የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 1-2 ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳ ከተማ ከአምስት ተከታታይ ሽንፈቶች አገግመው ወደ ድል ከተመለሱበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጡት አስተያየት እንደሚከተለው ቀርቧል።

አሰልጣኝ ዘርዐይ ሙሉ

ስለ ጨዋታው

ተከታታይ ሽንፈቶች አስተናግደናል፤ በአሰልጣኝነት ታሪኬ ለመጀመርያ ጊዜ ነው። ለክለቡም እንደዛው። የውስጥ የተወሰኑ ችግሮች ነበሩ፤ እሱን የመፍታት ስራ ነው የሰራነው። ቡድኑ ውስጥ ብዙ ወጣት ተጫዋቾች አሉ ዛሬ ሙሉ ጉልበታቸውን ሰጥተዋል፤ የቡድን መንፈሱ እጅግ የሚገርም ነበር። ብዙ ጎሎች መግባት ይችሉ ነበር አጥቂዎቻችን በጫና ብዙ ጎል የሚሆኑ ዕድሎችም አባክነዋል፤ ቢያንስ አራት አምስት ግቦች ማስቆጠር ነበረብን። ጫናው ነው እንደዚ ያደረጋቸው። እንደ ቡድን ወደ አሸናፊነት መመለሳችን የነበረን ተነሳሽነት ያሳያል፤ ምክንያቱም በሊግ እያንዳንዱ ጨዋታዎች ላይ ተነሳሽነት ይፈልጋል። ከሽንፈት ድባብ ወጥተን ወደ አሸናፊነት ተመልሰናል ቀሪ ባሉት ጨዋታዎች ጠንካራውን ሀዋሳ ይዘን እንቀርባለን። በወጣቶች ላይ ይበልጥ ሰርተን ቀጣይ የተሻለ እናደርጋለን ምክንያቱም ደጋፊዎቻችን ይሁን የክለብ አመራር አሳዝነናል። ለኛም ለነሱም ድንጋጤ ፈጥሯል፤ ዛሬ ወደ ድል መመለሳችንና በዚ ጭንቀት ውስጥ ሆነ እንደዚ መንቀሳቀሳችን የቡድኑ ጥንካሬ ያሳያል። በርግጥ ባለፉት ጨዋታዎችም ጥሩ እንቅስቃሴ ብናደርግም በጥሩ የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ስላልነበር ነው የተሸነፍነው።

ስለ ቡድኑ የዛሬው ጥንካሬ

ከዚ በፊትም የጎል ዕድሎች ፈጥረን ነበር፤ ባለፉት ሦስት አራት ጨዋታዎች ብዙ ዕድሎች ፈጥረን ነበር፤ በአማካዩና አጥቂው ያለው ቅንጅት ጥሩ ነው። የላላው የተከላካይ ክፍሉ ነው። ወደ ፊት ስንሄድ እጅግ በጣም ጥሩ ነው። በተለይም በፊት አጥቂያችን ዐሊ ሱሌይማን አማካኝነት ብዙ ዕድሎች ፈጥረን ነበር፤ ከዚ በኋላ ግን እሱም ጫናው ስለሚቀንስለት የሚያገኛቸው ዕድሎች ይጠቀማል ብዬ አስባለው። ባጠቃላይ ቡድናችን በጥቂት ስህተቶች ነበር ሲሸነፍ የነበረው፤ ዛሬ እሱን አርመናል።

አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ጥሩ ነው የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገናል። አንዳንድ ጥቃቅት ስህተቶች ስለነበሩ በዛ ዋጋ ከፍለናል። ጎሎች የገቡበት መንገድ ዋጋ አስከፍሎናል።

የወሳኝ ተጫዋቾች በጉዳት አለመኖር የፈጠረው ተፅዕኖ

የነሱ አለመኖር ተፅዕኖ ይፈጥራል፤ ቢሆንም ግን ያን ያህል የጎላ አልነበረም። የተሻሉ ዕድሎች መፍጠር የምንችልበት አጋጣሚ አግኝተናል። የሰራናቸው የማይጠበቁ ጥቃቅን ስህተቶች ዋጋ አስከፍለውናል። ጎሎችን ለማስቆጠር ባደረግነው ሂደትም ከፍተኛ ጉልበት ነው ያወጣነው፤ ከዛ በተጨማሪም ከሦስት ቀን በኋላ ነው የተጫወትነው
እሱም ተፅዕኖ ነበረው።

ስለ ተከላካይ ክፍሉ መዘናጋት

በቀጣይ ይታረማል፤ እግር ኳስ አንዳንዴ ስህተቶች ይኖራሉ፤ ከስህተቶቹ ተምረህ ነው ለቀጣይ የምትዘጋጀው። ስህተቶች አይኖሩም አልልም፤ አንዳንዴ አጥቂዎች ይሳሳቱና ጎል ሳናስቆጥር ልንወጣ እንችላለን። ዛሬ ግን የኋላ ክፍላችን ጥሩ አልነበረም፤ እሱም ዋጋ አስከፍሎናል። ከዕረፍት በኋላ ተስተካክለን ገብተን ብዙ ጥረት አድርገናል ግን መጀመርያው አጋማሽ ያጣነው መመለስ አልቻልንም።