አንድነት እና ሕብረት እጅግ በጣም ደስ ይላል” አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት

“ከጎል ጋር ያለን ርቀት እየበዛ ነው” አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ

በምሽቱ መርሐግብር ወልቂጤ ከተማ እና አዳማ ከተማ ጨዋታቸውን ያለ ግብ ካጠናቀቁ በኋላ ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኞቹ ጋር ቆይታ አድርጋለች።

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

“ጨዋታው አሪፍ ነበር። ሁለታችንም ነጥቦች ያስፈልጉናል። ከተደጋጋሚ ሽንፈቶች በኋላ አቻ ወጥተናል። በቀጣይ ደግሞ የተሻለ ነገር እንሠራለን።

ቡድንህ ላይ ያለው ማስቀጠል የምትፈልጉት ጥንካሬው…

“ቡድኑ ያው ሰሞኑን ቢሸነፍም በጣም ጠንካራ ነው። የተጫዋቾች አንድነት እና ሕብረት እጅግ በጣም ደስ ይላል። ወደ ድል ለመምጣት የሚቀረን ጎል ማስቆጠር ብቻ ስለሆነ በቀጣይ ሠርተንበት እንመጣለን።”

የወልቂጤ ከተማ ጉዞ ከውጤት አንጻር….

“እንግዲህ ያው ውድድሩ እንደምታየው ትንሽ ጠንከር ይላል። እኛም በተቻለ አቅም የተሻለ ነገር ለማምጣት እና የተሻለ ቦታ ላይ ሆነን ለመጨረስ ያለንን ጠንካራ ነገር ማስቀጠል ነው።”

ስለ ታዳጊው መድን ተክሉ…

“መድን በጣም ጥሩ ተጫዋች ነው እንዳያችሁት ወደፊት ትልቅ ተጫዋች መሆን የሚችል ነው እና በብዛት ሜዳ ላይ የሚያሳየው ነገር ይናገራል። እሱን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የእሱ ዓይነት ተጫዋቾች ብዙ ስላሉ ይሄ ደግሞ የእኛ ሥራ እና ኃላፊነት ስለሆነ እንደዚህ ዓይነት ልጆችን ማብቃት እና ማሳደግ የተሻለ ነገር እንዲያደርጉ ዕድል መስጠትን ጨምሮ ፤ መድን ራሱን የቻለ ጥሩ ልጅ ነው።”

አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ – አዳማ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

“ከውጤት ጋር ሲታጀብ ነው ጨዋታው ጥሩ ነው የምትለው እና ከጎል ጋር ያለን ነገር ሩቅ ሆኗል እና እሱን ማስተካከል ነው።”

በተከታታይ ጨዋታዎች የአጥቂ መስመሩ ላይ ስለሚታየው አለመረጋጋት…

“ያው አጥቂ መስመር ላይ እነ ቢኒያም ዮሴፍ እና ነቢል ታዳጊዎች ናቸው እና ሦስተኛው ሜዳ ላይ ደግሞ መረጋጋት ይፈልጋል ያንን ደግሞ ከጌም ጌም ነው እየቀረፍን የምንሄደው እንደዛም ሆኖ ግን ጎሎች ያስፈልጋሉ ምንም ጥርጥር የለውም ከጎል ርቀናል እሱን ነገር ማስተካከል አለብን።”

ዛሬ ላይ ያየኸው የቡድን ጠንካራ እና ደካማ ጎን…

“ቡድኑ ላይ ያለው ጠንካራ ጎን ብዬ የማስበው ያላቸውን ነገር መልቀቅ አልፈለጉም በባለፈው በሲዳማው ጨዋታም ኳስን መሠረት አድርገው ለመጫወት ይሞክራሉ በዛ ነው ጎል ጋር የሚደርሱት ፤ በአጋጣሚዎች መድረስ አይፈልጉም። ጎል ካልሆነ ውጤቱ እንደምታየው ነው የሚሆነው እና ጎል ጋር ያለን ርቀት እየበዛ ነው።”