ሪፖርት | የወልቂጤ እና አዳማ ጨዋታ ያለ ጎል ተቋጭቷል

ጥራት ያላቸውን የግብ ዕድሎች ብዙም ያላስመለከተን የወልቂጤ ከተማ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ 0ለ0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ወልቂጤ ከተማ ካለፈው የፋሲል ሽንፈት በቃሉ ገነነን በመድን ተክሉ ያደረጉት ብቸኛ ለውጣቸው ሲሆን ከሲዳማ ጋር ነጥብ ተጋርተው በነበሩት አዳማ ከተማ በኩል በተደረገ ሁለት ለውጥ አቡበከር ሻሚል እና ቦና ዓሊን በቻርለስ ሪባኑ እና ነቢል ኑሪ በመቀየር ለጨዋታው ቀርበዋል።

የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስታዲየም እንደነበረው ቀዝቃዛ ዓየር ሁሉ ተመሳሳይ የሜዳ ላይ መልክ የተላበሰው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥራት ያለውን ሙከራ ለመመልከት ሀያ ስድስት ደቂቃዎች ለመጠበቅ የተገደድንበት ነበር። በንፅፅር የቻርልስን ረጃጅም ኳሶች በመጠቀም ዮሴፍ እና ቢኒያምን ባማከለ ሁኔታ ወደ መስመር በማዘንበል ወደ ሳጥን በሚጣሉ ኳሶች አዳማ ከተማዎች ለመጫወት የሄዱበት መንገድ ከተጋጣሚ አንፃር ትኩረት የሚስብ ሆኖ ተስተውሏል። ቢኒያም አይተን አቅጣጫዋን የቀየረች ሙከራን ወደ ጎል መቶ በሙከራ ረገድ አዳማን ቀዳሚ ቢያደርግም ከአራት ማዕዘኑ ጎል ጋር የሚገናኙ ኳሶች አልነበሩም።

በመጠኑ ለኋላ ክፍላቸው ሽፋን በመስጠት በሽግግር ለመጫወት ጥረት ያደርጉ በነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች አቡበከር ሳኒ አመቻችቶ ሰጥቶት ከግራ መነሻውን ያደረገው አሜ ተፈጥሯዊ ባልሆነ እግሩ የመታቴ ኳስ የግራ የግቡን ቋሚ ታካ ወደ ውጪ ወጥታለች። ወደ ጎል አስቆጣሪነት ለመምጣት ዮሴፍ እና ቢኒያምን ባነጣጠረ የጨዋታ መንገድ የቀጠሉት አዳማዎች ዮሴፍ እና ቻርለስ በጥሩ መናበብ ያሰናዱለትን ኳስ ቢኒያም አይተን ባለመረጋጋት ውስጥ ሆኖ ሞክሮ ከመከነችው ኳስ በኋላ 26ኛ ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥራትን የተላበሰች ቆንጆ ጎል ሞክረዋል።

በተጠቀሰው ደቂቃ ዮሴፍ ከቀኝ ወደ ወልቂጤ የሜዳ ክፍል መሬት ለመሬት የሰጠውን መስዑድ በጥሩ ዕይታ አቀብሎ ከግቡ ጋር ፊት ለፊት ቆሞ የነበረው ነቢል ኑሪ ነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ የሞከራትን ግብ ጠባቂው ፋሪስ ዕላዊ በአግባቡ ይዞበታል። አዳማ ከተማዎች 43ኛው ደቂቃ ላይ በዮሴፍ ታረቀኝ አማካኝነት ጎልን ቢያስቆጥርም የዕለቱ ሁለተኛ ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ ከጨዋታ ውጪ ካሉ በኋላ ጨዋታው ያለ ጎል ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።


በሁለተኛ አጋማሽ ጨዋታው ሲቀጥል መጠነኛ ግለቶችን ያየንበት ግን አሁንም ከጥራት አኳያ ደካማ የግብ ዕድሎችን አሳይቶናል። አዳማ ከተማ ከፍ ባለ ተነሳሽነት በተመለሱበት በዚህ አጋማሽ ከዕረፍት ከተመለሱ አራት ደቂቃዎች እንደተቆጠሩ ግልፅ ዕድል ፈጥረዋል። መስዑድ ከቀኝ ወደ ውስጥ ያሻገረውን የቅጣት ምት ፍቅሩ ዓለማየሁ በግንባር ጨርፎ ያቀበለውን ነቢል ኑሪ በቀላሉ አስቆጠረው ሲባል ፋሪስ ከጎልነት ኳሷን ታድጓታል።

ለስህተት ተጋላጭ የነበረውን የአዳማን መከላከል በሚፈትን መልኩ በሽግግር ለመጫወት የጣሩት ወልቂጤ ከተማዎች አሜ መሐመድ ግልፅ የግብ ዕድል ፈጥሮ ካመከናት፣ በመልሶ ማጥቃት ደግሞ የአዳማ የግብ ክልል የደረሰችውን ኳስ ዮሴፍ ታረቀኝ በተቃራኒው ለአዳማ መልካም አጋጣሚን ፈጥሮ ሳይረጋጋ የመታት ኳስ ወደ ውጪ ወጥታች። የአጋማሹ የመጨረሻ ሀያ አምስት ደቂቃዎች ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ ፉክክርን እያሳየን ጨዋታው ቀጥሎ 61ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ተመስገን በጅሮንድ ጥሩ ዕድልን ፈጥሮ በወልቂጤ በኩል አስተውለናል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ቦና ዓሊ አዳማን አሸናፊ ልታደርግ የምችል አጋጣሚን አግኝቶ ግብ ጠባቂው ፋሪስ ዕላዊ ካዳናት ኳስ በኋላ ከእንቅስቃሴ ውጪ በሙከራ መድመቅ ያቃተው የቡድኖቹ ጨዋታ በመጨረሻም ያለ ጎል ፍፃሜውን አግኝቷል።